በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አንድ የምሥራቅ እስያ ሰው በጥንቷ ጣሊያን

አንድ የምሥራቅ እስያ ሰው በጥንቷ ጣሊያን

አንድ የምሥራቅ እስያ ሰው በጥንቷ ጣሊያን

ከ2,000 ዓመታት በፊት አንድ የምሥራቅ እስያ ዝርያ ያለው ሰው በጥንቷ የሮም ግዛት ሊገኝ የሚችለው እንዴት ነው? አርኪኦሎጂስቶች በ2009 በደቡብ ጣሊያን አንድ አስገራሚ ነገር በቁፋሮ ካገኙ በኋላ ይህ ጥያቄ ተፈጥሮባቸው ነበር።

ቁፋሮ የተደረገበት ቦታ በጥንት ጊዜ የሮማውያን መቃብር የነበረበት ሲሆን ይህ ስፍራ በአሁኑ ጊዜ ከባሪ በስተምዕራብ 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባለችው በቫንያሪ ይገኛል። በዚህ ቦታ የ75 ሰዎች አፅም ተገኝቷል። በአጥንቶቹ ላይ የተደረገው ጥናት አብዛኞቹ ሰዎች በዚያ አካባቢ እንደተወለዱ ጠቁሟል። ሆኖም የአንደኛው ሰው አፅም ተመራማሪዎቹን አስገርሟቸዋል። በዚህ አፅም ማይቶኮንዲሪያል ዲ ኤን ኤ ላይ የተደረገው ጥናት እንዳመለከተው ግለሰቡ በእናቱ በኩል የምሥራቅ እስያ ዝርያ አለው። * አፅሙ እንደሚጠቁመው ይህ ሰው ይኖር የነበረው በመጀመሪያው ወይም በሁለተኛው መቶ ዘመን ነው። ይህን አፅም በማስመልከት የቀረበው ሪፖርት “የምሥራቅ እስያ ዝርያ ያለው ሰው አፅም በጥንቷ የሮም ግዛት ሲገኝ ይህ የመጀመሪያ ጊዜ ይመስላል” ብሏል። ታዲያ ይህ ሰው ማን ሊሆን ይችላል?

ይኸው ሪፖርት “አንድ ሰው መጀመሪያ ላይ ይህን ግለሰብ ከቻይና ወደ ሮም ይደረግ ከነበረው የሐር ንግድ ጋር ለማያያዝ ይፈተን ይሆናል” ብሏል። ይሁንና ሐር ከቻይና ወደ ጣሊያን የሚደርሰው በተለያዩ አትራፊዎች እጅ አልፎ እንደሆነ ይታመናል፤ ምክንያቱም አንድ ሰው በራሱ ከቻይና እስከ ጣሊያን ያለውን 8,000 ኪሎ ሜትር መጓዝ አይችልም።

አፅሙ ከተገኘበት ቦታ ምን መገንዘብ እንችላለን? በጥንት ዘመን ቫንያሪ፣ የጉልበት ሠራተኞች ብረት የሚያቀልጡባትና ጡብ የሚያመርቱባት የንጉሠ ነገሥቱ ርስት ነበረች። በዚህ ቦታ ከሚሠሩት ሠራተኞች መካከል አብዛኞቹ ባሪያዎች ነበሩ፤ ከሩቅ ምሥራቅ የመጣውም ይህ ሰው ባሪያ እንደነበር ይታመናል። እንዲያውም የተቀበረበት ሁኔታ ባለጸጋ ሰው እንዳልነበር ይጠቁማል። ከእሱ ጋር ተቀብሮ የተገኘው አንድ ማሰሮ ብቻ ነው፤ ከዚህም በላይ የሌላ ሰው አስከሬን በእሱ ላይ ተደርቦ ተቀብሯል።

የዚህ ሰው አፅም በዚያ ቦታ ላይ መገኘቱ ትኩረታችንን የሚስበው ለምንድን ነው? በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. የክርስትና መልእክት መስፋፋቱ የተመካው የጥንት ሰዎች ከቦታ ወደ ቦታ በሚያደርጉት ጉዞ ርቀት ላይ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ በ33 ዓ.ም. የጴንጤቆስጤ በዓል ከተከበረ በኋላ ምሥራቹ ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው በነበሩ የውጪ አገር ሰዎች አማካኝነት ከጫፍ እስከ ጫፍ እንደተዳረሰ ይናገራል። (የሐዋርያት ሥራ 2:1-12, 37-41) ይህ አፅም ቢያንስ ቢያንስ በዚያ ዘመን ገደማ አንዳንድ ሰዎች ከምሥራቅ እስያ ወደ ሜድትራንያን ክልል ይጓዙ እንደነበር ይጠቁማል። *

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 በማይቶኮንዲሪያል ዲ ኤን ኤ ምርመራ በአባት ወገን ስላለው ዝርያ ምንም ዓይነት መረጃ ማግኘት አይቻልም።

^ አን.6 በምዕራብ የሚኖሩ ሰዎች ወደ ምሥራቅ እስያ ይጓዙ እንደነበር የሚጠቁሙ ማስረጃዎችም አሉ። በጥር 1, 2009 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ሚስዮናውያን በስተ ምሥራቅ የት ድረስ ተጉዘው ሊሆን ይችላል?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ሮም

ቫንያሪ

የሜድትራንያን ባሕር

ምሥራቅ እስያ

ፓስፊክ ውቅያኖስ

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጥንት ሮማውያን የመቃብር ስፍራ በቁፋሮ የተገኘ የአንድ የምሥራቅ እስያ ሰው አፅም

[የሥዕሉ ምንጭ]

© Su concessione del Ministero per i Beni e le Attività Culturali - Direzione Regionale per i Beni Culturali e Paesaggistici della Puglia - Soprintendenza per i Beni Archeologici della Puglia