“የይሖዋ ፊት በደስታ እንዲያበራ” አድርጉ
131ኛው የጊልያድ ምረቃ
“የይሖዋ ፊት በደስታ እንዲያበራ” አድርጉ
መስከረም 10 ቀን 2011 በተከናወነው የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት 131ኛው ክፍል የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ የተማሪዎቹን ቤተሰቦችና ወዳጆች ጨምሮ ሌሎች ብዙ ሰዎች ተገኝተው ነበር። በሥነ ሥርዓቱ መጀመሪያ ላይ ተናጋሪዎቹም ሆኑ ተማሪዎቹ ጭንቅ ብሏቸው ነበር። ፕሮግራሙ ሲያበቃ ግን በቦታው የታደሙት 9,063 ሰዎች በሙሉ በንግግሮቹ፣ በሠርቶ ማሳያዎቹና በቃለ ምልልሶቹ ስለተደሰቱ ዘና ብለውና ፊታቸው በፈገግታ ተሞልቶ ነበር።
የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባል የሆነውና የፕሮግራሙ ሊቀ መንበር የነበረው ወንድም ስቲቨን ሌት የመክፈቻውን ንግግር አቀረበ። ወንድም ሌት፣ ይሖዋ እንደ እኛ የሰውነት ክፍሎች እንዳሉት ተደርጎ በምሳሌያዊ መንገድ በተገለጸባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይ ትኩረት ያደረገ ሲሆን ይሖዋ ምሳሌያዊ ዓይኖቹን፣ ጆሮዎቹን፣ እጆቹንና ክንዱን እንዴት እንደሚጠቀምባቸው የሚገልጹትን ጥቅሶች አብራርቷል።
ወንድም ሌት መጀመሪያ ያብራራው “በፍጹም ልባቸው የሚታመኑበትን ለማበርታት የእግዚአብሔር ዐይኖች በምድር ሁሉ ላይ ይመለከታሉ” የሚለውን በ2 ዜና መዋዕል 16:9 ላይ የሚገኘውን ጥቅስ ነው። ተማሪዎቹ ሙሉ በሙሉ ለይሖዋ ያደረ ልብ እንዲያዳብሩ ተበረታተዋል። ወንድም ሌት፣ የሰዎችን መልካም ጎን በመመልከት አምላክን መምሰል እንደሚችሉ ለተማሪዎቹ ነገራቸው። ቀጥሎም በ1 ጴጥሮስ 3:12 ላይ የሚገኘውንና የይሖዋ ጆሮዎች የጻድቃንን ምልጃ ለመስማት የተከፈቱ እንደሆኑ የሚናገረውን ጥቅስ አብራራ። ተማሪዎቹ፣ ይሖዋ ጸሎታቸውን ለመስማት ከልቡ እንደሚፈልግ በማስታወስ ወደ እሱ አዘውትረው እንዲጸልዩ ተናጋሪው አበረታቷቸዋል።
ወንድም ሌት በመቀጠል ያብራራው ይሖዋ “እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ‘አትፍራ፤ እረዳሃለሁ’ ብዬ ቀኝ እጅህን እይዛለሁ” በማለት ቃል የገባበትን በኢሳይያስ 41:13 ላይ የሚገኘውን ጥቅስ ነው። ተናጋሪው ሞቅ ባለና ከልብ በመነጨ መንገድ እንዲህ አለ፦ “ይሖዋ የተናገረውን ይህን ልብ የሚነካ ሐሳብ አስተውሉ። ይሖዋ እጁን ዘርግቶ እጃችንን ይይዛል።” ወንድም ሌት፣ ምንጊዜም ይሖዋ እንዲረዳቸው ፈቃደኛ እንዲሆኑና የእሱን እርዳታ ለመቀበል ፈጽሞ አሻፈረን እንዳይሉ ተማሪዎቹን አሳስቧቸዋል። አክሎም ተማሪዎቹ፣ ለሌሎች የእርዳታ እጃቸውን በመዘርጋት የይሖዋን ምሳሌ መከተል እንደሚችሉ ተናግሯል።
