ከአምላክ ቃል ተማር
ከአምላክ ቃል ተማር
ከአምላክ መማር ያለብን ለምንድን ነው?
ይህ ርዕስ በአእምሮህ ሊመላለሱ የሚችሉ ጥያቄዎች በማንሳት መልሶቹን ከመጽሐፍ ቅዱስህ ውስጥ የት ቦታ ላይ ማግኘት እንደምትችል ይጠቁምሃል። የይሖዋ ምሥክሮች በመልሶቹ ላይ ከአንተ ጋር ለመወያየት ፈቃደኞች ናቸው።
1. ከአምላክ መማር ያለብን ለምንድን ነው?
አምላክ ለሰው ዘሮች ጥቅም ስለሚያስገኝ ምሥራች ተናግሯል። ይህ ምሥራች የሚገኘው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በሰማይ ከሚኖረው አፍቃሪ አባታችን የተላከ ደብዳቤ ነው ማለት ይቻላል።—ኤርምያስ 29:11ን አንብብ።
2. ምሥራቹ ምንድን ነው?
የሰው ዘር መልካም አስተዳደር ያስፈልገዋል። የሰው ልጆችን ከዓመፅ፣ ከፍትሕ መጓደል፣ ከበሽታና ከሞት ነፃ ማውጣት የቻለ አንድም ሰብዓዊ ገዥ የለም። ይሁን እንጂ አንድ ምሥራች አለ። አምላክ ለመከራና ሥቃይ መንስኤ የሆኑ ነገሮችን በሙሉ የሚያስወግድ መልካም አስተዳደር ለሰው ልጆች ለማምጣት ዝግጅት አድርጓል።—ዳንኤል 2:44ን አንብብ።
3. ከአምላክ መማር በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
አምላክ በሌሎች ላይ መከራ የሚያመጡ ሰዎችን በቅርቡ ከምድር ገጽ ያጠፋል። እስከዚያው ድረስ ግን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ትሑት ሰዎች ፍቅር በማሳየት የተሻለ ሕይወት እንዲመሩ እያስተማረ ነው። በአሁኑ ጊዜ ሰዎች፣ በሕይወታቸው ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች መቋቋም እንዲሁም እውነተኛ ደስታ ማግኘትና አምላክን ማስደሰት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ከአምላክ ቃል እየተማሩ ነው።—ሶፎንያስ 2:3ን አንብብ።
4. የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት ማን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ በውስጡ 66 ትንንሽ መጻሕፍትን ይዟል። እነዚህን መጻሕፍት የጻፉት 40 ሰዎች ናቸው። የመጀመሪያዎቹን አምስት መጻሕፍት ከዛሬ 3,500 ዓመታት ገደማ በፊት የጻፈው ሙሴ ነው። የመጨረሻው መጽሐፍ የተዘጋጀው ደግሞ ከ1,900 የሚበልጡ ዓመታት በፊት ሲሆን የጻፈው ሐዋርያው ዮሐንስ ነው። ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የጻፉት የራሳቸውን ሳይሆን የአምላክን ሐሳብ ነው። በመሆኑም የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት አምላክ ነው።—2 ጢሞቴዎስ 3:16ን እና 2 ጴጥሮስ 1:21ን አንብብ።
መጽሐፍ ቅዱስ ወደፊት ስለሚፈጸሙት ዝርዝር ነገሮች በትክክል ስለሚነግረን ከአምላክ የተገኘ ለመሆኑ እርግጠኞች ነን። ማንም ሰው እንዲህ ማድረግ አይችልም። (ኢሳይያስ 46:9, 10) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ ባሕርያት በሚገባ ይነግረናል። እንዲሁም ሰዎች የተሻለ ሕይወት እንዲመሩ የማድረግ ኃይል አለው። እነዚህ እውነታዎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል እንደሆነ እንዲያምኑ አድርገዋቸዋል።—ኢያሱ 23:14ን እና 1 ተሰሎንቄ 2:13ን አንብብ።
5. መጽሐፍ ቅዱስን መረዳት የምትችለው እንዴት ነው?
ኢየሱስ የአምላክ ቃል አስተማሪ በመሆኑ ይታወቅ ነበር። አብዛኞቹ አድማጮቹ ከቅዱሳን መጻሕፍት ጋር ትውውቅ ቢኖራቸውም መልእክቱን በደንብ ለመረዳት እገዛ ያስፈልጋቸው ነበር። ኢየሱስ እነዚህን ሰዎች ለመርዳት የተለያዩ ጥቅሶችን በመጥቀስ “የቅዱሳን መጻሕፍትን ትርጉም” ያብራራላቸው ነበር። “ከአምላክ ቃል ተማር” የተባለው ይህ አምድም አንተን ለመርዳት ተመሳሳይ ዘዴ ይጠቀማል።—ሉቃስ 24:27, 45ን አንብብ።
የሕይወትን ዓላማ በተመለከተ ከአምላክ የመማርን ያህል ደስታ የሚያስገኝ ነገር የለም ሊባል ይችላል። ይሁንና አንዳንድ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብህ አይደሰቱ ይሆናል። ይህ ሁኔታ ጥረትህን እንድታቆም ሊያደርግህ አይገባም። የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋህ የተመካው ስለ አምላክ እውቀት በመቅሰምህ ላይ ነው።—ማቴዎስ 5:10-12ን እና ዮሐንስ 17:3ን አንብብ።
ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 2 ተመልከት።