ፈታኝ ስሜቶችን ማሸነፍ ትችላለህ!
“ኢንተርኔት የከፈትኩት ፖርኖግራፊ ለማየት አልነበረም። ነገር ግን ድንገት አንድ ማስታወቂያ ብቅ አለ። ምን እንደነካኝ አላውቅም፣ ብቻ ማስታወቂያውን ለማየት ከፈትኩት።”—ኮዲ *
“በሥራ ቦታ የማውቃት አንዲት ቆንጆ ልጅ እኔን ማሽኮርመም ጀመረች። አንድ ቀን ወደ አንድ ሆቴል ሄደን ጥሩ ጊዜ እንድናሳልፍ ግብዣ አቀረበችልኝ። ምን እንደፈለገች ገብቶኛል።”—ዲለን
“በፍላጎት የሚመጣ ፈተና አይሁን እንጂ ሌሎች ነገሮችን ማሸነፍ አያቅተኝም።” በቀልድ መልክ የተነገረው ይህ አባባል ሰዎች ስለ ፈታኝ ስሜቶች ያላቸውን አመለካከት ጥሩ አድርጎ ይገልጻል፤ ውስጣቸው እንዲህ ያለውን ስሜት ይፈልገዋል። ሌሎች ግን ፈታኝ ስሜትን የሚመለከቱት ድል ቢያደርጉት በጣም ደስ የሚላቸው እረፍት የማይሰጥ ጠላት እንደሆነ አድርገው ነው። አንተስ ምን ትላለህ? ፈታኝ ስሜት ሲያጋጥምህ እጅ ትሰጣለህ ወይስ ትቋቋመዋለህ?
እርግጥ ነው፣ ፈታኝ ስሜቶች ሁሉ የከፋ ችግር ውስጥ ያስገቡናል ማለት አይደለም። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው መብላት ከሚገባው ጣፋጭ ነገር ትንሽ በዛ አድርጎ በድብቅ ቢበላ በጤናው ላይ ያን ያህል ጉዳት አይመጣ ይሆናል። ይሁን እንጂ ለሌሎች ፍላጎቶች በተለይም ወደ ፆታ ብልግና ለሚመሩ ስሜቶች መሸነፍ አሳዛኝ መዘዞች ሊያስከትል ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “የሚያመነዝር ሰው ግን ማመዛዘን ይጐድለዋል፤ እንዲህ የሚያደርግ ሁሉ ራሱን ያጠፋል” በማለት ያስጠነቅቃል።—ምሳሌ 6:32, 33
የሥነ ምግባር ብልግና እንድትፈጽም የሚገፋፋ ፈተና ድንገት ቢያጋጥምህ ምን ምላሽ መስጠት ይኖርብሃል? መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ መልስ ሲሰጥ “የአምላክ ፈቃድ እንድትቀደሱ ይኸውም ከዝሙት እንድትርቁ እንዲሁም ከእናንተ እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ዕቃ እንዴት በቅድስናና በክብር መያዝ እንዳለበት እንዲያውቅ ነው” ይላል። (1 ተሰሎንቄ 4:3, 4) ታዲያ እንዲህ ያለውን ጥንካሬ ማዳበር የምትችለው እንዴት ነው? በዚህ ረገድ ሊረዱህ የሚችሉ ሦስት እርምጃዎችን እንመልከት።
እርምጃ 1፦ ዓይንህን ተቆጣጠር
የፆታ ስሜት የሚያነሳሱ ነገሮችን ወደ ዓይናችን ማስገባታችን ትርፉ ተገቢ ያልሆኑ ምኞቶች እንዲቀሰቀሱ ማድረግ ብቻ ነው። ኢየሱስ በማየትና በመመኘት መካከል ያለውን ቁርኝት ሲገልጽ “የፆታ ስሜቱ እስኪቀሰቀስ ድረስ አንዲትን ሴት በምኞት የሚመለከት ሁሉ በዚያን ጊዜ በልቡ ከእሷ ጋር አመንዝሯል” በማለት አስጠንቅቋል። ነጥቡን በግልጽ ለማስረዳት የግነት ዘይቤያዊ አነጋገር በመጠቀም “ቀኝ ዓይንህ ቢያሰናክልህ አውጥተህ ጣለው” በማለት አሳስቧል። (ማቴዎስ 5:28, 29) ኢየሱስ ሊያስተላልፍ የፈለገው ነጥብ ምንድን ነው? ፈታኝ ስሜቶችን ለመቋቋም ከፈለግን ቆራጥ እርምጃ መውሰድና ዓይናችን የፆታ ስሜት የሚቀሰቅሱ ነገሮችን እንዳይመለከት መቆጣጠር አለብን።
ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት፦ አንድ ሰው ብረት ሲበይድ ነጸብራቁ ድንገት ዓይንህ ላይ በራብህ እንበል። ነጸብራቁን አፍጥጠህ ማየትህን ትቀጥላለህ? እንዲህ እንደማታደርግ የታወቀ ነው! ዓይንህን ለመጠበቅ፣ ወይ ፊትህን ታዞራለህ አሊያም ነጸብራቁን በሆነ መንገድ ትጋርዳለህ። በተመሳሳይም በወረቀት፣ በፊልም ወይም በአካል ሊሆን ይችላል የፆታ ስሜት የሚቀሰቅስ ነገር ድንገት ቢያጋጥምህ ቶሎ ብለህ ፊትህን አዙር። የምታየው ነገር አእምሮህን እንዳይመርዘው ተጠንቀቅ። ቀደም ሲል የፖርኖግራፊ ሱሰኛ የነበረ ኽዋን የሚባል ሰው እንዲህ ብሏል፦ “ቆንጆ ሴት በማይበት ጊዜ በአብዛኛው ደጋግሜ እንዳያት የሚገፋፋ ስሜት ይሰማኛል። ስለዚህ ዓይኖቼን ወደ ሌላ አቅጣጫ እንዲመለከቱ አስገድዳቸዋለሁ፤ እንዲሁም ‘ወደ ይሖዋ ጸልይ! አሁኑኑ መጸለይ ያስፈልግሃል!’ ብዬ ለራሴ እናገራለሁ። ከጸለይኩ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የሚገፋፋኝ ስሜት ይለቀኛል።”—ማቴዎስ 6:9, 13፤ 1 ቆሮንቶስ 10:13
ታማኙ ኢዮብ የተናገረውንም ልብ በል፦ “ወደ ኰረዳዪቱ ላለመመልከት፣ ከዓይኔ ጋር ቃል ኪዳን ገብቻለሁ።” (ኢዮብ 31:1) አንተስ እንዲህ ያለ ቁርጥ ውሳኔ ለምን አታደርግም?
እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ የፆታ ስሜት የሚቀሰቅስ ነገር ድንገት ብትመለከት ቶሎ ብለህ ዓይኖችህን አዙር። “ከንቱ ነገር ከማየት ዓይኖቼን መልስ” በማለት የጸለየውን መዝሙራዊ ምሳሌ ተከተል።—መዝሙር 119:37
እርምጃ 2፦ የምታስበውን ነገር ተቆጣጠር
ሁላችንም ፍጹማን ባለመሆናችን አንዳንድ ጊዜ ከመጥፎ ምኞት ጋር እንታገል ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ “እያንዳንዱ ሰው በራሱ ምኞት ሲማረክና ሲታለል ይፈተናል። ከዚያም ምኞት ከፀነሰች በኋላ ኃጢአትን ትወልዳለች” በማለት ይናገራል። (ያዕቆብ 1:14, 15) ታዲያ እንዲህ ወዳለው አዘቅት ውስጥ ከመግባት መቆጠብ የምትችለው እንዴት ነው?
መጥፎ ምኞቶች ሲመጡብህ፣ ምርጫ ማድረግ እንደምትችል አስታውስ። እነዚህን ምኞቶች ተዋጋቸው። ከአእምሮህ ነቅለህ አውጣቸው። የብልግና ሐሳብ ሲመጣብህ በጉዳዩ ላይ ለማውጠንጠን እምቢ በል። በኢንተርኔት ፖርኖግራፊ የማየት ሱስ የነበረበት ትሮይ የተባለ አንድ ሰው እንዲህ ብሏል፦ “መልካም በሆኑ ሐሳቦች ላይ በማተኮር መጥፎ ሐሳቦችን ከአእምሮዬ ለማስወገድ ታግያለሁ። ይህን ማድረግ ቀላል አልነበረም። ብዙ ጊዜ አገርሽቶብኝ ያውቃል። የኋላ ኋላ ግን የማስበውን ነገር መቆጣጠር ተማርኩ።” በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ሳለች ለሥነ ምግባር ብልግና ከሚገፋፉ ፈታኝ ስሜቶች ጋር ትታገል የነበረች ኤልሳ የምትባል አንዲት ሴት ደግሞ “በሥራ በመጠመድና ወደ ይሖዋ በመጸለይ መጥፎ ሐሳቦችን መቆጣጠር ችያለሁ” በማለት ተናግራለች።
እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ የብልግና ሐሳቦች ሲመጡብህ ወዲያውኑ ጸልይ። “እውነት የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ቁም ነገር ያለበትን ነገር ሁሉ፣ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ተወዳጅ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ በመልካም የሚነሳውን ነገር ሁሉ፣ በጎ የሆነውን ሁሉና ምስጋና የሚገባውን ነገር ሁሉ” በማሰብ መጥፎ ሐሳቦችን ተዋጋ።—ፊልጵስዩስ 4:8