በመጨረሻም ወንድም ሌት ኢሳይያስ 40:11ን አነበበ። ከዚያም የይሖዋን ፍቅራዊ አሳቢነት የሚጠቁመውን በዚህ ጥቅስ ላይ የተገለጸውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናቸው እንዲስሉ አድማጮቹን ጋበዛቸው። ወንድም ሌት፣ “ይሖዋ በክንዱ ይሰበስበናል፤ በዕቅፉም ይይዘናል” በማለት ተናገረ። ታዲያ እኛ ምን ምላሽ መስጠት ይኖርብናል? ተማሪዎቹ፣ ልክ እንደ አንድ ጠቦት ለስላሳና ገር በመሆን ይሖዋ በእቅፉ ሊይዛቸው የሚፈልግ ዓይነት ሰዎች እንዲሆኑ ተመክረዋል።
“ይህ ውድ ሀብት በሸክላ ዕቃ ውስጥ አለን”
የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ዴቪድ ስፕሌን ከላይ ባለው ጥቅስ ላይ የተመሠረተ ንግግር አቀረበ። (2 ቆሮንቶስ 4:7) ውድ ሀብት የተባለው ምንድን ነው? እውቀት ወይም ጥበብ ነው? “አይደለም” በማለት ተናጋሪው መልሷል። ከዚያም “ሐዋርያው ጳውሎስ የጠቀሰው ውድ ሀብት ‘እውነትን በመግለጥ’ የምናከናውነው ‘አገልግሎት’” መሆኑን ገለጸ። (2 ቆሮንቶስ 4:1, 2, 5) ተማሪዎቹ ለአምስት ወራት ያገኙት ሥልጠና በአገልግሎቱ ለሚሰጣቸው ልዩ ተልዕኮ የሚያዘጋጃቸው እንደነበረ ወንድም ስፕሌን አስታውሷቸዋል። ይህን ኃላፊነታቸውን ከፍ አድርገው ሊመለከቱት ይገባል።
ወንድም ስፕሌን ‘የሸክላው ዕቃ’ የሚያመለክተው ደካማ የሆነውን ሥጋችንን እንደሆነ ያብራራ ሲሆን ከሸክላ የተሠራን ዕቃ ከወርቅ ከተሠራ ዕቃ ጋር አወዳድሯል። ከወርቅ የተሠሩ ዕቃዎች አገልግሎት ላይ የሚውሉት አልፎ አልፎ ነው። በሌላ በኩል ግን የሸክላ ዕቃዎች ሁልጊዜ አገልግሎት ላይ ይውላሉ። አንድን ውድ ነገር በወርቅ ዕቃ ውስጥ ካስቀመጥን በውስጡ የተቀመጠውን ውድ ሀብት ያህል ለወርቁ ዕቃም ትኩረት መስጠታችን አይቀርም። ወንድም ስፕሌን “እናንተም የሰዎችን ትኩረት ወደ ራሳችሁ መሳብ እንደማትፈልጉ ግልጽ ነው” ብሏል። አክሎም እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “ሚስዮናውያን እንደመሆናችሁ መጠን ሰዎች
በይሖዋ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ትፈልጋላችሁ። እናንተ ቦታችሁን የምታውቁ የሸክላ ዕቃዎች ናችሁ።”ወንድም ስፕሌን ንጽጽሩን በመቀጠል በጥንት ዘመን የነበሩ አንዳንድ የሸክላ ዕቃዎች እሳትን መቋቋም እንዲችሉ ተደርገው እንደሚሠሩ ገልጿል፤ ሌሎች የሸክላ ዕቃዎች ደግሞ እንዳይሸራረፉ ለማድረግ ማጠንከሪያ ይቀቡ ነበር። ሊያጎላ የፈለገው ነጥብ ምንድን ነው? ሚስዮናውያኑ በተመደቡበት ቦታ በሚያገለግሉባቸው የመጀመሪያ ወራት የሚያጋጥሟቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎች ጽናትን እንዲያዳብሩ ስለሚረዷቸው ማጠንከሪያ እንደተቀባ ሸክላ ይሆናሉ። በመሆኑም ሚስዮናውያኑ ትችትና ተቃውሞ ሲያጋጥማቸው ቶሎ ቅር አይሰኙም። ወንድም ስፕሌን፣ “ከምታስቡት በላይ ጠንካሮች እንደሆናችሁ ይገባችኋል” ብሏቸዋል። ይሖዋ፣ ውድ ሀብት የሆነውን ይህንን አገልግሎት በአደራ የሰጠው ለመላእክት ሳይሆን በሸክላ ዕቃ ለተመሰሉት የሰው ልጆች ነው። “ይህም ይሖዋ በእናንተ እንደሚተማመን ያሳያል” በማለት ወንድም ስፕሌን ንግግሩን ደምድሟል።
“ከእግረኞች ጋር ሮጣችኋል፤ ከፈረሰኞች ጋርስ ልትወዳደሩ ትችላላችሁ?”
የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ሳሙኤል ኸርድ “ምን ያህል ርቀት መሮጥ ትችላላችሁ? ፍጥነታችሁስ ምን ያህል ነው?” በማለት ተማሪዎቹን ጠየቃቸው። እነዚህን ጥያቄዎች ያነሳው ለምንድን ነው? ተናጋሪው፣ ተማሪዎቹ ያጋጠሟቸውን እና ነቢዩ ኤርምያስ ያሳለፋቸውን ሁኔታዎች አነጻጸረ። ይህ ታማኝ ነቢይ የተጋረጡበትን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመወጣት ተቸግሮ ነበር። ይሁንና ከፊት ለፊቱ የበለጠ ከባድ የሆኑ ፈተናዎች ይጠብቁት ነበር። በመሆኑም ይሖዋ “ከእግረኞች ጋር ሮጠህ፣ እነርሱ ካደከሙህ፣ ከፈረሰኞች ጋር እንዴት ልትወዳደር ትችላለህ?” በማለት ጠይቆታል።—ኤርምያስ 12:5
ወንድም ኸርድ ይህ ነጥብ ከተማሪዎቹ ጋር በተያያዘ እንዴት እንደሚሠራ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “በትምህርት ቤቱ የነበሩት የጽሑፍ ፈተናዎች ከፈረሰኞች ጋር እየሮጣችሁ እንዳለ ሆኖ እንዲሰማችሁ አድርገዋችሁ ሊሆን ይችላል። ይሁንና እስካሁን የሮጣችሁት ከፈረሰኞች ሳይሆን ከእግረኞች ጋር ነበር። በአገልግሎት ምድባችሁ ላይ ግን ከፈረሰኞች ጋር ትወዳደራላችሁ፤ በሌላ አባባል አሁን ከምታስቡት የበለጠ ተፈታታኝ የሆኑ ሁኔታዎች ያጋጥሟችኋል። ታዲያ በዚህ ጊዜ ምን ታደርጉ ይሆን? በጊልያድ ያገኛችሁት ሥልጠና ከፈረሰኞች ጋር ብትሮጡም እንዳትታክቱ አዘጋጅቷችኋል።” ወንድም ኸርድ፣ ተማሪዎቹ ራሳቸውን በመንፈሳዊ ማሠልጠናቸውን እንዲቀጥሉ እንዲሁም ቋሚ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና የጸሎት ልማድ እንዲያዳብሩ አበረታቷቸዋል።
በመቀጠልም ወንድም ኸርድ፣ አንዳንዶቹ ተማሪዎች ሚስዮናውያን ሆነው ከተላኩ በኋላ የተስፋ መቁረጥ ስሜት እንደሚሰማቸው ወይም የሰዎች ግድ የለሽነት ተጽዕኖ እንደሚያሳድርባቸው ተናግሯል። ሌሎች ደግሞ በበሽታ ወይም ብቃት የለኝም በሚል ስሜት እንደሚደቆሱ ገልጿል። ሆኖም ተማሪዎቹ ማንኛውንም ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታ ሳይታክቱ ለመወጣት የሚያስችላቸው የብርታት ምንጭ እንዳላቸው አስረግጦ ተናግሯል። ከዚያም ወንድም ኸርድ እንዲህ አላቸው፦ “የምትሮጡት ከእግረኞችም ሆነ ከፈረሰኞች ጋር የአምላክ ኃያል ክንድ ውድድሩን በድል እንድታጠናቅቁ እንደሚረዳችሁ እምነት ይኑራችሁ። በዚህ መንገድ ለይሖዋ ክብርና ውዳሴ የምታመጡ ውጤታማ ሚስዮናውያን ትሆናላችሁ።”
ሌሎች የፕሮግራሙ ጎላ ያሉ ገጽታዎች
