የሕይወት ታሪክ
ከታዋቂነት የሚበልጥ ነገር አገኘሁ
በ1984 አንድ ምሽት ላይ ተራ ሰው መሆኔ አብቅቶ በድንገት ዝነኛ ወጣት ለመሆን በቃሁ። የዚያን ቀን ወይዘሪት ሆንግ ኮንግ ሆኜ በማሸነፌ ዘውድ ተደፋልኝ። ፎቶግራፌ በመጽሔቶችና በጋዜጦች የፊት ገጽ ላይ ወጣ። ከዚያ በኋላ መዝፈን፣ መደነስ፣ ንግግር ማቅረብ፣ በቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ላይ መቅረብ፣ የሚያማምሩ ልብሶችን መልበስ እንዲሁም እንደ ሆንግ ኮንግ ገዢ ካሉ ታላላቅ ሰዎች ጋር መታየት የሕይወቴ ክፍል ሆነ።
በቀጣዩ ዓመት የፊልም ተዋናይ ሆንኩ፤ ብዙ ጊዜም መሪ ተዋናይ ሆኜ ሠርቻለሁ። ጋዜጠኞች ስለ እኔ ታሪክ ማወቅ ፈለጉ፣ ፎቶግራፍ አንሺዎች እኔን ፎቶግራፍ ለማንሳት አጋጣሚ ይጠባበቁ ነበር፤ በተጨማሪም ሰዎች በፊልምም ሆነ በሌሎች ነገሮች የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ይጋብዙኝ እንዲሁም በምሳና በእራት ግብዣዎች ላይ እንድገኝላቸው ይጠሩኝ ነበር። የሰው ሁሉ ትኩረት በእኔ ላይ አረፈ።
ሲውል ሲያድር ግን ይህ ሁሉ ነገር ያሰብኩትን ያህል የሚያጓጓ እንዳልሆነ ተገነዘብኩ። አብዛኛውን ጊዜ በድርጊት የተሞላ ፊልም ላይ እሠራ ነበር፤ ይህ ደግሞ ለአደጋ ሊዳርግ ይችላል። በሆንግ ኮንግ ያሉ ተዋናዮች በሆሊዉድ የሚደረገውን ያህል ተለዋጭ ተዋናይ ስለማይጠቀሙ ሞተር ብስክሌት እየነዱ በመኪና ላይ መዝለልን የመሳሰሉ ተውኔቶችን የምሠራው እኔ ራሴ ነበርኩ። ኮከብ ተዋናይ ሆኜ የሠራሁባቸው ብዙዎቹ ፊልሞች የፆታ ብልግናና ጭካኔ የሚታይባቸው ነበሩ። በአንዳንዶቹ ላይ ደግሞ መናፍስታዊ ድርጊት ይቀርባል።
በ1995 አንድ የፊልም አዘጋጅ አገባሁ። ደስታ ያስገኛል የሚባለውን ነገር ሁሉ ባገኝም ይኸውም ታዋቂነት፣ ሀብትና አፍቃሪ ባል ቢኖረኝም በመንፈስ ጭንቀትና በሐዘን ተውጬ ነበር። በመሆኑም ትወናውን ለማቆም ወሰንኩ።
የልጅነት እምነቴ ትዝ አለኝ
ትንሽ ልጅ ሳለሁ የነበረኝን እምነትና ያሳለፍኩትን አስደሳች ጊዜ ማስታወስ ጀመርኩ። በዚያን ጊዜ እኔና ታላቅ እህቴ ቅዳሜ በመጣ ቁጥር አንድ የይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰብ ጋር እንሄድ ነበር። አባትየው ጆ መግራዝ ከሦስት ሴቶች ልጆቹ ጋር አንድ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠናን ነበር። ቤተሰባቸው ሞቅ ያለና አፍቃሪ ሲሆን “አጎቴ ጆ” ለሚስቱና ለልጆቹ አክብሮት ነበረው። በተጨማሪም ከእነሱ ጋር ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች መሄድ ያስደስተናል። አንዳንድ ጊዜም ወደ ትልልቅ ስብሰባዎች ይወስዱናል። ከእነሱ ጋር አስደሳች ጊዜ አሳልፈናል። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ስሆን መረጋጋት ይሰማኝ ነበር።
በአንጻሩ ግን በቤተሰባችን ውስጥ አሳዛኝ ነገሮች አይቻለሁ። የአባቴ አኗኗር እናቴን ለከፍተኛ ሐዘን ዳርጓት ስለነበረ ከባድ የመንፈስ ጭንቀት አጋጠማት። አሥር ዓመት ገደማ ሲሆነኝ እናቴ
ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የነበራትን ግንኙነት አቋረጠች። እኔ ግን ከእነሱ ጋር የነበረኝን ግንኙነት ያዝ ለቀቅ እያደረግኩ ቀጠልኩ፤ ከዚያም በ17 ዓመቴ ተጠመቅሁ። ብዙም ሳይቆይ ግን ክርስቲያናዊ ያልሆነ ተግባር በመፈጸሜ የጉባኤው አባል መሆኔ አበቃ።ለመመለስ ወሰንኩ