እርምጃ 3፦ እርምጃህን ተቆጣጠር
ምኞት፣ ፈተናና የሁኔታዎች መመቻቸት አብረው ሲገጣጠሙ በቀላሉ ችግር ውስጥ ልትገባ ትችላለህ። (ምሳሌ 7:6-23) ታዲያ እንዲህ ያለ ወጥመድ ውስጥ እንዳትገባ ራስህን መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ “አስተዋይ ሰው አደጋ ሲያይ መጠጊያ ይሻል፤ ብስለት የጐደለው ግን በዚያው ይቀጥላል፤ መከራም ያገኘዋል” በማለት ጥበብ ያዘለ ምክር ይሰጣል። (ምሳሌ 22:3) በመሆኑም እርምጃህን ተቆጣጠር። ችግር ውስጥ ሊጨምሩህ የሚችሉ ሁኔታዎችን አስቀድመህ በማወቅ ራቃቸው። (ምሳሌ 7:25) ፖርኖግራፊ ከማየት ሱስ የተላቀቀ ፊሊፕ የተባለ አንድ ሰው እንዲህ ብሏል፦ “የቤተሰባችንን ኮምፒውተር ሁሉም ሰው ማየት በሚችልበት ቦታ ያስቀመጥኩት ሲሆን አላስፈላጊ ድረ ገጾችን የሚያጣራ ፕሮግራም ጫንኩበት። በተጨማሪም ኢንተርኔት የምጠቀመው ሌሎች በሚኖሩበት ጊዜ ብቻ ነው።” ቀደም ሲል የተጠቀሰው ትሮይም እንዲህ ብሏል፦ “የፆታ ስሜት የሚቀሰቅሱ ፊልሞችን ከማየትና የብልግና ወሬ ከሚያወሩ ሰዎች ጋር ጊዜ ከማሳለፍ እቆጠባለሁ። ራሴን ለአደጋ ማጋለጥ አልፈልግም።”
እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ የራስህን ድክመቶች በሐቀኝነት መርምርና ለፈተና ሊያጋልጡህ ከሚችሉ ሁኔታዎች ለመራቅ አስቀድመህ እቅድ አውጣ።—ማቴዎስ 6:13
ተስፋ አትቁረጥ!
የቻልከውን ሁሉ ጥረት አድርገህም ለፈተና ብትሸነፍስ? ተስፋ ቆርጠህ ጥረት ማድረግህን አትተው። መጽሐፍ ቅዱስ “ጻድቅ ሰባት ጊዜ እንኳ ቢወድቅ ይነሣል” ይላል። (ምሳሌ 24:16) አዎን፣ የሰማዩ አባታችን ‘እንድንነሳ’ ያበረታታናል። ታዲያ የእሱን ፍቅራዊ እርዳታ ትቀበላለህ? ከሆነ እንዲረዳህ በጸሎት ከመጠየቅ አትታክት። ቃሉን በማጥናት እምነትህን ገንባ። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት ቁርጥ ውሳኔህን አጠናክር። “አበረታሃለሁ፤ እረዳሃለሁ” በማለት አምላክ የገባውን ቃል አስብ።—ኢሳይያስ 41:10
በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው ኮዲ “የፖርኖግራፊ ሱሴን ለማሸነፍ ብርቱ ጥረት ማድረግ ጠይቆብኛል። የተሸነፍኩባቸው በርካታ ጊዜያት ቢኖሩም በመጨረሻ በአምላክ እርዳታ ተሳክቶልኛል” ብሏል። ዲለንም እንዲህ ብሏል፦ “ከሥራ ባልደረባዬ ጋር በቀላሉ የፆታ ግንኙነት ልፈጽም እችል ነበር። ይሁን እንጂ በአቋሜ በመጽናት ‘እምቢ!’ አልኳት። ንጹሕ ሕሊና መያዝ እጅግ ያስደስታል። ከሁሉ በላይ ደግሞ የይሖዋን ልብ እንዳስደሰትኩ አውቃለሁ።”
አንተም ቆራጥ በመሆን ፈታኝ ስሜቶችን የምታሸንፍ ከሆነ አምላክ እንደሚደሰትብህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ።—ምሳሌ 27:11
^ አን.2 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተቀይረዋል።