በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ወደ አምላክ ቅረብ

“ደጋግማችሁ ለምኑ፣ ይሰጣችኋል”

“ደጋግማችሁ ለምኑ፣ ይሰጣችኋል”

“ጌታ ሆይ፣ . . . እንዴት እንደምንጸልይ አስተምረን።” (ሉቃስ 11:1) ከደቀ መዛሙርቱ መካከል አንዱ ለኢየሱስ ከላይ ያለውን ጥያቄ አቅርቦለት ነበር። ኢየሱስ ለጥያቄው መልስ ሲሰጥ ሁለት ምሳሌዎችን የተናገረ ሲሆን ምሳሌዎቹ መጸለይ ያለብን እንዴት እንደሆነና በአምላክ ዘንድ ተሰሚነት ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለብን ያስገነዝቡናል። አንተም አምላክ ጸሎትህን ይሰማ እንደሆነና እንዳልሆነ አሳስቦህ የሚያውቅ ከሆነ ኢየሱስ የሰጠውን መልስ ለማወቅ መጓጓትህ አይቀርም።ሉቃስ 11:5-13ን አንብብ።

የመጀመሪያው ምሳሌ በጸሎት አቅራቢያው ላይ ያተኩራል። (ሉቃስ 11:5-8) ኢየሱስ በተናገረው ታሪክ ላይ፣ አንድ ሰው በማታ እንግዳ ይመጣበታል፤ ሆኖም ይህ ሰው ለእንግዳው የሚያቀርበው ምግብ አልነበረውም። እንግዳ ለተቀበለው ሰው ይህ ጉዳይ በጣም አሳሳቢ ነበር። ጊዜው ሌሊት ቢሆንም ይህ ግለሰብ ዳቦ ለመበደር ወደ አንድ ጓደኛው ቤት ሄደ። ጓደኛው ከቤተሰቡ ጋር ተኝቶ ስለነበር መጀመሪያ ላይ ተነስቶ ሊሰጠው ፈቃደኛ አልሆነም። ነገር ግን የጠየቀውን ነገር ሳያገኝ ላለመመለስ የቆረጠው እንግዳ የመጣበት ይህ ሰው፣ ጓደኛው ተነስቶ የተወሰነ ምግብ እስኪሰጠው ድረስ መወትወቱን ቀጠለ። *

ታዲያ ይህ ምሳሌ ስለ ጸሎት ምን ያስተምረናል? ኢየሱስ መወትወት እንዳለብን ማስተማሩ ነበር፤ በሌላ አባባል ደጋግመን መለመን፣ መፈለግና ማንኳኳት አለብን ማለት ነው። (ሉቃስ 11:9, 10) ለምን? ኢየሱስ፣ አምላክ ጸሎታችንን ለመስማት ፈቃደኛ እንዳልሆነ መናገሩ ነበር? አይደለም። ኢየሱስ፣ አቅማምቶ ከነበረው ጎረቤት በተለየ ሁኔታ አምላክ በእምነት ወደ እሱ የሚጸልዩ ሰዎች ተገቢ የሆነ ጥያቄ እስካቀረቡ ድረስ መልስ ለመስጠት እንደሚጓጓ እያስተማረ ነበር። እኛም በጸሎት በመጽናት እንዲህ ዓይነት እምነት እንዳለን እናሳያለን። ደጋግመን በመለመን የጠየቅነውን ነገር በእርግጥ እንደምንፈልግ እንዲሁም አምላክ ፈቃዱ ከሆነ ሊሰጠን እንደሚችል ጽኑ እምነት እንዳለን እናሳያለን።—ማርቆስ 11:24፤ 1 ዮሐንስ 5:14

ሁለተኛው ምሳሌ ደግሞ የሚያተኩረው ‘ጸሎት ሰሚ’ በሆነው በይሖዋ ላይ ነው። (መዝሙር 65:2) ኢየሱስ “ከመካከላችሁ ልጁ ዓሣ ቢለምነው በዓሣ ፋንታ እባብ የሚሰጥ አባት ይኖራል? ወይስ እንቁላል ቢለምነው ጊንጥ ይሰጠዋል?” የሚል ጥያቄ አቅርቧል። መልሱ ግልጽ ነው፣ አሳቢ የሆነ አንድ አባት ለልጆቹ የሚጎዳቸውን ነገር አይሰጣቸውም። በተጨማሪም ኢየሱስ የምሳሌውን ትርጉም ሲያብራራ ፍጹም ያልሆኑ አባቶች ለልጆቻቸው “መልካም ስጦታ” የሚሰጡ ከሆነ “በሰማይ ያለው አባት” ምድራዊ ልጆቹ ሲለምኑት ከሁሉ የተሻለውን ስጦታ ማለትም “መንፈስ ቅዱስን እንዴት አብልጦ አይሰጣቸውም!” ብሏል። *ሉቃስ 11:11-13፤ ማቴዎስ 7:11

አምላክ በእምነት ወደ እሱ የሚጸልዩ ሰዎች ተገቢ የሆነ ጥያቄ እስካቀረቡ ድረስ መልስ ለመስጠት ይጓጓል

ይህ ምሳሌ ‘ጸሎት ሰሚ’ ስለሆነው ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረናል? ይሖዋን ለልጆቹ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማቅረብ በጣም እንደሚጓጓ አሳቢ አባት አድርገን እንድንመለከተው ኢየሱስ ይፈልጋል። በመሆኑም የይሖዋ አገልጋዮች እሱን መለመን የሚፈልጉትን ነገር ለመጠየቅ ነፃነት ሊሰማቸው ይችላል። ደግሞም ይሖዋ ከሁሉ የተሻለውን ነገር እንደሚመኝላቸው ስለሚያውቁ የጸሎታቸው መልስ ያልጠበቁት ዓይነት ቢሆንም እንኳ ያለማንገራገር ሊቀበሉ ይችላሉ። *

በሚያዝያ ወር የሚነበብ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል፦

ከሉቃስ 7 እስከ 21

^ စာပိုဒ်၊ 4 ኢየሱስ የተናገረው ምሳሌ በወቅቱ የነበረውን ልማድና ባሕል ያሳያል። አይሁዳውያን እንግዳ መቀበልን የተቀደሰ ተግባር አድርገው ይመለከቱት ነበር። አንድ ቤተሰብ ዳቦ የሚጋግረው ለዕለቱ የሚበቃውን ያህል ስለነበረ ዳቦ ካለቀበት ከጎረቤት መበደር የተለመደ ነገር ነበር። እንዲሁም ቤተሰቡ ድሃ ከሆነ ሁሉም የቤተሰቡ አባላት የሚተኙት በአንድ ክፍል ውስጥ መሬት ላይ ነበር።

^ စာပိုဒ်၊ 6 ኢየሱስ አብዛኛውን ጊዜ ትንሽ ከሆነው ነገር ተነስቶ ይበልጥ ክብደት ያለውን ነገር ለማብራራት “እንዴት አብልጦ” የሚለውን አነጋገር ይጠቀም ነበር። አንድ ምሁር እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል፦ “‘ሀ እውነት ከሆነ ለ ደግሞ እንዴት አብልጦ እውነት አይሆንም?’ ብሎ የማስረዳት ያህል ነው።”

^ စာပိုဒ်၊ 7 መጸለይ ያለብህ እንዴት እንደሆነና በአምላክ ዘንድ ተሰሚነት ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለብህ ለማወቅ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 17 ተመልከት።