በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለነጠላ ወላጆች አሳቢነት አሳይ

ለነጠላ ወላጆች አሳቢነት አሳይ

ለነጠላ ወላጆች አሳቢነት አሳይ

ከነጠላ ወላጆች የበለጠ ብዙ ጊዜና ጉልበት የሚጠይቅ ተደራራቢ ኃላፊነት ያለበት ሰው የለም ማለት ይቻላል። * ነጠላ ወላጆች የሚገጥማቸው ተፈታታኝ ሁኔታ ስፍር ቁጥር የለውም። እነዚህ ወላጆች ቤተሰብ ማስተዳደር የሚጠይቀውን ዘርፈ ብዙ ኃላፊነት መወጣት አለባቸው። ገቢ ለማግኘት መሥራት ያለባቸው ከመሆኑም ሌላ ገበያ መውጣት፣ ምግብ ማብሰል፣ ቤት ማጽዳትና ልጆችን ማሳደግ ይጠበቅባቸዋል። ይህም ሲባል የልጆቻቸውን ጤንነት መንከባከብ፣ እነሱን ማዝናናትና ስሜታዊ ድጋፍ መስጠት የሚቻል ከሆነ ደግሞ ጥቂትም ቢሆን ከልጆቻቸው ጋር አብረው የሚያሳልፉት አስደሳች ጊዜ ለማግኘት ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል ማለት ነው።

በነጠላ ወላጅ የሚተዳደር ቤተሰብ ቁጥር ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ ከመሆኑም ሌላ ይህ ሁኔታ በኅብረተሰቡ ዘንድ እየተለመደ መጥቷል፤ ይሁን እንጂ እነዚህ ቤተሰቦች በቀላሉ ችላ ሊባሉ ይችላሉ። አንዲት እናት “እኔ ራሴ ነጠላ ወላጅ እስከሆንኩበት ጊዜ ድረስ ለነጠላ ወላጆች ትኩረት ሰጥቼ አላውቅም ነበር” በማለት በግልጽ የተናገረችው ነገር ሐቁን ያሳየናል። ታዲያ ለነጠላ ወላጆች አሳቢነት ለማሳየት ምን ማድረግ ትችላለህ? ደግሞስ የእነሱ ጉዳይ ሊያሳስብህ ይገባል? የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማሟላት ትኩረት መስጠት ያለብን ለምን እንደሆነ እስቲ ሦስት ምክንያቶችን እንመልከት።

አሳቢነት እንድናሳይ የሚያደርጉን ምክንያቶች

ብዙ ነጠላ ወላጆች እርዳታ ማግኘት ይፈልጋሉ። ባሏ የሞተባትና የሁለት ልጆች እናት የሆነች አንዲት የ41 ዓመት ሴት “አንዳንድ ጊዜ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ግራ የሚገባኝ ሲሆን ያሉብኝ በርካታ ኃላፊነቶች ውጥረት ያስከትሉብኛል” በማለት ተናግራለች። የሕይወት አጋራቸውን በሞት ያጡ፣ የትዳር ጓደኛቸው የከዳቸው ወይም ሌላ አሳዛኝ ሁኔታ ያጋጠማቸው በርካታ ነጠላ ወላጆች አንዲት ነጠላ እናት የገለጸችው ዓይነት ስሜት ይሰማቸዋል። “እፎይታ ለማግኘት እየለመንን ነው፤ ይህ ለእኛ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው!” ብላለች።

አሳቢነት ማሳየትህ ለአንተም ደስታ ያመጣልሃል። በጣም ከባድ የሆነ ሸክም የተሸከመ ሰው አጋጥሞህ ያገዝክበት ጊዜ አለ? ከሆነ ተግባራዊ በሆነ መንገድ እርዳታ በመስጠትህ ሳትደሰት አትቀርም። በተመሳሳይም ነጠላ ወላጆች ያለባቸው ኃላፊነት አንዳንድ ጊዜ አንድ ሰው ብቻውን ሊሸከመው የማይችለው ከባድ ሸክም ሊሆን ይችላል። ለእነሱ የእርዳታ እጅህን ስትዘረጋ በ⁠መዝሙር 41:1 (NW) ላይ የሚገኘውን “ለተቸገረ ሰው አሳቢነት የሚያሳይ ደስተኛ ነው” የሚለውን ሐሳብ እውነተኝነት ትገነዘባለህ።

