በቅርቡ የተሻለ ጊዜ ይመጣል!
በቅርቡ የተሻለ ጊዜ ይመጣል!
“ለአፍታ እንጂ፣ ክፉ ሰው አይዘልቅም፤ . . . ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ።”—መዝሙር 37:10, 11
ከላይ የተጠቀሰው ትንቢት ቢፈጸም ደስ ይልሃል? ደስ እንደሚልህ ጥርጥር የለውም። ይህ ተስፋ በቅርቡ እንደሚፈጸም ለማመን የሚያስችሉ ጠንካራ ምክንያቶች አሉ።
የምንኖረው “በመጨረሻዎቹ ቀኖች” ውስጥ መሆኑን በግልጽ የሚጠቁሙ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን ከዚህ በፊት ባሉት ርዕሶች ላይ ተመልክተናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) አምላክ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎችን በመንፈሱ በመምራት እነዚህን ትንቢቶች እንዲናገሩ ያደረገው ተስፋ እንዲኖረን ብሎ ነው። (ሮም 15:4) ትንቢቶቹ ተፈጸሙ ማለት ዛሬ እየደረሰብን ያለው መከራ የሚያከትምበት ጊዜ ቀርቧል ማለት ነው።
የመጨረሻዎቹ ቀኖች ካበቁ በኋላ ምን ይከሰታል? የአምላክ መንግሥት ሁሉንም የሰው ዘር ይገዛል። (ማቴዎስ 6:9, 10) በዚያን ጊዜ በምድር ላይ የሚኖረውን ሁኔታ በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ተመልከት፦
● ረሃብ ጨርሶ አይኖርም። “በምድሪቱ ላይ እህል ይትረፍረፍ፤ በተራሮችም ዐናት ላይ ይወዛወዝ።”—መዝሙር 72:16
● በሽታ ይወገዳል። “‘ታምሜአለሁ’ የሚል አይኖርም።”—ኢሳይያስ 33:24
● ምድር ትታደሳለች። “ምድረ በዳውና ደረቁ ምድር ደስ ይላቸዋል፤ በረሓው ሐሤት ያደርጋል፤ ይፈካል፤ እንደ አደይም ያብባል።”—ኢሳይያስ 35:1
እነዚህ በቅርቡ ከሚፈጸሙት አጽናኝ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ውስጥ ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። የይሖዋ ምሥክሮች በቅርቡ የተሻለ ጊዜ እንደሚመጣ ይህን ያህል እርግጠኞች እንዲሆኑ ያደረጋቸው ምክንያት ምን እንደሆነ እንዲገልጹልህ ለምን አትጠይቃቸውም?