በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ልጆቻችሁን አስተምሩ

አምላክ ሊያዝን ይችላል—እሱን ማስደሰት የምንችለው እንዴት ነው?

አምላክ ሊያዝን ይችላል—እሱን ማስደሰት የምንችለው እንዴት ነው?

በሰውነትህ ላይ ጉዳት በመድረሱ በጣም ስላመመህ አልቅሰህ ታውቃለህ? * ሁላችንም እንዲህ ዓይነት ነገር አጋጥሞን ያውቅ ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ ግን የምናለቅሰው አካላችን ስለተጎዳ ሳይሆን የሚያሳዝን ነገር ስላጋጠመን ሊሆን ይችላል። አንድ ሰው ስለ እኛ እውነት ያልሆነ መጥፎ ነገር ተናግሮ ይሆናል። ይህ የሚያሳዝን ነገር ነው አይደል?— አምላክም ስለ እሱ ውሸት ሲነገር ያዝናል። እስቲ አምላክን ስላሳዘነው ሁኔታ እንመልከት፤ እንዲሁም አምላክን ከማሳዘን ይልቅ እሱን ማስደሰት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመርምር።

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክን እንደሚወዱ የተናገሩ አንዳንድ ሰዎች እሱን ‘እንዳሳዘኑት’ ይናገራል። ይሖዋ፣ ያዘዘንን ነገር ሳናደርግ ስንቀር የሚያዝነው ለምን እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

ይሖዋ በምድር ላይ የፈጠራቸው የመጀመሪያዎቹ ሁለት ሰዎች በጣም አሳዝነውታል። አምላክ፣ እነዚህ ሁለት ሰዎች “በዔድን የአትክልት ስፍራ” እንዲኖሩ አድርጎ ነበር። እነዚህ ሁለት ሰዎች እነማን ናቸው?— አዎን፣ አዳም እና ከእሱ በኋላ የተፈጠረችው ሔዋን ናቸው። እነዚህ ሰዎች ይሖዋን ያሳዘኑት እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

ይሖዋ በዔድን ገነት ውስጥ ካስቀመጣቸው በኋላ የአትክልት ቦታውን እንዲንከባከቡ ነገራቸው። በተጨማሪም ልጆች ወልደው ከልጆቻቸው ጋር በዚህ የአትክልት ስፍራ ለዘላለም መኖር እንደሚችሉ ገለጸላቸው። ይሁን እንጂ አዳምና ሔዋን ልጆች ከመውለዳቸው በፊት አንድ የሚያሳዝን ነገር ተፈጸመ። ይህ የሚያሳዝን ነገር ምን እንደሆነ ታውቃለህ?— አንድ መልአክ፣ መጀመሪያ ላይ ሔዋንን ከዚያ በኋላ ደግሞ አዳምን በይሖዋ ላይ አሳመፃቸው። ይህ የሆነው እንዴት እንደሆነ ማወቅ ትፈልጋለህ?

መልአኩ፣ የሚናገር የሚመስል እባብ በመጠቀም ሔዋንን ቀረባት። ሔዋንም እባቡ የተናገረው ነገር አስደሰታት፤ ምክንያቱም እባቡ “እንደ እግዚአብሔር” እንደምትሆን ነግሯት ነበር። ስለዚህ እባቡ የነገራትን ነገር አደረገች። እባቡ ‘ምን አድርጊ’ እንዳላት ታውቃለህ?

 ይሖዋ፣ በአትክልቱ ስፍራ ካሉት ዛፎች መካከል የአንዱን ዛፍ ፍሬ እንዳይበሉ ለአዳም ነግሮት ነበር፤ ሔዋን ግን ይህን ፍሬ በላች። አምላክ ሔዋንን ከመፍጠሩ በፊት ለአዳም “በአትክልት ስፍራው ውስጥ ከሚገኝ ከማንኛውም ዛፍ ፍሬ ትበላለህ። ነገር ግን መልካምና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ አትብላ፤ ምክንያቱም ከእርሱ በበላህ ቀን በእርግጥ ትሞታለህ” ብሎት ነበር።

ሔዋን ይህንን ትእዛዝ ታውቅ ነበር። ይሁን እንጂ ዛፉን አተኩራ ስትመለከት “የዛፉ ፍሬ ለመብል መልካም፣ ለዐይን የሚያስደስት” እንደሆነ ተሰማት፤ ከዚያም “ከፍሬው ወስዳ በላች።” በኋላም ፍሬውን ለአዳም ሰጠችውና “እርሱም በላ።” አዳም ፍሬውን የበላው ለምን ይመስልሃል?— ሔዋንን ከይሖዋ አስበልጦ ስለወደዳት ነው። አምላክን ከማስደሰት ይልቅ እሷን ለማስደሰት መረጠ። ይሁን እንጂ ከማንም የበለጠ መታዘዝ ያለብን ይሖዋን ነው!

ሔዋንን ያናገራትን እባብ ታስታውሰዋለህ? ሰዎች፣ አሻንጉሊት እንደሚናገር ማስመሰል እንደሚችሉ ሁሉ ይህ እባብ እንደሚናገር ያስመሰለው አንድ አካል አለ። እባቡ እንደተናገረ ያስመሰለው ማን ነው?— “ዲያብሎስና ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው የመጀመሪያው እባብ” ነው።

ይሖዋን ማስደሰት የምትችለው እንዴት እንደሆነ ታውቃለህ?— ይህን ማድረግ የምትችለው ምንጊዜም አምላክን ለመታዘዝ ጥረት በማድረግ ነው። ሰይጣን፣ ሁሉም ሰው እሱ የሚፈልገውን ነገር እንዲፈጽም ማድረግ እንደሚችል ይናገራል። በመሆኑም ይሖዋ “ልጄ ሆይ፣ ጠቢብ ሁን፣ ልቤንም ደስ አሰኘው፣ ለሚሰድበኝ መልስ መስጠት ይቻለኝ ዘንድ” በማለት አጥብቆ ይመክረናል። ሰይጣን ይሖዋን ይሰድበዋል። ሰይጣን፣ ሰው ሁሉ አምላክን ማገልገሉን እንዲተው ማድረግ እንደሚችል ይናገራል። ስለዚህ ይሖዋን በመታዘዝና እሱን በማገልገል ልታስደስተው ትችላለህ! ይህን ለማድረግ የቻልከውን ሁሉ ትጥራለህ?

ከመጽሐፍ ቅዱስህ ላይ

^ አን.3 ይህን ርዕስ የምታነበው ከትንሽ ልጅ ጋር ከሆነ፣ ይህ ሰረዝ ቆም ብለህ ልጁ ሐሳቡን እንዲገልጽ እንድታበረታታው ለማስታወስ ተብሎ የተደረገ ነው።