በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው መቼ ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው መቼ ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው መቼ ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ በዓይነቱ ልዩ የሆነ መጽሐፍ ነው። ከሦስት ቢሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ቅዱስ መጽሐፍ እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል። መጽሐፍ ቅዱስ (በሙሉም ሆነ በከፊል) ከ2,400 በሚበልጡ ቋንቋዎች 6,000,000,000 ገደማ በሚሆኑ ቅጂዎች እንደታተመ ይታመናል፤ በመሆኑም በታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ሽያጭ በማግኘት ረገድ ተወዳዳሪ የሌለው መጽሐፍ እንደሆነ ይነገርለታል።

መጽሐፍ ቅዱስ በታሪክ ውስጥ ሰፊ ተነባቢነት ያገኘ መጽሐፍ ቢሆንም፣ የተጻፈበትን ዘመን በተመለከተ በተለይ ደግሞ ብሉይ ኪዳን እየተባሉ የሚጠሩት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት የተጻፉበትን ጊዜ አስመልክቶ ብዙ አስተያየቶች ይሰነዘራሉ። አንተም እንደዚህ ያሉ አስተያየቶችን በመጽሔቶችና በመጻሕፍት ላይ አንብበህ ወይም ምሑራን በቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ላይ ቀርበው ማብራሪያ ሲሰጡባቸው ተመልክተህ ይሆናል። በዘመናችን የተስፋፋውን አመለካከት ጎላ አድርገው የሚገልጹ አንዳንድ ሐሳቦች ቀጥሎ ቀርበዋል።

“የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በአብዛኛው የተጻፉት ከስምንተኛው እስከ ስድስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ወይም በነቢዩ ኢሳይያስና በነቢዩ ኤርምያስ ዘመን መካከል ባለው ጊዜ ነበር።”

“ላለፉት ሁለት መቶ ዓመታት የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን የዕብራይስጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የተጻፈውና የተዘጋጀው የፋርስና የግሪክ ባሕል ተስፋፍቶ በነበረበት ዘመን (ከአምስተኛው እስከ ሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ.) እንደሆነ ያምኑ ነበር።”

“የዕብራይስጡ መጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎች በሙሉ አሁን ባሉበት ሁኔታ የተዘጋጁት የግሪካውያን ባሕል ከተስፋፋበት ዘመን (ከ2ኛው እስከ 1ኛው መቶ ዘመን [ዓ.ዓ.]) ጀምሮ ነው።”

“ቅዱስ መጽሐፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ ነው” ብሎ የሚያምን አንድ ክርስቲያን እነዚህን እርስ በርሳቸው የሚጋጩ ሐሳቦች እንዴት ሊመለከታቸው ይገባል? (2 ጢሞቴዎስ 3:16) የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት እነዚህን እርስ በርስ የሚቃረኑ ሐሳቦች እስቲ እንመርምር።

መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ የሚገልጸው የጊዜ ሰሌዳ

የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ዘመንን የሚጠቅሱ በርካታ ዘገባዎች ይዘዋል። እነዚህ ዘገባዎች የመጀመሪያዎቹ መጻሕፍት በሙሴና በኢያሱ ዘመን ማለትም ከ3,500 ዓመታት ገደማ በፊት እንደተጻፉ ያመለክታሉ። * ሳሙኤል፣ ዳዊት፣ ሰለሞንና ሌሎችም፣ ተጨማሪ ጽሑፎችን በ11ኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ጽፈዋል። ከዚህ በኋላ ደግሞ ከዘጠነኛው እስከ አምስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ድረስ በነበሩት ዘመናት ታሪካዊ ዘገባ፣ ግጥሞችና ትንቢት የያዙ መጻሕፍት ተጽፈዋል።

የአስቴርን መጽሐፍ ሳይጨምር የእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ቅጂዎች ወይም ቁርጥራጮች በሙት ባሕር ጥቅልሎች መካከል ተገኝተዋል። ካርበን 14⁠ን (ሬዲዮአክቲቭ ካርበን) እና ፔሊዮግራፊን (የጥንት ጽሑፎች ጥናት) በመጠቀም የተደረገው የዘመን ስሌት ከእነዚህ ጥቅልሎች መካከል በጣም ጥንታዊ የሚባሉት ከ200 ዓ.ዓ. እስከ 100 ዓ.ዓ. ገደማ ባለው ጊዜ ውስጥ የተጻፉ እንደሆኑ ያረጋግጣል።

ሃያሲያን ምን ይላሉ?

መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ የሚጠቅሰውን የጊዜ ሰሌዳ ለመጠራጠር እንደ ትልቅ ምክንያት ሆኖ የሚቀርበው፣ መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ እንደሆነ የሚናገር መሆኑ ነው። ፕሮፌሰር ዎልተር ካይዘር ጁኒየር ዚ ኦልድ ቴስታመንት ዶክመንትስ በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ ይህን አስመልክተው ሲጽፉ “[መጽሐፍ ቅዱስ] መለኮታዊ ምንጭ ያለው መሆኑን መግለጹ እንዲሁም ስለ ተአምራትና ስለ አምላክ መናገሩ እንደ ትልቅ ጥፋት ተቆጥሮበታል” ብለዋል። መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ መሪነት ተጽፏል ብለው የማያምኑ ምሑራን መጽሐፍ ቅዱስ እንደ ማንኛውም መጽሐፍ ሂስ ሊሰጥበት ይገባል ብለው ይከራከራሉ።

አንዳንዶች፣ ሃይማኖቶች በጊዜ ሂደት እንዴት እየተለወጡ እንደመጡ ለመግለጽ የዳርዊንን የዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ ሲጠቀሙበት ቆይተዋል። ሰዎች በመጀመሪያ ተፈጥሮን ያመልኩ እንደነበር፣ ከዚያም ብዙ አማልክትን ማምለክ እንደጀመሩና በመጨረሻም አንድ አምላክን የማምለክ ልማድ እየዳበረ እንደመጣ ይገልጻሉ። የመጀመሪያዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ስለ አንድ አምላክ አምልኮ የሚገልጹ በመሆናቸው፣ አንዳንዶች እነዚህ መጻሕፍት ተጽፈውበታል ተብሎ ከሚታመንበት ዘመን በጣም ብዙ ቆይተው የተጻፉ መሆን አለባቸው ይላሉ።

ከዚያን ጊዜ አንስቶ መጽሐፍ ቅዱስ የተለያየ ዓይነት ሂስ ሲሰጥበት ቆይቷል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ በቅርቡ የታተመ የብሉይ ኪዳን መዝገበ ቃላት በመጽሐፍ ቅዱስ አጻጻፍ፣ በዘገባዎቹ ትክክለኛነት፣ በሥነ ጽሑፋዊ ይዘቱ ወይም በአተራረኩ፣ አምስቱ የኦሪት መጻሕፍት በያዙት ታሪክ፣ በምንጩ እንዲሁም ከባሕሎችና ወጎች ጋር በተያያዘ በቀረቡት ዘገባዎች ላይ የተሰነዘሩ በርካታ ሂሶችን ይዞ ወጥቷል።

ምሑራን የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ከተጻፉበት ዘመን ጋር በተያያዘ የተለያየ አመለካከት ቢኖራቸውም ብዙዎቹ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ኤሊዮት ፍሪድማን ያቀረቡትን ጽንሰ ሐሳብ ይደግፋሉ። ፕሮፌሰሩ እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “የጥንት ጸሐፊዎች በብዙ መቶ ዓመታት በሚቆጠሩ ጊዜያት ውስጥ የግጥም፣ የስድ ንባብና የሕግ ሰነዶችን አዘጋጅተዋል። ከዚያም ሌሎች ጸሐፊዎች እነዚህን ሰነዶች ምንጭ አድርገው ተጠቀሙባቸው። በዚህ መንገድ ጸሐፊዎቹ መጽሐፍ ቅዱስን አዘጋጁ።”

ፌይዝ፣ ትራዲሽን ኤንድ ሂስትሪ የተሰኘው መጽሐፍ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተሰነዘሩትን እነዚህንና ሌሎች በርካታ ሂሶች በዝርዝር አቅርቧል። ይሁን እንጂ በማጠቃለያው ላይ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቷል፦ “ምሑራን በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ እምነት ማጣታቸውና በራሳቸው ጽንሰ ሐሳብ ከመጠን በላይ መተማመናቸው አንድ ቢያደርጋቸውም አንዳቸው የሌላውን አመለካከት ክፉኛ ይተቻሉ።”