አሳቢነት ማሳየትህ አምላክን ያስደስተዋል። ያዕቆብ 1:27 “በአምላካችንና በአባታችን ዓይን ንጹሕና ያልረከሰ አምልኮ ወላጅ የሌላቸውን ልጆችና መበለቶችን በመከራቸው መርዳት [ነው]” ይላል። ይህ ደግሞ ነጠላ የሆኑ ወላጆችን መርዳትን ይጨምራል። * ዕብራውያን 13:16 “መልካም ማድረግንና ያላችሁን ነገር ለሌሎች ማካፈልን አትርሱ፤ ምክንያቱም አምላክ እንዲህ ባሉት መሥዋዕቶች እጅግ ይደሰታል” በማለት ይናገራል።

ለነጠላ ወላጆች አሳቢነት እንድናሳይ የሚያነሳሱንን ሦስት ምክንያቶች በአእምሯችን ይዘን እነሱን ለመርዳት ምን ማድረግ እንደምትችል እንዲሁም የምታደርግላቸው እርዳታ ተግባራዊ መሆን አለመሆኑን እንዴት ማወቅ እንደምትችል እንመልከት።

የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለይቶ ማወቅ

እርዳታ ለማድረግ ቀላሉ መንገድ “ልረዳሽ የምችለው ነገር አለ?” ብሎ መጠየቅ ሊመስል ይችላል። ይሁንና እውነቱን እንነጋገር ከተባለ፣ እንዲህ ብለህ መጠየቅህ የሚያስፈልጋትን ነገር በግልጽ እንድትናገር ላያደርጋት ይችላል። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው በመዝሙር 41:1 ላይ ‘አሳቢነት እንድናሳይ’ ተመክረናል። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንደገለጸው ይህን ሐሳብ ለማመልከት የገባው የዕብራይስጥ ሐረግ “ጥበብ የሚንጸባረቅበት አንድ እርምጃ ላይ መድረስ እንዲቻል የተለያዩ ሐሳቦችን የማውጣትና የማውረድ ሂደት” የሚል ትርጉም ሊኖረው ይችላል።

በመሆኑም እርዳታ መስጠት የምትችልበትን ከሁሉ የተሻለ መንገድ ለማግኘት ነጠላ ወላጅ የሆነችው ሴት የሚያጋጥሟትን ተፈታታኝ ሁኔታዎች በጥሞና ማሰብ ያስፈልግሃል። ሁኔታውን ላይ ላዩን ብቻ ከማየት ይልቅ አስተዋይ ሁን። ‘እኔ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ብሆን ኖሮ ምን ዓይነት እርዳታ እንዲደረግልኝ እፈልግ ነበር?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። እርግጥ ነው፣ የቱንም ያህል ብትጥር ሁኔታው እስካልደረሰብህ ድረስ ነጠላ ወላጅ መሆን ምን ማለት እንደሆነ ሙሉ በሙሉ መረዳት እንደማትችል ብዙ ነጠላ ወላጆች ሊነግሩህ ይችላሉ። ያም ሆኖ ራስህን በነጠላ ወላጆች ቦታ አስቀምጠህ ስሜታቸውን ለመረዳት መጣርህ ለእነሱ ‘አሳቢነት ለማሳየት’ የተሻለ ብቃት እንዲኖርህ ያስችልሃል።

አምላክ የተወውን ፍጹም ምሳሌ ተከተል

ለነጠላ ወላጆች አሳቢነት የማሳየት ጉዳይ ከተነሳ ፍቅራዊ ብሎም ውጤታማ የሆነ እርዳታ በመስጠት ረገድ ይሖዋ አምላክን የሚወዳደረው የለም። ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች፣ ይሖዋ የመበለቶችና አባት የሌላቸው ልጆች ሁኔታ እንደሚያሳስበው ጎላ አድርገው ይገልጻሉ፤ በሌላ አባባል የነጠላ ወላጆች ጉዳይ ይገደዋል ማለት ነው። እኛም አምላክ እንደነዚህ ያሉ ሰዎችን መሠረታዊ ፍላጎት ያሟላው እንዴት እንደሆነ በመመርመር ጠቃሚና ተግባራዊ የሆነ እርዳታ መስጠት ስለምንችልበት መንገድ ብዙ መማር እንችላለን። ልብ ልትላቸው የሚገቡ አራት ቁልፍ ነጥቦችን እስቲ እንመልከት።

