በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበረው ሕይወት​—ገበሬው

በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበረው ሕይወት​—ገበሬው

በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበረው ሕይወት​—ገበሬው

“[ኢየሱስ] ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ አላቸው፦ ‘በእርግጥ አዝመራው ብዙ ነው፤ ሠራተኞቹ ግን ጥቂት ናቸው። ስለዚህ የመከሩ ሥራ ጌታ ወደ መከር ሥራው ሠራተኞች እንዲልክ ለምኑት።’”​—ማቴዎስ 9:37, 38

ኢየሱስ ወሳኝ የሆኑ ትምህርቶችን ለማስረዳት ብዙውን ጊዜ የግብርና ዘዴዎችንና መሣሪያዎችን እንደ ምሳሌ አድርጎ ይጠቀም ነበር። (ማቴዎስ 11:28-30፤ ማርቆስ 4:3-9፤ ሉቃስ 13:6-9) እንዲህ ያደረገው ለምንድን ነው? የሚኖረው በግብርና በሚተዳደር ማኅበረሰብ ውስጥ ስለሆነ ነው። ከአድማጮቹ መካከል ብዙዎቹ የሚጠቀሙባቸው የግብርና ዘዴዎች ለብዙ መቶ ዘመናት ሲሠራባቸው የኖሩ ናቸው። ኢየሱስ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቻቸውን ጠቅሶ ያስተምራቸው ስለነበር አድማጮቹ ትምህርቶቹን ለመረዳት አልከበዳቸውም። ኢየሱስ የማኅበረሰቡን አኗኗር በደንብ ስለሚያውቅ ልባቸውን በሚነካ መንገድ ማስተማር ችሏል።​—ማቴዎስ 7:28

በመጀመሪያው መቶ ዘመን ስለነበረው ገበሬ ሕይወት ማለትም ስለሚያመርታቸው ሰብሎች፣ ስለሚጠቀምባቸው መሣሪያዎችና ስለሚያጋጥሙት ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያለንን ግንዛቤ ማስፋታችን ኢየሱስ የተጠቀመባቸውን ምሳሌዎችና ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን ይበልጥ ለመረዳት ያስችለናል።

ገበሬው ሥራውን ሲያከናውን በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር። ጥቅሶቹን አውጥተህ ካነበብክ በኋላ ምን ትምህርት እንደምታገኝ ቆም ብለህ አስብ።

የዘር ወቅት

ከጎሬዋ የምትወጣው ጀምበር ብርሃን ዓይን ይወጋል፤ ገበሬው ደጃፉ ላይ ቆሞ የማለዳውን አየር ሳብ ሲያደርገው ዝናብ እንደጣለ ታወቀው። ሐሩሩ ያደረቀውን መሬት ዝናብ አረስርሶታል። ገበሬው ሲጠብቀው የቆየው መሬቱን የሚያርስበት ጊዜ ደርሷል። ስለዚህ እርፍና ሞፈሩን ተሸክሞ ወደ ማሳው ይገሰግሳል።

ገበሬው ማሳው ጋ ሲደርስ በሬዎቹን ከጠመደ በኋላ በሬዎቹን በመውጊያው ጠቅ እያደረገ ማረሱን ተያያዘው። ማረሻው ጫፍ ላይ ያለው ሹል ብረት ድንጋያማውን መሬት እየፈነቃቀለ ያልፋል። ማረሻው መሬቱን ከላይ ከላይ ከመቆፈር አልፎ ወደ ውስጥ ጠልቆ በመግባት አፈሩን መገልበጥ ባይችልም ጥልቀት የሌለው ቦይ ወይም ትልም (1) ያወጣል። ገበሬው ወደ ግራም ሆነ ወደ ቀኝ ሳያማትር ፊት ፊቱን እያየ ፈሩን ጠብቆ ለማረስ ይታገላል፤ ወደኋላ እየዞረ የሚመለከት ከሆነ ማረሻው ትልሙን ስቶ እንደሚወጣ ያውቃል። (ሉቃስ 9:62) የድንበር ምልክቱን እንዳያልፍ እየተጠነቀቀ አነስተኛ የሆነችውን መሬቱን ምንም ሳያስቀር ያርሳል።

ገበሬው መሬቱን በዚህ መንገድ አርሶ ትልም ካወጣ በኋላ ዘር ለመዝራት ይዘጋጃል። ገብስ የያዘውን ከረጢት አንግቶ የገብሱን ዘር እየዘገነ ግራና ቀኝ ማሳው ላይ ይበትናል (2)። ዘሩ፣ ማሳውን አቋርጠው በሚያልፉት እግር የሚበዛባቸው መንገዶች ላይ እንዳያርፍ እየተጠነቀቀ “ጥሩ አፈር ላይ” ለመዝራት ይጥራል።​—ሉቃስ 8:5, 8

ዘሩ ከተዘራ በኋላ ቀጣዩ ሥራ ጓሉን መከስከስ ነው። ከዚያም ገበሬው፣ በሬዎቹ እሾህ ያላቸው የዛፍ ዝንጣፊዎችን በማሳው ላይ እየጎተቱ እንዲሄዱ ያደርጋል። በማሳው ላይ የተዘራውን ዘር በዚህ መንገድ አፈር ካላለበሰው ወፎቹ ይለቅሙበታል። ቆየት ብሎም ገበሬው፣ መሬቱን ለማለስለስና ቡቃያውን አንቆ እንዳያፈራ የሚያደርገውን አረም በሙሉ ነቅሎ ለማውጣት በገሶ (3) ይጠቀማል።​—ማቴዎስ 13:7