“ጥቂት ሳይሆን ብዙ ማድጋ ተዋሺ።” የዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ጆን ኤክረን ስለ ነቢዩ ኤልሳዕ እንዲሁም ልጆቿ ለባርነት ሊሸጡባት ስለነበረች አንዲት መበለት የሚናገረውን ዘገባ አብራራ። (2 ነገሥት 4:1-7) መበለቲቱ የነበራት አንድ አነስተኛ የዘይት ማድጋ ብቻ ነበር። ኤልሳዕ ከጎረቤቶቿ ሌሎች ማድጋዎችን እንድትዋስ ከነገራት በኋላ “ጥቂት ሳይሆን ብዙ ማድጋ ተዋሺ” አላት። ይሖዋ በኤልሳዕ አማካኝነት፣ መበለቲቱ የሰበሰበቻቸው ማድጋዎች በሙሉ በተአምራዊ መንገድ በዘይት እንዲሞሉ አደረገ። መበለቲቱ ዘይቱን በመሸጥ ያገኘችው ገቢ ዕዳዎቿን ከመክፈልም ባሻገር ለተወሰነ ጊዜ ቤተሰቧን ለማስተዳደር አስቻላት።
ተመራቂዎቹ ከዚህ ዘገባ ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ? መበለቲቱ ማድጋዎቹን ስትዋስ፣ ያገኘችውን ሁሉ ትሰበስባለች እንጂ እንደማትመርጥ የታወቀ ነው። ተናጋሪው “ዘይት ሊይዝ የሚችለውን ማንኛውንም ዕቃ ሰብስባ ማምጣቷ አይቀርም፤ ዕቃው ትልቅ ቢሆን ደግሞ የተሻለ ነው” ብሏል። ከዚያም ወንድም ኤክረን፣ ተማሪዎቹ ትንሽ ትልቅ ሳይሉ የተሰጣቸውን ማንኛውንም ዓይነት ምድብ ለመቀበል ፈቃደኞች እንዲሆኑ አበረታታቸው። “መራጮች አትሁኑ” አላቸው። በተጨማሪም መበለቲቱ ለኤልሳዕ መመሪያ ትኩረት መስጠቷ ካገኘችው በረከት ጋር በቀጥታ ተያያዥነት እንደነበረው ተማሪዎቹን አስታወሳቸው። ነጥቡ? የምናገኘው በረከት መጠን ከምናሳየው ቅንዓትና እምነት ጋር ቀጥተኛ ተያያዥነት አለው። ወንድም ኤክረን “ራሳችሁን አትቆጥቡ” ብሏል።
ዘኍልቍ 14:9 ላይ የተመሠረተውን ይህን ንግግር አቀረበ። ወንድም ሳሙኤልሰን፣ ኢያሱና ካሌብ የተዉትን ግሩም ምሳሌ ጎላ አድርጎ ገልጿል። “እንጀራ” የሚለው ቃል በዚህ አገባቡ የከነዓን ነዋሪዎች በቀላሉ እንደሚሸነፉና ይህ ሁኔታ እስራኤላውያንን እንደሚያበረታቸው ብሎም እንደሚያጠነክራቸው ይጠቁማል። ተመራቂዎቹ ከዚህ ምን ትምህርት ያገኛሉ? ተናጋሪው “ወደፊት መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎቻችሁን ስታከናውኑ የሚያጋጥሟችሁን ተፈታታኝ ሁኔታዎች፣ ብርታትና ጥንካሬ እንደሚሰጧችሁ አጋጣሚዎች አድርጋችሁ ተመልከቷቸው” አለ።
“እንደ እንጀራ እንጐርሳቸዋለን።” ቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶችን የሚከታተለው ክፍል የበላይ ተመልካች የሆነው ወንድም ዊልያም ሳሙኤልሰን በ“የእምነታቸው መርከብ ወደፊት የሚመጣውን ማዕበል ጸንቶ ለማለፍ የሚያስችል መልሕቅ አለው?” ከጊልያድ አስተማሪዎች አንዱ የሆነው ወንድም ሳም ሮበርሰን፣ ሐዋርያው ጳውሎስ አንዳንዶች “ባሕር ላይ አደጋ ደርሶበት እንደተሰባበረ መርከብ እምነታቸው ጠፍቷል” በማለት የሰጠውን ማስጠንቀቂያ አብራርቷል። (1 ጢሞቴዎስ 1:19) ጠንካራ መልሕቅ አንድን መርከብ እንዳይነቃነቅ አድርጎ እንደሚይዘው ሁሉ ሰዎችም ለመጽናት የሚያስችላቸውን ጠንካራ እምነት በይሖዋ አምላክ ላይ እንዲያዳብሩ እንዲረዷቸው ተማሪዎቹን አበረታቷቸዋል። ወንድም ሮበርሰን “ሥራችሁ ከአንጥረኛ ሥራ ጋር ይመሳሰላል” አለ። እንዴት? አንድ አንጥረኛ የብረት ቀለበቶችን አንድ ላይ አገናኝቶ በመበየድ መልሕቁን የሚይዘውን ጠንካራ ሰንሰለት ይሠራል፤ የዚህ ዓይነት መልሕቅ መርከቡን እንዳይነቃነቅ አድርጎ ያቆመዋል። በተመሳሳይም ሚስዮናውያኑ፣ ለመዳን የሚያበቁ መንፈሳዊ ባሕርያት እንዲያዳብሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻቸውን ይረዷቸዋል።
ተናጋሪው የሰንሰለቱን ቀለበቶች በ2 ጴጥሮስ 1:5-8 ላይ ከተጠቀሱት ስምንት ባሕርያት ጋር አመሳስሏቸዋል። ወንድም ሮበርሰን እንደተናገረው ሚስዮናውያኑ፣ ይሖዋ እነዚህን ባሕርያት እንዴት እንደሚያንጸባርቅ ለመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻቸው ካስገነዘቧቸው ጥናቶቻቸው ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ሊመሠርቱ ይችላሉ። እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ማንኛውንም እንደ ማዕበል ያለ የእምነት ፈተና መቋቋም ይችላሉ።
ተሞክሮዎችና ቃለ ምልልሶች
የጊልያድ አስተማሪ የሆነው ማይክል በርኔት፣ ተማሪዎቹ በቅርቡ በአገልግሎት ላይ ያጋጠሟቸውን ተሞክሮዎች እንዲናገሩና በሠርቶ ማሳያ መልክ እንዲያቀርቡ ጋበዛቸው። ተማሪዎቹ በገበያ ማዕከል፣ በአውሮፕላን ማረፊያና ከቤት ወደ ቤት እንዴት እንደሰበኩ እንዲሁም የተሳሳተ ቁጥር ለደወለ ሰው በስልክ እንዴት እንደመሠከሩ ተሞክሯቸውን ሲናገሩ መስማት የሚያስደስት ነበር።
ቀጥሎም የዩናይትድ ስቴትስ ቤቴል ቤተሰብ አባል የሆነው ወንድም ማይክል ሃንሰን፣ በሚስዮናዊነት ረጅም ዓመታት ካገለገሉ ሦስት ወንድሞች ጋር ቃለ ምልልስ አደረገ፤ እነሱም በፓናማ የሚያገለግለው ወንድም ስቲቨን መክዳውል፣ በኬንያ ያገለግል የነበረው ወንድም ማርክ ኑሜር እንዲሁም በፓራጓይ ያገለግል የነበረው ወንድም ዊልያም ያሶቭስኪ ናቸው። የተናገሩት ነገር “የይሖዋን ፈቃድ በማድረግ መደሰት” የሚለውን የዚህን ንግግር ጭብጥ የሚያጎላ ነበር። (መዝሙር 40:8) ለምሳሌ ወንድም ማርክ ኑሜር፣ እሱና ባለቤቱ በተመደቡበት ቦታ ሲያገለግሉ ያስደሰቷቸውን አንዳንድ ነገሮች ጠቅሷል። በተመደቡበት ቦታ ካሉት ወንድሞች ጋር የመሠረቱት ወዳጅነት እነዚህን ባልና ሚስት በጣም አስደስቷቸዋል። ወንድሞች የተሰጣቸውን መመሪያ ሲከተሉና በሕይወታቸው ትልቅ ለውጥ ሲያደርጉ መመልከት እንዲሁም ይሖዋ ጥረታቸውን እንዴት እንደባረከላቸው ማየትም በጣም እንዳስደሰታቸው ገልጿል። ወንድም ኑሜር፣ ተማሪዎቹ ወደፊት ከፍተኛ ደስታ የሚያስገኝ ሁኔታ እንደሚጠብቃቸው አረጋገጠላቸው።
