አምላክ ክፋትና መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው?
ከአምላክ ቃል ተማር
አምላክ ክፋትና መከራ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው?
ይህ ርዕሰ ትምህርት በአእምሮህ ሊመላለሱ የሚችሉ ጥያቄዎችን የሚያነሳ ሲሆን መልሶቹን ከመጽሐፍ ቅዱስህ ውስጥ የት ቦታ ላይ ማግኘት እንደምትችልም ይጠቁምሃል። የይሖዋ ምሥክሮች ለጥያቄዎቹ በተሰጡት መልሶች ላይ ከአንተ ጋር ቢወያዩ ደስ ይላቸዋል።
1. ክፋት የጀመረው እንዴት ነው?
ክፋት በምድር ላይ የጀመረው ሰይጣን የመጀመሪያውን ውሸት በተናገረበት ጊዜ ነበር። ሰይጣን ሲፈጠር ክፉ አልነበረም። መጀመሪያ ላይ ፍጹም መልአክ ነበር፤ ይሁን እንጂ “በእውነት ውስጥ ጸንቶ አልቆመም።” (ዮሐንስ 8:44) ሰይጣን ለአምላክ ብቻ የሚገባውን አምልኮ ለራሱ የማድረግ ምኞት አደረበት። በመሆኑም ሰይጣን የመጀመሪያዋ ሴት ለሆነችው ለሔዋን ውሸት በመናገር ከአምላክ ይልቅ እሱን እንድትታዘዝ አሳመናት። አዳምም በአምላክ ላይ በማመፅ ከሔዋን ጋር ተባበረ። የአዳም ውሳኔ መከራና ሞት አስከተለ።—ዘፍጥረት 3:1-6, 17-19ን አንብብ።
ሰይጣን፣ አምላክን እንዳትታዘዝ ሔዋንን ሲያግባባት በአምላክ ሉዓላዊ ገዥነት ላይ እንድታምፅ እያደረጋት ነበር። አብዛኞቹ የሰው ዘሮች የአምላክን አገዛዝ ለመቀበል አሻፈረን በማለት ከሰይጣን ጋር ተባብረዋል። በዚህም ምክንያት ሰይጣን “የዚህ ዓለም ገዥ” ሆኗል።—ዮሐንስ 14:30ን እና ራእይ 12:9ን አንብብ።
2. የአምላክ ፍጥረታት ጉድለት ነበረባቸው?
የአምላክ ፍጥረታት የሆኑት ሰዎችም ሆኑ መላእክት የእሱን መመሪያዎች ፍጹም በሆነ መንገድ መታዘዝ ይችሉ ነበር። (ዘዳግም 32:4, 5) አምላክ የፈጠረን መልካም ወይም ክፉ የሆነውን የመምረጥ ነፃነት እንዲኖረን አድርጎ ነው። ይህ ነፃነት ለአምላክ ያለንን ፍቅር እንድንገልጽ አጋጣሚ ይሰጠናል።—ያዕቆብ 1:13-15ን እና 1 ዮሐንስ 5:3ን አንብብ።
3. አምላክ መከራና ሥቃይ እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው?
ይሖዋ በእሱ ሉዓላዊነት ላይ የተነሳውን ዓመፅ ለጊዜው ታግሷል። ለምን? ያለ እሱ ድጋፍ የሰው ልጆችን ለማስተዳደር የሚደረገው ጥረት ሁሉ ምንም ፋይዳ እንደሌለው ለማሳየት ነው። (ኤርምያስ 10:23) የሰው ልጆች የ6,000 ዓመት ታሪክ ይህ ጉዳይ እውነት መሆኑን አረጋግጧል። ሰብዓዊ ገዥዎች ጦርነትን፣ ወንጀልን፣ የፍትሕ መጓደልንና በሽታን ለማስቀረት ያደረጉት ጥረት መና ሆኖ ቀርቷል።—መክብብ 7:29ን፤ 8:9ን እና ሮም 9:17ን አንብብ።
ከዚህ በተቃራኒ አምላክን እንደ ገዥያቸው አድርገው የሚቀበሉ ሰዎች ጥቅም ያገኛሉ። (ኢሳይያስ 48:17, 18) በቅርቡ ይሖዋ ሰብዓዊ መንግሥታትን በሙሉ ያጠፋል። የአምላክን አገዛዝ የመረጡ ሰዎች ብቻ በምድር ላይ ይኖራሉ።—ኢሳይያስ 2:3, 4፤ 11:9፤ ዳንኤል 2:44ን አንብብ።
4. አምላክ መታገሡ ምን አጋጣሚ ከፍቷል?
ሰይጣን ይሖዋን በታማኝነት የሚታዘዝ ማንም ሰው የለም የሚል ክስ ሰንዝሯል። አምላክ መታገሡ ከእሱ ወይም ከሰዎች አገዛዝ የትኛውን እንደምንመርጥ ለማሳየት ለእያንዳንዳችን አጋጣሚ ከፍቶልናል። የመረጥነው የትኛውን አገዛዝ እንደሆነ ደግሞ በአኗኗራችን እናሳያለን።—ኢዮብ 1:8-11ን እና ምሳሌ 27:11ን አንብብ።
5. የአምላክን አገዛዝ እንደመረጥን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በሠፈረው መሠረት እውነተኛውን አምልኮ የምንፈልግና በዚያው መንገድ የምንመላለስ ከሆነ አምላክ ገዥያችን እንዲሆን እንደመረጥን እናሳያለን። (ዮሐንስ 4:23) በተጨማሪም ልክ እንደ ኢየሱስ በፖለቲካ ውስጥ አንገባም፤ አልፎ ተርፎም በጦርነት አንካፈልም።—ዮሐንስ 17:14ን አንብብ።
ሰይጣን ኃይሉን ተጠቅሞ ሥነ ምግባር የጎደላቸውን መጥፎ ድርጊቶች ያስፋፋል። አንዳንድ ጓደኞቻችን እና ዘመዶቻችን እንደነዚህ ባሉ ድርጊቶች የማንካፈል መሆኑን ሲመለከቱ ሊያሾፉብን ወይም ሊቃወሙን ይችላሉ። (1 ጴጥሮስ 4:3, 4) በመሆኑም ሁላችንም ምርጫ ቀርቦልናል። አምላክን ከሚወዱ ሰዎች ጋር ለመተባበር ፈቃደኛ ነን? ጥበብና ፍቅር የተንጸባረቀባቸውን የአምላክ ሕጎች እንታዘዛለን? እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ሰይጣን ‘ማንም ሰው አምላክ በተናገረው መሠረት አይሄድም’ በማለት የሰነዘረው ክስ ውሸት መሆኑን እናረጋግጣለን።—1 ቆሮንቶስ 6:9, 10ን እና 15:33ን አንብብ።
ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 11 ተመልከት።
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አዳም መጥፎ ምርጫ አደረገ
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የምናደርገው ምርጫ አምላክ ገዥያችን እንዲሆን የምንፈልግ መሆን አለመሆናችንን ያሳያል