የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | መጨረሻው ቀርቧል?
ብዙዎች ከመጨረሻው ቀን በሕይወት ይተርፋሉ—አንተም መትረፍ ትችላለህ
መጽሐፍ ቅዱስ “ከዓለም መጀመሪያ አንስቶ እስካሁን ድረስ ሆኖ የማያውቅ . . . ታላቅ መከራ ይከሰታል። እንዲያውም ቀኖቹ ባያጥሩ ኖሮ ሥጋ ለባሽ ሁሉ ባልዳነ ነበር” በማለት በመጨረሻው ቀን ጥፋትም እንደሚኖር ይነግረናል። (ማቴዎስ 24:21, 22) ይሁን እንጂ ብዙ ሰዎች ከጥፋት እንደሚተርፉ አምላክ ቃል ገብቷል፦ “ዓለምም ሆነ ምኞቱ ያልፋሉ፤ የአምላክን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።”—1 ዮሐንስ 2:17
አንተስ ይህ ዓለም ሲያልፍ በሕይወት ተርፈህ ‘ለዘላለም መኖር’ የምትፈልግ ከሆነ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? ለክፉ ቀን መጠባበቂያ የሚሆን እህልና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ማከማቸት ወይም ሌሎች አካላዊ ዝግጅቶችን ማድረግ መጀመር ይኖርብህ ይሆን? እንዲህ ማድረግ አያስፈልግህም። መጽሐፍ ቅዱስ ቅድሚያ መስጠት ያለብን ለእነዚህ ነገሮች እንዳልሆነ ይነግረናል። እንዲህ ይላል፦ “እነዚህ ሁሉ ነገሮች በዚህ ሁኔታ የሚቀልጡ ከሆነ ቅዱስ ሥነ ምግባር በመከተልና ለአምላክ ያደራችሁ መሆናችሁን የሚያሳዩ ተግባሮች በመፈጸም ምን ዓይነት ሰዎች መሆን እንዳለባችሁ ልታስቡበት ይገባል! . . . የይሖዋን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና በአእምሯችሁ አቅርባችሁ እየተመለከታችሁ ልትኖሩ ይገባል!” (2 ጴጥሮስ 3:10-12) በዚህ ጥቅስ ዙሪያ ያለው ሐሳብ እንደሚያሳየው እንደሚቀልጡ የተገለጹት “እነዚህ ሁሉ ነገሮች” የዚህን ብልሹ ዓለም አገዛዞችና ከአምላክ አገዛዝ ይልቅ እንዲህ ዓይነቱን ብልሹ አገዛዝ የሚመርጡ ሰዎችን ሁሉ ያካትታሉ። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ቁሳዊ ነገሮችን ማከማቸት ከመጪው ጥፋት ለመዳን አይረዳንም።
በእርግጥም ከጥፋቱ መትረፋችን የተመካው ለይሖዋ አምላክ ያደርን በመሆናችን ላይ ነው፤ እንዲሁም እሱን ለማስደሰት ምን ዓይነት ባሕርይ ማሳየት ብሎም ምን ዓይነት ተግባር መፈጸም እንዳለብን መማር ያስፈልገናል። (ሶፎንያስ 2:3) ስለዚህ ከፍተኛ ትኩረት በሚያሻው ጊዜ ውስጥ እየኖርን መሆናችንን የሚያሳዩትን ግልጽ ምልክቶች ችላ በማለት ብዙኃኑን ከመከተል ይልቅ ‘የይሖዋን ቀን መምጣት መጠበቅና በአእምሯችን አቅርበን መመልከት’ ይኖርብናል። የይሖዋ ምሥክሮች ከመጪው የጥፋት ቀን እንዴት በሕይወት መትረፍ እንደምትችል ከመጽሐፍ ቅዱስ ሊያሳዩህ ይችላሉ።