ለመጽሐፍ ቅዱስ የጊዜ ሰሌዳ መከላከያ ማቅረብ

የመጀመሪያዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የተጻፉት በቀላሉ ሊበላሹ በሚችሉ ነገሮች ላይ ነበር። በመሆኑም በሙሴ፣ በኢያሱ፣ በሳሙኤል ወይም በዳዊት ዘመን የነበሩት የመጀመሪያዎቹ ጽሑፎች ወይም የመጀመሪያዎቹ ቅጂዎች በአሁኑ ጊዜ ይገኛሉ ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው። ይሁን እንጂ ተደማጭነት ያላቸው በርካታ ምሑራንና የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች እንደሚያደርጉት ሁሉ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ የሚገልጸውን ዘመን መቀበል ምክንያታዊ እንደሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የሚጠቁመውን ታሪካዊ ማስረጃ መመርመር ይቻላል። ታዲያ ማስረጃው ምን ያሳያል? ጥቂት ምሳሌዎችን ተመልከት።

መጽሐፍ ቅዱስ ሙሴና ኢያሱ እንደኖሩበት በሚያመለክተው ዘመን ማለትም ከ3,500 ዓመታት በፊት፣ በጥንቱ የመካከለኛው ምሥራቅ ክልል የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ይገኙ ነበር? በጥንት ዘመን በሜሶጶጣሚያና በግብፅ ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ሥነ ጽሑፋዊና ሕጋዊ ጽሑፎች ተጽፈው ነበር። ስለ ሙሴና ስለ እስራኤላውያንስ ምን ሊባል ይችላል? ዲክሽነሪ ኦቭ ዚ ኦልድ ቴስታመንት፦ ፔንታቱች የተባለው መጽሐፍ “በኋለኛው የነሐስ ዘመን [ከ1550 እስከ 1200 ዓ.ዓ.] በከነዓን የተጻፈ ሥነ ጽሑፍ ለመኖሩ ምንም ጥርጥር የለውም” በማለት መልስ ይሰጣል። አክሎም “በጥንት ዘመን ከነበረው ጽሑፎችን የማዘጋጀት ልማድ አንጻር ሙሴም ሆነ ሌሎች ጽፈዋቸዋል ከሚባሉት መጻሕፍት ውስጥ አብዛኞቹ በዚያ ዘመን ሊጻፉ የማይችሉበት ምንም ምክንያት የለም” ብሏል።​—ዘፀአት 17:14፤ 24:4፤ 34:27, 28፤ ዘኍልቁ 33:2፤ ዘዳግም 31:24

የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ጥንታዊ ምንጮችን ለማመሣከሪያነት ተጠቅመው ነበር? አዎን፣ አንዳንዶቹ ጸሐፊዎች የመንግሥት ሰነዶች ናቸው ተብለው የሚታሰቡ ‘መጻሕፍትን፣’ የዘር ሐረግ ዝርዝር የያዙ መዛግብትን፣ ታሪካዊ ጽሑፎችን እንዲሁም የነገድና የቤተሰብ ሰነዶችን ጠቅሰው ጽፈዋል።​—ዘኍልቁ 21:14፤ ኢያሱ 10:13፤ 2 ሳሙኤል 1:18፤ 1 ነገሥት 11:41፤ 2 ዜና መዋዕል 32:32

ከሙት ባሕር ጥቅልሎች በፊት የተዘጋጁ ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ሰነዶች ያልተገኙት ለምንድን ነው? ቢብሊካል አርኪኦሎጂ ሪቪው የተሰኘው መጽሔት እንደሚከተለው በማለት ይገልጻል፦ “በሙት ባሕር ዙሪያ እንዳሉት ባሉ በጣም በረሃማ ክልሎች ካልሆነ በቀር በአብዛኛው የፓለስቲና ምድር በፓፒረስና በቆዳ ላይ የተጻፉ ሰነዶች ጠፍተዋል። እነዚህ ነገሮች እርጥበት ባለው አፈር ውስጥ ተቀብረው ሲቆዩ ይበሰብሳሉ። በመሆኑም በመሬት ቁፋሮ አልተገኙም ማለት ጨርሶ አልነበሩም ማለት አይደለም።” እንዲያውም ሰነዶችን ለማሸግ ያገለግሉ የነበሩ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ የሸክላ ማኅተሞች ተገኝተዋል። በፓፒረስና በቆዳ ላይ የተጻፉት ሰነዶች በእሳት ወይም እርጥበት ባለው አፈር የተነሳ የጠፉ ቢሆንም የሸክላ ማኅተሞቹ ግን እስከ አሁን ድረስ አሉ። እነዚህ የሸክላ ማኅተሞች የተሠሩት ከዘጠነኛው እስከ አምስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. በነበረው ጊዜ ውስጥ እንደሆነ ይገመታል።

የመጽሐፍ ቅዱስ የጥንት ቅጂዎች ተጠብቀው እንዲቆዩ ይደረግ የነበረው እንዴት ነው? ዘ ባይብል አዝ ኢት ዎዝ የተሰኘው መጽሐፍ እንደሚከተለው ይላል፦ “ታሪኮችን፣ መዝሙራትን፣ ሕጎችንና ትንቢቶችን የያዙት ዛሬ በእጃችን የሚገኙት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በዚያም ዘመን እንኳ በተደጋጋሚ ሲገለበጡ የቆዩ መሆን አለባቸው። . . . እነዚያ ጽሑፎች በዚያው በተጻፉበት ዘመን ጭምር በተደጋጋሚ ይገለበጡ ከነበረ አገልግሎት ላይ ይውሉ ነበር ማለት ነው፤ ሰዎች በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ይጠቀሙባቸው ነበር። . . . ማንኛውም ሰው ያለ ምንም ዓላማ ጽሑፎቹን በመገልበጥ የሚደክምበት ምክንያት የለም።”​—ዘዳግም 17:18፤ ምሳሌ 25:1

በመሆኑም የመጀመሪያዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት እስከ አንደኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. በነበሩት 1,500 ዓመታት ጊዜ ውስጥ በተደጋጋሚ ሲገለበጡ ቆይተዋል ማለት ነው። ይህ በትክክል የመገልበጥ ሥራ “ዘመን ያለፈባቸውን የሰዋስው ሕጎችና ሥርዓተ ሆሄያት ከጊዜው ጋር እንዲስማሙ አድርጎ ማሻሻልን ይጨምር የነበረ ሲሆን በጥንት ዘመን በመካከለኛው ምሥራቅ እንዲህ ማድረግ የተለመደ ነበር” በማለት ኦን ዘ ሪላያብሊቲ ኦቭ ዚ ኦልድ ቴስታመንት የተሰኘው መጽሐፍ ይናገራል። * ይህ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ አጻጻፍና የአቀራረብ ስልት ላይ ተመሥርተው የተሰነዘሩ ሂሶችን ተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው መቼ ነው?

በሙሴ፣ በኢያሱ፣ በሳሙኤልና በሌሎችም የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ዘመን የተጻፉ ጥንታዊ ቅጂዎች ስላልተገኙ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በዚያ ዘመን አልተጻፉም ብሎ መከራከር ምክንያታዊ ነው? እነዚህ ጥንታዊ ቅጂዎች አለመገኘታቸው ጭራሽ እንዳልነበሩ የሚያሳይ ማስረጃ ተደርጎ ሊጠቀስ እንደማይችል ብዙ ምሑራን ይስማማሉ። እንደ እውነቱ ከሆነ በቀላሉ ሊበላሽ በሚችል ነገር ላይ ከተጻፈ ጽሑፍ ውስጥ እስከ አሁን ድረስ ተጠብቆ ሊቆይ የሚችለው ምን ያህሉ ነው? ለምሳሌ ያህል፣ በጥንታዊቷ ግብፅ ሥልጣኔ ላይ ጥናት ያካሄዱት ኬነዝ አንደርሰን ኪችን፣ ከግሪክና ከሮም ሥልጣኔ በፊት በፓፒረስ ላይ ተጽፈው የነበሩት ሁሉም የግብፅ ጽሑፎች ማለት ይቻላል እንደጠፉ ገምተዋል።

ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት ያላቸው ሰዎች ‘ኢየሱስ ለዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ምን አመለካከት ነበረው?’ ብለውም ይጠይቁ ይሆናል። በዚያ ወቅት የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት የተጻፉበት ዘመን አከራካሪ ጉዳይ አልነበረም። እንደ ሌሎቹ አይሁዳውያን ሁሉ ኢየሱስም በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የተጠቀሱትን ዘመንን የሚገልጹ መረጃዎች ተቀብሏቸው እንደነበረ ጥርጥር የለውም። ታዲያ ኢየሱስ የመጀመሪያዎቹን የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ጸሐፊዎች እውቅና ሰጥቷቸው ነበር?