የመከር ወቅት

ቀን ቀንን እየተካ ወራት ያልፋሉ። ዝናብም ይጥላል። ከዚያም የገብሱ አዝመራ ይጎመራል፤ የፀሐይ ብርሃን በሚዘናፈለው የገብስ ዛላ ላይ ሲያርፍ ማሳው ነጭ ሆኖ መታየት ይጀምራል።​—ዮሐንስ 4:35

የመከር ወቅት ለገበሬውም ሆነ ለቤተሰቦቹ ሥራ የሚበዛበት ጊዜ ነው። አጫጁ በመደዳ ያለውን የገብስ ሰብል በግራ እጁ ሰብሰብ ያደርግና በቀኝ እጁ ማጭዱን እየሰደደ ያጭዳል (4)። ሌሎቹ ደግሞ የታጨደውን ገብስ በመሰብሰብ በየነዶ (5) እያሰሩ በአህያ ወይም በጋሪ (6) ጭነው በመንደራቸው ወዳለው አውድማ ይወስዱታል።

ፀሐይዋ አናት ላይ ስትሆን ቤተሰቡ በበለስ ዛፍ ሥር አረፍ ይላሉ። ከዚያም ለምሳቸው ያዘጋጁትን ዳቦ፣ የተጠበሰ እሸት፣ የወይራ ፍሬ፣ የደረቀ በለስና ዘቢብ እርስ በርስ እየተጨዋወቱና እየተሳሳቁ ይመገባሉ። ምሳቸውን ጎረስ ጎረስ ካደረጉ በኋላ ከምንጭ የቀዱትን ውኃ ይጎነጫሉ፤ በዚህ መንገድ ኃይላቸውን አድሰው ወደ ሥራቸው ይመለሳሉ።​—ዘዳግም 8:7

አንዳንዶች በአቅራቢያው ባለ ማሳ ላይ በእርሻው ላይ የቀረውን ሰብል ሲቃርሙ ይታያል (7)። ከእነዚህ ሰዎች አንዳንዶቹ የራሳቸው መሬት የሌላቸው ድሆች ናቸው።​—ዘዳግም 24:19-21

ሰብሉ ወደ መንደሩ ከተወሰደ በኋላ ገበሬው ከፍ ባለ ቦታ አፈሩ በደንብ ተጠቅጥቆ በተዘጋጀ አውድማ ላይ ነዶዎቹን ይነሰንሳቸዋል። ከዚያም በአውድማው ላይ የተዘረጋውን ሰብል ለማበራየት በሬዎች ከባድ ማሄጃ (8) እየጎተቱ እንዲዞሩ ያደርጋል። (ዘዳግም 25:4) የማሄጃው እንጨት ከሥሩ ሹል ድንጋዮችና የብረት ቁርጥራጮች የሚሰኩበት ሲሆን በሬዎቹ በሰብሉ ላይ ሲጎትቱት ብርኡን ይሰባብረዋል።

ከዚያም ገበሬው አመሻሹ ላይ የሚኖረውን ነፋሻማ አየር ይጠብቃል። (ሩት 3:2) ቀኑ ደንገዝገዝ ሲል ገበሬው የተወቃውን እህል በመንሽ እና ‘በላይዳ’ (9) እየዛቀ አየር ላይ ይበትነዋል። (ማቴዎስ 3:12) እህሉ ክብደት ስላለው ወደ መሬት ሲወድቅ እብቁን ግን ነፋስ ይወስደዋል። ገበሬው የተወቃውን እህል ሙሉ በሙሉ ከገለባው እስኪለይ ድረስ እየደጋገመ ያዘራዋል።

ጎህ ሲቀድ የገበሬው ሚስትና ሴት ልጆቹ በዘርዛራ ወንፊት ማንገዋለል (10) ይጀምራሉ። እህሉን በወንፊት እየሞሉ ይነፉታል። ገብሱ ወደ ቅርጫቶቹ ሲገባ ወንፊቱ ላይ የቀረው ግርድ ደግሞ ይጣላል። በዚህ ዓመት ብዙ ምርት አግኝተዋል። ሠራተኞቹ የተወሰነውን እህል ጎታ (የእህል ማስቀመጫ) (11) ውስጥ ይከትቱታል። የተቀረው እህል ደግሞ ጎተራ ውስጥ ይከማቻል።

ገበሬው በአውድማው ላይ ቆሞ እየተንጠራራ የዛለውን ሰውነቱን ካፍታታ በኋላ በመንደሩ ዙሪያ ያሉትን ማሳዎች አሻግሮ ቃኘ። በቆረን (ሰብሉ ከታጨደ በኋላ በሚቀረው አገዳ) የተሸፈኑትን ማሳዎች ሲመለከት ለረጅም ጊዜ በትጋት መልፋቱ እንደካሰው በማሰብ የእርካታ ስሜት ተሰማው። ሌሎች ገበሬዎች የወይን ተክሎቻቸውን እንዲሁም የወይራ፣ የሮማንና የበለስ ዛፎቻቸውን ሲንከባከቡ ተመለከተ። ፊቱን መለስ ሲያደርግ ደግሞ በጓሮው ሆኖ የአትክልት ቦታውን የሚኮተኩተው ጎረቤቱ እጁን በማወዛወዝ ሰላምታ ሰጠው። መሬቱ ምስር፣ ባቄላ፣ ሽንብራ፣ ባሮ ሽንኩርት፣ ቀይ ሽንኩርትና ኪያር ያበቅላል። ገበሬው ዓይኖቹን ወደ ሰማይ በማንሳት አምላክን ለመልካም ስጦታዎቹ ሁሉ ከልቡ አመሰገነ።​—መዝሙር 65:9-11

[ከገጽ 28-30 የሚገኙ ሥዕሎች]

(ጽሑፉን ተመልከት)