ልጆቻችሁን አስተምሩ
ኢዮአታም በቤተሰቡ ውስጥ ችግር ቢያጋጥመውም በታማኝነት ጸንቷል
አንድ ወላጅ እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን ማገልገል ሲያቆም ልጁ ሁኔታዎች አስቸጋሪ ሊሆኑበት ይችላሉ። እስቲ ኢዮአታምን እንደ ምሳሌ እንመልከት። ኢዮአታም ልጅ በነበረበት ጊዜ በቤተሰቡ ውስጥ ያጋጠመውን ችግር እንመለከታለን።
የኢዮአታም አባት ዖዝያን የይሁዳ ንጉሥ ነበር። በአገሪቱ ውስጥ የመጨረሻው ከፍተኛ ሥልጣን የነበረው እሱ ነው። ዖዝያን፣ ኢዮአታም ከመወለዱም በፊት ለበርካታ ዓመታት ጥሩ ንጉሥ ሆኖ አስተዳድሯል። ይሁንና ከጊዜ በኋላ ማለትም ኢዮአታም ገና ትንሽ ልጅ እያለ ዖዝያን በትዕቢት የአምላክን ሕግ ጣሰ። በመሆኑም አምላክ ለምጽ በሚባል መጥፎ በሽታ እንዲያዝ አደረገ። በዚህ ወቅት ኢዮአታም ምን እንዳደረገ ታውቃለህ?— *
ኢዮአታም ይሖዋን ማገልገሉን ቀጠለ። እናቱ ኢየሩሳ ረድታው ሊሆን ይችላል። ያም ቢሆን አባቱ ዖዝያን ከይሖዋ ቤት ከተባረረ በኋላ ኢዮአታም ለይሖዋ ያለውን ታማኝነት ጠብቆ መቀጠል ቀላል እንደማይሆንለት ግልጽ ነው።
አባትህ ወይም እናትህ ይሖዋን ማምለካቸውን ቢያቆሙስ? ይህ ሁኔታዎች በጣም አስቸጋሪ እንዲሆኑብህ ያደርጋል አይደል?— ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነት ነገር ሊያጋጥም እንደሚችል ማሰብ ስህተት አይደለም። ዳዊት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የጻፈው ሐሳብ ይህን ያሳያል።
የዳዊት አባት የሆነው እሴይ ጥሩ ሰው ነበር። እሴይ የይሖዋ አገልጋይ የነበረ ሲሆን ዳዊትም አባቱን እንደሚወደው እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ይሁንና ዳዊት ይሖዋን ከእሴይ አስበልጦ ይወደው ነበር። እንዲህ የምንለው ለምን እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
እባክህ መዝሙር 27:10ን ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አውጣ። ዳዊት እዚህ ጥቅስ ላይ “አባቴና እናቴ ቢተዉኝ እንኳ፣ እግዚአብሔር ይቀበለኛል” በማለት ጽፏል። እስቲ አስበው! እዚህ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ የዳዊት አባት እሴይ ወይም እናቱ ይሖዋን ማገልገላቸውን ቢያቆሙ እንኳ እሱ ይሖዋን ማምለኩን እንደማያቋርጥ እየገለጸ ነው።
አንተስ? አባትህ ወይም እናትህ ይሖዋን ማምለካቸውን ቢያቆሙ አንተ እሱን ማገልገልህን ትቀጥላለህ?— ራስህን እንዲህ ብለህ መጠየቅህ በጣም አስፈላጊ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተገለጸው በጣም አስፈላጊ ትእዛዝ አንጻር ይህን ጥያቄ ማንሳታችን ጠቃሚ ነው። ትእዛዙ “አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና በሙሉ አእምሮህ ውደድ” ይላል።
ይህ ትእዛዝ ሁኔታዎች አስቸጋሪ ቢሆኑም ለይሖዋ ታማኝ መሆን እንዳለብን ይጠቁማል። ይሖዋን ማገልገላችንን እንድናቆም የሚፈልገው ማን ይመስልሃል?— የአምላክ ጠላት የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ ነው። ኢየሱስ ሰይጣንን “የዚህ ዓለም ገዥ” በማለት ጠርቶታል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣን “የዚህ ሥርዓት አምላክ” እንደሆነ ይናገራል። ታዲያ ሰይጣንን ልንፈራው ይገባል?—
አይገባም። ሰይጣንን ከመፍራት ይልቅ ይሖዋ ከእሱ የበለጠ ኃይል እንዳለው ማስታወስ ይኖርብናል። ይሖዋ፣ በእሱ ከታመንን ጥበቃ ያደርግልናል። መጽሐፍ ቅዱስህን አውጥተህ ይሖዋ ዳዊትን፣ ግዙፍና አስፈሪ ከነበረው ከጎልያድ ጥቃት የጠበቀው እንዴት እንደሆነ አንብብ። በታማኝነት የምትጸና ከሆነ ይሖዋ ለአንተም ጥበቃ ያደርግልሃል።
ከመጽሐፍ ቅዱስህ ላይ
^ စာပိုဒ်၊ 4 ይህን ርዕስ የምታነበው ከትንሽ ልጅ ጋር ከሆነ፣ ይህ ሰረዝ ቆም ብለህ ልጁ ሐሳቡን እንዲገልጽ እንድታበረታታው ለማስታወስ ተብሎ የተደረገ ነው።