የ131ኛው ክፍል አባል የሆነ አንድ ወንድም የተማሪዎቹን አድናቆት ግሩም አድርጎ የሚገልጽ ደብዳቤ ካነበበ በኋላ ወንድም ስቲቨን ሌት፣ ተመራቂዎቹን በጥበብ እንዲመላለሱ በማበረታታት ፕሮግራሙን ደመደመ። ተመራቂዎቹ በጥበብ የሚመላለሱ ከሆነ “የይሖዋ ፊት በደስታ እንዲያበራ” ማድረግ እንደሚችሉ ገልጿል። እነዚህ ሚስዮናውያን በተመደቡበት ቦታ በታማኝነት ሲያገለግሉ የይሖዋ ፊት በደስታ እንዲያበራ ማድረግ ይችላሉ።—ኢሳይያስ 65:19
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ/ካርታ]
ተማሪዎቹን የሚመለከት አኃዛዊ መረጃ
10 የተውጣጡባቸው አገሮች
34.7 አማካይ ዕድሜ
19.0 ከተጠመቁ በኋላ ያሳለፉት ዓመታት በአማካይ
13.5 በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ
[ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ተመራቂዎቹ በካርታው ላይ ወደሚታዩት አገሮች ተመድበዋል
ሚስዮናውያን የተመደቡባቸው አገሮች
ቤኒን
ብራዚል
ቡልጋሪያ
ቡሩንዲ
ካሜሩን
ካናዳ
መካከለኛው አፍሪካ ሪፑብሊክ
ጀርመን
ጋና
ሆንግ ኮንግ
ኢንዶኔዥያ
ኬንያ
ላይቤሪያ
ሊቱዌኒያ
ማሌዥያ
ሞዛምቢክ
ኔፓል
ፓናማ
ፓራጓይ
ሴራ ሊዮን
ስሎቫኪያ
ደቡብ አፍሪካ
ዩናይትድ ስቴትስ ኦቭ አሜሪካ
ቬኔዙዌላ
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የጊልያድ ተማሪዎች ካገኟቸው ተሞክሮዎች መካከል አንዱን በሠርቶ ማሳያ ሲያቀርቡ
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የ131ኛው ክፍል ተመራቂዎች
ከዚህ በታች ባለው ዝርዝር ለእያንዳንዱ ረድፍ ቁጥር የተሰጠው ከፊት ወደኋላ ሲሆን ስሞቹ የሰፈሩት ከግራ ወደ ቀኝ ነው።
(1) ክሪስቶፍ ሌሽ፣ ናዲን ሌሽ፣ ፓትሪክ ሻካርጂን፣ ቴራ ሻካርጂን፣ ራሞን በደን፣ ካሊ በደን፣ ታሚ ናሽ፣ ሊ ናሽ
(2) ኤንሪኮ ትራንብሌ፣ ካሮላይን ትራንብሌ፣ ዶርካስ ጋርቪ፣ ጋርፊልድ ጋርቪ፣ ሩት ጎንት፣ ፒተር ጎንት፣ ጄስሚን ላው፣ ጆን ላው
(3) ሾን ዴቪስ፣ ሳብሪና ዴቪስ፣ ጆሹዋ ሳርጀንት፣ ጄሲካ ሳርጀንት፣ ቻርልስ ፎንሴካ፣ ስቴፋኒ ፎንሴካ፣ ኤስተር ቴናር፣ አርማንድ ቴናር
(4) አንቶኒ ፔትራዮተን፣ ሬቸል ፔትራዮተን፣ ናጊሳ ሬይስ፣ ኔፍታሊ ሬይስ፣ ቢርጊት አይዚሚንገር፣ ሾን አይዚሚንገር፣ ጆይ ሃከር፣ ቻርልስ ሃከር
(5) ኤሪክ ሃርትማን፣ ትሬዝ ሃርትማን፣ ዌድ ጉልያ፣ ክሪስተን ጉልያ፣ ጄሰን ቶማስ፣ ኤሪን ቶማስ፣ ናሆኮ ኦካዛኪ፣ ማሳ ኦካዛኪ
(6) ከርተስ ሚልዝ፣ አምበር ሚልዝ፣ ሉሲ ቤኒንግ፣ ትሬሲ ቤኒንግ፣ ሣራ ሶቢስኪ፣ ቶማስ ሶቢስኪ፣ ሊንዳ ጋንዮን፣ ዩጂን ጋንዮን
(7) ብራይስ ሃንሰን፣ ማርያ ሃንሰን፣ አድሪአን ፌሂ፣ መሼል ፌሂ፣ የስፐር ዴልጎር፣ ዬን ዴልጎር፣ ማሊን አንደርሰን፣ ሮበርት አንደርሰን