ምሥራቹን የሚሰብኩት እነማን ናቸው?
ምሥራቹን የሚሰብኩት እነማን ናቸው?
“. . . በመላው ምድር ይሰበካል።”—ማቴዎስ 24:14
የይሖዋ ምሥክሮች ምሥራቹን በዓለም ዙሪያ እየሰበኩ ነው። ይህንንም የሚያደርጉት የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ነው። ምሥራቹን የሚሰብኩበት አንዱ መንገድ የሚከተለው ነው፦
ሰዎችን በማነጋገር። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ እንዳደረጉት ሁሉ የይሖዋ ምሥክሮችም ሰዎች ወዳሉባቸው ቦታዎች በመሄድ ምሥራቹን ይሰብካሉ። (ሉቃስ 8:1፤ 10:1) ሰዎች እነሱ ወዳሉበት እስኪመጡ ድረስ አይጠብቁም። ከሰባት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች ስለ አምላክ መንግሥት ለሰዎች በመስበኩ ሥራ ይካፈላሉ። ከቤት ወደ ቤት በመሄድ፣ በመንገድ ላይ፣ በስልክና በሌሎች መንገዶች ምሥራቹን ይሰብካሉ። ባለፈው ዓመት የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ ሥራ ላይ ከአንድ ቢሊዮን ተኩል በላይ ሰዓት አሳልፈዋል።
የይሖዋ ምሥክሮች ስለ አምላክ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ሰዎች ኢየሱስ “[ያዘዛቸውን] ሁሉ እንዲጠብቁ” ጭምር ያስተምራሉ። (ማቴዎስ 28:20) በዓለም ዙሪያ ከስምንት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎችን በቋሚነት በነፃ መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠናሉ።
የይሖዋ ምሥክሮች ምሥራቹን የሚሰብኩት በ236 አገሮች ውስጥ ነው። የተለያየ የኑሮ ደረጃ ላላቸው ሰዎች ይሰብካሉ። በገጠርም ሆነ በከተማ፣ በአማዞን ጫካም ሆነ በሳይቤሪያ ደን፣ በአፍሪካ በረሃም ሆነ በሂማሊያ ተራሮች ይሰብካሉ። ይህን የሚያደርጉት ተከፍሏቸው አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ምሥራቹን የሚሰብኩት ለአምላክና ለሰዎች ካላቸው ፍቅር የተነሳ የራሳቸውን ጊዜና ገንዘብ መሥዕዋት በማድረግ ነው። ምሥራቹን ለማዳረስ የሚጠቀሙበት ሌላው መንገድ ደግሞ የሚከተለው ነው፦
በጽሑፎች። በአሁኑ ጊዜ በ185 ቋንቋዎች የሚታተመው የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ የሚባለው ይህ መጽሔት በእያንዳንዱ እትም ከ42 ሚሊዮን በሚበልጡ ቅጂዎች ይሰራጫል። በይሖዋ ምሥክሮች የሚዘጋጀው ንቁ! የተባለው መጽሔትም መንግሥቱን የሚያስታውቅ ሲሆን እያንዳንዱ እትም በ83 ቋንቋዎች ወደ 40 ሚሊዮን በሚጠጉ ቅጂዎች ይታተማል።
መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርቶችን የሚያብራሩ መጽሐፎች፣ ብሮሹሮች፣ ትራክቶች፣ ሲዲዎች/ኤምፒ3ዎችና ዲቪዲዎች ወደ 540 ገደማ በሚሆኑ ቋንቋዎች ይዘጋጃሉ። የይሖዋ ምሥክሮች ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ብቻ ከ20 ቢሊዮን የሚበልጡ እንዲህ ዓይነት መርጃ መሣሪያዎችን አዘጋጅተው አሰራጭተዋል፤ ይህም ሲባል በምድራችን ላይ ለሚኖር ለእያንዳንዱ ግለሰብ በአማካይ ሦስት ሦስት ይደርሰዋል ማለት ነው!
ከዚህም በተጨማሪ የይሖዋ ምሥክሮች ራሳቸው ያዘጋጁትንም ሆነ በሌሎች የተዘጋጁ የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን ኃላፊነት ወስደው ያትማሉ። የይሖዋ ምሥክሮች ተርጉመው የሚያትሙትና የሚያሰራጩት የቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በአሁኑ ጊዜ በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ በ96 ቋንቋዎች ይገኛል። ይህ ትርጉም እስከ አሁን ከ166 ሚሊዮን ቅጂዎች በላይ ተሰራጭቷል። የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥቱን ምሥራች የሚያሠራጩበት ሌላው መንገድ የሚከተለው ነው፦
በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች። የይሖዋ ምሥክሮች በአካባቢያቸው ባሉ የመንግሥት አዳራሾች የሚያካሂዷቸው ሳምንታዊ ስብሰባዎች እንዲያው ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች ብቻ አይደሉም፤ ከዚህ ይልቅ እውቀት ለማስጨበጥ ታስበው የሚዘጋጁ ናቸው። በስብሰባዎቹ ላይ መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት ያደረጉ ንግግሮች ይሰጣሉ፤ እንዲሁም በመጠበቂያ ግንብ መጽሔትና በሌሎች ጽሑፎች አማካኝነት መጽሐፍ ቅዱስ ይጠናል። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ የይሖዋ ምሥክሮች የበለጠ ውጤታማ የምሥራቹ ሰባኪዎች መሆን የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ይማራሉ።
የይሖዋ ምሥክሮች፣ በዓለም ዙሪያ ባሉ ከ107,000 በሚበልጡ ጉባኤዎች ውስጥ ተመሳሳይ ጽሑፎችን ያጠናሉ፤ ይህም ለአንድነታቸው አስተዋጽኦ ያበረክታል። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ማንኛውም ሰው መገኘት ይችላል። እንዲሁም ሙዳየ ምጽዋት በፍጹም አይዞርም። እርግጥ ነው፣ የይሖዋ ምሥክሮች የተማሩትን በተግባር የማያውሉ ቢሆን ኖሮ እነዚህ ሁሉ ነገሮች መና ሆነው ይቀሩ ነበር። በመሆኑም ሰዎች ምሥራቹን እንዲቀበሉ የሚከተለውን ያደርጋሉ፦
በግለሰብ ደረጃ ምሳሌ ይሆናሉ። ክርስቲያናዊ ባሕርያትን በማሳየት ሌሎች እንዲይዟቸው በሚፈልጉበት መንገድ እነሱም ሌሎችን ለመያዝ የተቻላቸውን ጥረት ያደርጋሉ። (ማቴዎስ 7:12) ፍጹማን ባለመሆናቸው ምክንያት ስህተት የሚሠሩባቸው ጊዜያት ቢኖሩም ሰዎችን ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ ለመያዝ ልባዊ ጥረት ያደርጋሉ፤ ይህን የሚያደርጉት ለሌሎች ምሥራቹን በመስበክ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ መንገዶች ተግባራዊ እርዳታ በመስጠት ጭምር ነው።
የይሖዋ ምሥክሮች እነሱ በሚያከናውኑት የስብከት ሥራ ብቻ ዓለም ትለወጣለች ብለው አያስቡም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ አስቀድሞ እንደተናገረው፣ ይሖዋ ይህ ሥራ እንደተጠናቀቀ ሲሰማው የዚህ ሥርዓት መጨረሻ ይመጣል። ታዲያ ይህ ለምድርና በውስጧ ለሚኖሩት ሰዎች ምን ትርጉም ይኖረዋል?
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሖዋ ምሥክሮች ምሥራቹን በዓለም ዙሪያ እየሰበኩ ነው