አዳማጭ ሁን

ይሖዋ ለጥንቱ የእስራኤል ሕዝብ በሰጠው ሕግ ላይ ችግር ውስጥ የወደቁ ሰዎችን ‘ጩኸት በእርግጥ እንደሚሰማ’ ተናግሯል። (ዘፀአት 22:22, 23) ታዲያ ይሖዋ የተወውን ይህን ግሩም ምሳሌ መከተል የምትችለው እንዴት ነው? ነጠላ ወላጆች ሐሳባቸውን የሚያካፍሉት ትልቅ ሰው አጠገባቸው ስለማይኖር ብዙውን ጊዜ የብቸኝነት ስሜት ያጠቃቸዋል። አንዲት ነጠላ ወላጅ “ልጆቹ ከተኙ በኋላ የማለቅስበት ጊዜ አለ። አንዳንዴ ብቸኝነቱ ከአቅሜ በላይ ይሆንብኛል” በማለት በምሬት ተናግራለች። ነጠላ ወላጆች የልባቸውን አውጥተው መናገር በሚፈልጉበት ጊዜ ተገቢ ሆኖ እስካገኘኸው ድረስ ‘ጩኸታቸውን’ ለመስማት ራስህን ታቀርባለህ? ብቻችሁን በማትሆኑበት ሁኔታ ‘ለጩኸታቸው’ ጆሮህን መስጠትህ ነጠላ ወላጅ መሆን የሚያስከትልባቸውን ተፈታታኝ ሁኔታ እንዲቋቋሙ በእጅጉ ሊረዳቸው ይችላል።

የሚያበረታቱ ቃላትን ተናገር

ይሖዋ፣ እስራኤላውያን በአምልኳቸው ላይ የሚዘምሯቸውን ቅዱስ መዝሙራት በመንፈስ መሪነት አስጽፎ ነበር። በእስራኤል የሚኖሩ መበለቶችና አባት የሌላቸው ልጆች ይሖዋ ‘አባታቸው’ እና ‘ተሟጋቻቸው’ እንደሆነ እንዲሁም የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ እንደሚያቀርብላቸው የሚያስታውሷቸውን በመለኮታዊ መንፈስ መሪነት የተጻፉትን ሐሳቦች ሲዘምሩ እንዴት ሊበረታቱ እንደሚችሉ መገመት ትችላለህ። (መዝሙር 68:5፤ 146:9) እኛም፣ ነጠላ ወላጆች ለረጅም ጊዜ ሊያስታውሱት የሚችሉት የሚያበረታታ ሐሳብ መናገር እንችላለን። ሩት የተባለች አንዲት ነጠላ ወላጅ ተሞክሮ ያለው አንድ አባት “ሁለቱን ወንዶች ልጆችሽን ጥሩ አድርገሽ እያሳደግሻቸው ነው። በዚሁ ቀጥይ” በማለት የተናገረበትን ጊዜ ከ20 ዓመታት በኋላም ታስታውሰዋለች። ሩት “እነዚያን ቃላት ከእሱ መስማቴ በእኔ ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል” በማለት ተናግራለች። በእርግጥም “በደግነት የተነገሩ ቃላት ጥሩ መድኃኒት” ስለሆኑ ከምናስበው በላይ ነጠላ ወላጆችን ሊያበረታቱ ይችላሉ። (ምሳሌ 15:4 ኮንቴምፖራሪ ኢንግሊሽ ቨርሽን) አንዲትን ነጠላ ወላጅ ከልብ እንድታመሰግናት የሚያደርግህን አንድ ነገር ማሰብ ትችላለህ?

አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ቁሳዊ እርዳታ አድርግ

ይሖዋ ለጥንቶቹ እስራኤላውያን የሰጠው ሕግ መበለቶችና አባት የሌላቸው ልጆች ክብራቸውን በሚጠብቅ መንገድ የሚያስፈልጋቸውን ምግብ እንዲያገኙ የተደረገውን ዝግጅት አካቶ የያዘ ነበር። እንዲህ ያለው ዝግጅት እነዚህ የተቸገሩ ሰዎች “በልተው እንዲጠግቡ” ያስችላቸው ነበር። (ዘዳግም 24:19-21፤ 26:12, 13) እኛም በነጠላ ወላጅ ለሚተዳደሩ የተቸገሩ ቤተሰቦች አስተዋይነት በሚንጸባረቅበትና ክብራቸውን በማይነካ መንገድ ቁሳዊ እርዳታ መስጠት እንችላለን። ምግብ ወይም የምግብ ሸቀጣ ሸቀጥ ገዝተህ ቤታቸው ልትወስድላቸው ትችል ይሆን? አንዲት ነጠላ ወላጅ ወይም ልጆቿ ሊጠቀሙበት የሚችሉት ልብስ አለህ? ወይስ ቤተሰቧ የሚያስፈልጉትን አንዳንድ ነገሮች እንድትገዛ ገንዘብ መስጠት ትችል ይሆን?

አብረሃቸው ጊዜ አሳልፍ

ይሖዋ መበለቶችና አባት የሌላቸው ልጆች ከእስራኤላውያን ወገኖቻቸው ጋር አብረው መደሰት በሚያስችሏቸው መላው ብሔር በሚያከብራቸው ዓመታዊ በዓላት ላይ እንዲገኙ ትእዛዝ ሰጥቶ ነበር። እንዲያውም “ደስ ይበላችሁ” ተብለው ነበር። (ዘዳግም 16:10-15) በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ ክርስቲያኖች አብረው አስደሳች ጊዜ እንዲያሳልፉ “አንዳችሁ ለሌላው የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ አሳዩ” ተብለው ተመክረዋል። (1 ጴጥሮስ 4:9) ታዲያ በነጠላ ወላጅ የሚተዳደርን አንድ ቤተሰብ ለምን ቤትህ አትጋብዝም? ግብዣው የተንዛዛ መሆን አያስፈልገውም። ኢየሱስ በወዳጆቹ ቤት ጊዜ ሲያሳልፍ እንደተናገረው የሚያስፈልገው “ጥቂት ወይም አንድ ነገር ብቻ ነው።”—ሉቃስ 10:42

የምታሳየው አሳቢነት ይደነቃል

ሦስት ልጆችን ያሳደገች ካትሊን የተባለች አንዲት ነጠላ እናት “ምንም ነገር አትጠብቅ፤ ሆኖም የሚደረግልህን ሁሉ አድንቅ” የሚለውን ጥበብ ያዘለ ምክር ፈጽሞ እንደማትረሳ ተናግራለች። እንደ ካትሊን ሁሉ ብዙ ነጠላ ወላጆችም ልጆቻቸውን የማሳደጉ ኃላፊነት የራሳቸው እንደሆነ ይገነዘባሉ። በመሆኑም ራሳቸው ማድረግ ያለባቸውን ነገር ሌሎች እንዲያደርጉላቸው አይጠብቁም። ይሁን እንጂ የሚደረግላቸውን ማንኛውንም እርዳታ እንደሚያደንቁ ጥርጥር የለውም። ለነጠላ ወላጆች አሳቢነት በማሳየት ለደኅንነታቸው አስተዋጽዖ ማበርከት የምትችል ከመሆኑም በላይ ለራስህም ደስታ ታገኛለህ፤ በተጨማሪም ይሖዋ አምላክ ‘ስላደረግኸው ተግባር ዋጋ እንደሚከፍልህ’ እርግጠኛ ሁን።—ምሳሌ 19:17

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.2 በዚህ ርዕስ ውስጥ በአብዛኛው ነጠላ እናቶችን ብንጠቅስም መሠረታዊ ሥርዓቶቹ ለነጠላ አባቶችም ይሠራሉ።

^ አን.7 “ነጠላ ወላጅ” የሚለው አገላለጽ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባይገኝም “መበለት” እና “አባት የሌለው ልጅ” የሚሉት አገላለጾች ግን በተደጋጋሚ ጊዜ ተጠቅሰዋል። ይህ ደግሞ ነጠላ ወላጆች በጥንት ዘመንም እንደነበሩ ያመለክታል።—ኢሳይያስ 1:17

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በነጠላ ወላጅ የሚተዳደርን ቤተሰብ ለመጨረሻ ጊዜ ቤትህ የጋበዝከው መቼ ነው? ለምን በቅርቡ እንዲህ አታደርግም?