በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበረው ሕይወት—ሙዚቀኞችና የሙዚቃ መሣሪያዎቻቸው
በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበረው ሕይወት—ሙዚቀኞችና የሙዚቃ መሣሪያዎቻቸው
“[አምላክን] በመለከት ድምፅ አመስግኑት፤ በበገናና በመሰንቆ ወድሱት። በከበሮና በሽብሸባ አመስግኑት፤ በባለ አውታር መሣሪያና በእምቢልታ አወድሱት። ተርገብጋቢ ድምፅ ባለው ጸናጽል አመስግኑት፤ ድምፀ መልካም በሆነ ጸናጽል ወድሱት።”—መዝሙር 150:3-5
ከጥንት ዘመን ጀምሮ፣ ሙዚቃና ሙዚቀኞች ለይሖዋ አምላክ በሚቀርበው አምልኮ ውስጥ ወሳኝ ሚና ነበራቸው። ለምሳሌ ያህል፣ እስራኤላውያን ቀይ ባሕርን ተአምራዊ በሆነ መንገድ ከተሻገሩ በኋላ የሙሴ እህት ማርያምና ሌሎቹ ሴቶች የድል መዝሙር ዘምረዋል፤ እንዲሁም አታሞ እየመቱ ጨፍረዋል። ይህ ታሪክ እስራኤላውያን ለሙዚቃ ምን ያህል ትልቅ ቦታ ይሰጡ እንደነበር ይጠቁመናል። ምክንያቱም ሕዝቡ ከግብፃውያን ሸሽተው የወጡ ቢሆንም ብዙዎቹ ሴቶች የሙዚቃ መሣሪያዎቻቸውን ይዘው ነበር፤ እንዲሁም በዚህ ወቅት መሣሪያዎቻቸውን አውጥተው ለመጫወት ዝግጁ ነበሩ። (ዘፀአት 15:20) ከጊዜ በኋላ ንጉሥ ዳዊት፣ በማደሪያው ድንኳን ውስጥ በሚከናወነው የአምልኮ ሥነ ሥርዓት ላይ የሙዚቃ መሣሪያ የሚጫወቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሙዚቀኞች አዘጋጅቶ ነበር። ልጁ ሰለሞን በገነባው ቤተ መቅደስ ውስጥም ይህ ዝግጅት ቀጥሏል።—1 ዜና መዋዕል 23:5
ሙዚቀኞቹ የሚጫወቱባቸው የሙዚቃ መሣሪያዎች የሚሠሩት ከምን ነበር? እነዚህ መሣሪያዎች ምን ይመስሉ ነበር? ምን ዓይነት ድምፅ ያወጡ ነበር? የሚጠቀሙባቸውስ ምን ጊዜ ነበር?
የሙዚቃ መሣሪያዎቹ ዓይነት
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት የሙዚቃ መሣሪያዎች የሚሠሩት ውድ ከሆኑ እንጨቶች፣ ከለፋ ቆዳ፣ ከብርና ከመሳሰሉት ማዕድኖች እንዲሁም ከቀንድ ነበር። አንዳንዶቹ መሣሪያዎች በዝሆን ጥርስ ይለበጣሉ። ለመሣሪያዎቹ የሚያገለግለው አውታር የሚሠራው ከተክሎች ከሚገኝ
ቃጫ ወይም ከጅማት (የከረረ የእንስሳት አንጀት) ነበር። ጥንት ከነበሩት መሣሪያዎች መካከል አንዳቸውም በአሁኑ ጊዜ ባይገኙም ምስላቸውን ግን ማግኘት እንችላለን።