ኢየሱስ የሙሴን መጻሕፍት ጠቅሶ ተናግሯል። ለምሳሌ ያህል፣ ‘የሙሴን መጽሐፍ’ ጠቅሷል። (ማርቆስ 12:26፤ ዮሐንስ 5:46) ኢየሱስ በዘፍጥረት (ማቴዎስ 19:4, 5፤ 24:37-39)፣ በዘፀአት (ሉቃስ 20:37)፣ በዘሌዋውያን (ማቴዎስ 8:4)፣ በዘኁልቁ (ማቴዎስ 12:5) እና በዘዳግም (ማቴዎስ 18:16) መጻሕፍት ላይ የሚገኙ ዘገባዎችን ጠቅሷል። “በሙሴ ሕግ፣ በነቢያትና በመዝሙራት ስለ እኔ የተጻፉት ነገሮች ሁሉ መፈጸም አለባቸው” ብሎ ነበር። (ሉቃስ 24:44) ኢየሱስ ሙሴንና ሌሎችንም የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች እውቅና ከሰጣቸው በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የተጠቀሱት ዘመንን የሚገልጹ መረጃዎችም ትክክለኛ ናቸው ብሎ ያምን እንደነበረ ጥርጥር የለውም።

ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው መቼ ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ የሚገልጸው የጊዜ ሰሌዳ እምነት ሊጣልበት የሚችል ነው? ብዙ ምሑራን የሰጧቸውን ሂሶች፣ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ የያዘውን መረጃ፣ በተዘዋዋሪ መንገድ የተጠቀሱ ታሪካዊ ማስረጃዎችንና የኢየሱስን አመለካከት ተመልክተናል። ከዚህ በመነሳት ለእነዚህ ጥያቄዎች የምትሰጠው መልስ ኢየሱስ ወደ አባቱ ወደ ይሖዋ አምላክ ሲጸልይ “ቃልህ እውነት ነው” በማለት ከተናገረው ሐሳብ ጋር ይስማማ ይሆን?​—ዮሐንስ 17:17

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.9 የመጽሐፍ ቅዱስን የዘመን አቆጣጠር በተመለከተ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ጥራዝ 1 ከገጽ 447-467 ተመልከት።

^ አን.23 በመጋቢት 15, 2007 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 18-20 ላይ የወጣውን “የጥንቶቹ ጸሐፍትና የአምላክ ቃል” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[ከገጽ 20-23 የሚገኝ ቻርት/​ሥዕል]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

(የጊዜ ቅደም ተከተሉ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ተጽፈው የተጠናቀቁበት ጊዜ ነው ተብሎ የሚታመንበትን ዘመን ያመለክታል)

2000 ዓ.ዓ.

1800

[ሥዕል]

ግብፃውያን ጸሐፍት ከሙሴ ዘመን በፊት የጻፏቸው ጽሑፎች ነበሩ

[የሥዕሉ ምንጭ]

© DeA Picture Library/Art Resource, NY

1600

[ሥዕል]

ሙሴ የዘፍጥረት መጽሐፍን ጽፎ ያጠናቀቀው በ1513 ዓ.ዓ. ሲሆን የጻፈበትም ነገር በቀላሉ ሊበላሽ የሚችል ነበር

ዘፍጥረት 1513 ዓ.ዓ.

ኢያሱ

1400

1200

ሳሙኤል

1000 ዓ.ዓ.

[ሥዕል]

በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ የሸክላ ማኅተሞች ተገኝተዋል

ከ900 እስከ 500 ዓ.ዓ.

ዮናስ

800

ኢሳይያስ

600

ኤርምያስ

ዳንኤል

[ሥዕል]

በገመድና በሸክላ ማኅተም የታሰረና የተጣጠፈ የፓፒረስ ሰነድ

ከ449 ዓ.ዓ. ወዲህ

[የሥዕሉ ምንጭ]

Brooklyn Museum, Bequest of Theodora Wilbour from the collection of her father, Charles Edwin Wilbour

400

200

[ሥዕል]

የሙት ባሕር ጥቅልሎች በበፍታ ተጠቅልለውና በማሰሮ ውስጥ ተቀምጠው ተገኝተዋል። እነዚህ ጥቅልሎች እስከ ዛሬ ተጠብቀው ከቆዩት የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎች ሁሉ በዕድሜ ይበልጣሉ

ከ200 እስከ 100 ዓ.ዓ.

[የሥዕሉ ምንጭ]

Shrine of the Book, Photo © The Israel Museum, Jerusalem