በጥንት ዘመን የነበሩት የሙዚቃ መሣሪያዎች በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ሊመደቡ ይችላሉ፤ እነሱም፦ እንደ በገና (1) እና ክራር (ባለ ሦስት አውታር) (2) ያሉት የአውታር መሣሪያዎች፣ እንደ ቀንደ መለከት ወይም ሾፋር (3)፣ መለከት (4) እና ተወዳጁ ዋሽንት ወይም እምቢልታ ያሉት (5) የትንፋሽ መሣሪያዎች እንዲሁም እንደ አታሞ (6)፣ ጸናጽል (7)፣ ሲምባል (8) እና ቃጭል (9) ያሉት የምት መሣሪያዎች ናቸው። ሕዝቡ ደስ የሚል ግጥም ያላቸውን ዘፈኖች እየዘፈኑ ሲጨፍሩ ሙዚቀኞቹ በእነዚህ መሣሪያዎች አማካኝነት ያጅቧቸው ነበር። (1 ሳሙኤል 18:6, 7) ከሁሉ በላይ ደግሞ እነዚህን መሣሪያዎች፣ ሙዚቃ የመጫወትን ስጦታ ለሰጣቸው አምላክ በሚያቀርቡት አምልኮ ላይ ይጠቀሙባቸው ነበር። (1 ዜና መዋዕል 15:16) እስቲ እነዚህን የሙዚቃ መሣሪያዎች አንድ በአንድ እንመርምር።
የአውታር መሣሪያዎች በገና እና ባለ ሦስት አውታሩ ክራር በቀላሉ በእጅ ሊያዙ የሚችሉ ሲሆኑ የሚሠሩትም አውታሮችን በእንጨት ፍሬም ላይ በመወጠር ነበር። ዳዊት በጭንቀት የተዋጠውን የንጉሥ ሳኦልን መንፈስ ለማረጋጋት በገና ይደረድር ነበር። (1 ሳሙኤል 16:23) ሰለሞን ያሠራው ቤተ መቅደስ ለይሖዋ አምልኮ በተወሰነበት ወቅት የመዘምራኑ ቡድን በአውታር መሣሪያዎች ተጫውቶ ነበር፤ እነዚህ መሣሪያዎች እንደ በዓላት ባሉ አስደሳች ወቅቶችም ጥቅም ላይ ይውሉ ነበር።—2 ዜና መዋዕል 5:12፤ 9:11
ባለ ሦስት አውታሩ ክራር ቅርጹ ከበገና የተለየ ነው። ይህ መሣሪያ የሚሠራው አውታሮችን በእንጨት ሳጥን ላይ በመወጠር ነው። ሙዚቀኛው አውታሮቹን በመምታት በዚህ መሣሪያ ሲጫወት ከዘመናዊው ጊታር ጋር የሚመሳሰል ማራኪ ዜማ ይፈጥር ነበር። አውታሮቹ የሚሠሩት ከተገመደ ቃጫ ወይም ከጅማት ነው።
የትንፋሽ መሣሪያዎች እነዚህ መሣሪያዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ጊዜ ተጠቅሰዋል። እጅግ ጥንታዊ ከሆኑት የትንፋሽ መሣሪያዎች አንዱ ሾፋር በመባል የሚታወቀው አይሁዳውያን የሚጠቀሙበት ቀንደ መለከት ነው። ከተቦረቦረ የአውራ በግ ቀንድ የሚሠራው ይህ የሙዚቃ መሣሪያ ኃይለኛ ድምፅ ያወጣ ነበር። እስራኤላውያን ሾፋርን የሚጠቀሙት ሠራዊቱን ለጦርነት ለመሰብሰብ እና ብሔሩን ለተግባር ለማንቀሳቀስ ነበር።—መሳፍንት 3:27፤ 7:22
ሌላው የትንፋሽ መሣሪያ ደግሞ በብረት የሚሠራው መለከት ነው። ከሙት ባሕር ጥቅልሎች ጋር የተገኘ አንድ ሰነድ እንደሚያሳየው ሙዚቀኞች በዚህ መሣሪያ በመጠቀም የተለያዩ ድምፆችን ማውጣት ይችላሉ። ይሖዋ፣ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የሚያገለግሉ ሁለት መለከቶችን ከብር እንዲሠራ ሙሴን አዝዞት ነበር። ዘኍልቍ 10:2-7) ከጊዜ በኋላም የሰለሞን ቤተ መቅደስ ለይሖዋ አምልኮ በተወሰነበት ወቅት፣ መለከት የሚነፉ 120 ካህናት ለፕሮግራሙ ድምቀት ሰጥተውታል። (2 ዜና መዋዕል 5:12, 13) የዕደ ጥበብ ባለሙያዎች የተለያየ ርዝመት ያላቸው መለከቶችን ይሠሩ ነበር። አንዳንድ መለከቶች ከጫፍ እስከ ጫፍ ከ90 ሴንቲ ሜትር በላይ ርዝመት ነበራቸው።
(በእስራኤላውያን ዘንድ ተወዳጅ የነበረው ሌላው የትንፋሽ መሣሪያ እምቢልታ ነው። ቤተሰቦች አንድ ላይ ሲሰባሰቡም ሆነ በግብዣና በሠርግ ላይ በእምቢልታ መጫወት የተለመደ ሲሆን ይህ መሣሪያ የሚያወጣው ደስ የሚል ዜማ ዘና የሚያደርግ ነበር። (1 ነገሥት 1:40፤ ኢሳይያስ 30:29) ሙዚቀኞች የሐዘን ሥነ ሥርዓትን ለማጀብም በእምቢልታ ስለሚጠቀሙ ይህ መሣሪያ የሚያወጣውን ስሜት የሚኮረኩር ድምፅ በቀብር ቦታዎች ላይ መስማት የተለመደ ነበር (ገጽ 14ን ተመልከት)።—ማቴዎስ 9:23
የምት መሣሪያዎች እስራኤላውያን ልዩ በሆኑ አጋጣሚዎች ላይ ሲዘፍኑና ሲጨፍሩ የተለያዩ የምት መሣሪያዎችን ይጠቀማሉ። እነዚህ መሣሪያዎች የሚያወጡት ድምፅ ስሜት የሚቀሰቅስ ነው። ክብ በሆነ የእንጨት ፍሬም ላይ የለፋ ቆዳ በመወጠር የሚሠራው አታሞ በእጅ ሲመታ እንደ ከበሮ ዓይነት ድምፅ ያወጣል። ሙዚቀኛው አታሞውን በእጁ ይዞ ሲወዘውዘው አታሞው ላይ የተንጠለጠሉት ትናንሽ ቃጭሎች “ክሽ ክሽ” የሚል ድምፅ ያሰማሉ።
ሌላው የምት መሣሪያ ደግሞ ጸናጽል ይባላል። የባላ ቅርጽ ባለው ብረት ላይ የሚቅጨለጨሉ ትናንሽ ብረቶችን በማንጠልጠል የሚሠራ የሙዚቃ መሣሪያ ነው። ሙዚቀኛው የጸናጽሉን እጀታ ይዞ ሲወዘውዘው የሚያቃጭል ድምፅ ያወጣል።
ከነሐስ የተሠሩ ሲምባሎች ከዚህም ይበልጥ የጎላ ድምፅ ያሰማሉ። ሲምባሎች ሁለት ዓይነት መጠን አላቸው። ትልልቆቹን ሲምባሎች ሙዚቀኛው በሁለት እጆቹ ይዞ ሲያጋጫቸው ኃይለኛ ድምፅ ያወጣሉ። በትናንሾቹ ሲምባሎች ሲጫወት ደግሞ ሁለት ጣቶቹን ይጠቀማል። ሁለቱም ዓይነት ሲምባሎች “ክሽሽ” የሚል ድምፅ የሚያወጡ ቢሆንም የድምፁ መጠን ይለያያል።—መዝሙር 150:5 NW
ምሳሌያቸውን መከተል
በዛሬው ጊዜ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች በአምልኮ ቦታቸው የሚያደርጓቸውን ስብሰባዎች የሚጀምሩትና የሚደመድሙት በመዝሙር ነው። በትላልቅ ስብሰባዎቻቸው ላይ የሚሰሙት በኦርኬስትራ የተቀናበሩ ጣዕመ ዜማዎች ዘመናዊ የሆኑ የአውታር፣ የትንፋሽና የምት መሣሪያዎችን በመጠቀም የተቀረጹ ናቸው።
የይሖዋ ምሥክሮች፣ መዝሙር የአምልኳቸው ክፍል እንዲሆን በማድረግ የጥንቶቹን እስራኤላውያንና በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን ክርስቲያኖች ምሳሌ ይከተላሉ። (ኤፌሶን 5:19) እንደ ጥንቶቹ የአምላክ አገልጋዮች ሁሉ በዛሬው ጊዜ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችም ግጥምን ከዜማ ጋር አዋህደው ይሖዋን ማወደስ ያስደስታቸዋል።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
(ትክክለኛ መጠናቸው አይደለም)
(ጽሑፉን ተመልከት)