ከሠርጌ ከጥቂት ጊዜ በኋላ፣ በአካባቢው ከሚገኝ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ሁለት የበላይ ተመልካቾች ሊጠይቁኝ መጡ። ወደ ይሖዋ አምላክ ለመመለስ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ገለጹልኝ፤ እንዲሁም ሲንዲ የምትባል አንዲት ሚስዮናዊ እንድትረዳኝ ዝግጅት አደረጉ። በወቅቱ እምነቴ በጣም ተዳክሞ ነበር፤ በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ የአምላክ ቃል መሆኑን እንድታስረዳኝ ጠየቅኋት። እሷም ፍጻሜያቸውን ያገኙ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን አሳየችኝ። ቀስ በቀስ ጓደኝነታችን እየጠበቀ ሄደ፤ ደግሞም መሠረታዊ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን እንዳጠና ሐሳብ አቀረበችልኝ። እኔም በነገሩ ተስማማሁ። በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ይሖዋ የፍቅር አምላክ እንደሆነና ደስተኛ እንድሆን እንደሚፈልግ ተገነዘብኩ።
ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች እንደገና መሄድ ስጀምር በፊልም ሥራ ላይ ከተሰማሩት ሰዎች ጋር ከመሆን ይልቅ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ጊዜ ማሳለፍ ይበልጥ እንደሚያስደስተኝ ተገነዘብኩ። ይሁንና የልጅነት ሕይወቴ በሰው ላይ እምነት እንዳልጥል አድርጎኛል፤ ከዚህም ሌላ ራሴን እጠላ ነበር። አንዲት የጉባኤው አባል እነዚህን የስሜት ቀውሶች እንዴት መቋቋም እንደምችል ከመጽሐፍ ቅዱስ በማሳየት ረዳችኝ፤ እውነተኛ ወዳጆች ማፍራት የሚቻልበትንም መንገድ ተገነዘብኩ።
ከታዋቂነት የሚበልጥ ነገር
በ1997 እኔና ባለቤቴ በዩናይትድ ስቴትስ፣ ካሊፎርኒያ ወደሚገኘው ወደ ሆሊዉድ ተዛወርን። በዚያም የአምላክ ቃል ከያዘው ጥበብ ጥቅም እንዲያገኙ ሰዎችን በመርዳቱ ሥራ ይበልጥ መካፈል ጀመርኩ። መጽሐፍ ቅዱስን ማስተማር፣ ተዋናይና የፊልም ኮከብ መሆን ከሚያስገኘው የበለጠ ደስታ አምጥቶልኛል። ለምሳሌ ያህል፣ ሆንግ ኮንግ ሳለሁ አውቃት ከነበረችው ከሼሪ ጋር በ2002 ተገናኘን። ሕይወታችን በብዙ መንገድ ይመሳሰላል። ከእኔ በፊት ወይዘሪት ሆንግ ኮንግ የነበረችው እሷ ናት። እንዲያውም በቀጣዩ ዓመት እኔ በውድድሩ ሳሸንፍ ዘውዱን የጫነችልኝ ሼሪ ነበረች። በተጨማሪም የፊልም ተዋናይ፣ ከዚያም የፊልም አዘጋጅ በመሆን ታዋቂ ከሆኑ የፊልም ዳይሬክተሮች ጋር ሠርታለች። ደግሞም ወደ ሆሊዉድ ተዛውራ ነበር።
ሼሪ እጮኛዋን በድንገተኛ የልብ ሕመም በሞት እንዳጣች ስሰማ በጣም አዘንኩላት። ከምትከተለው የቡድሂዝም ሃይማኖት አንድም ማጽናኛ ማግኘት አልቻለችም። እሷም እንደ እኔ ሌሎች የሚቀኑባት ታዋቂ ሰው ብትሆንም ሕይወቷ ደስታ የራቀው ከመሆኑም ሌላ እምነት የምትጥልበት ሰው አልነበረም። ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማርኩትን ነገር እነግራት ጀመር፤ ይሁንና ያደገችው በቡድሂዝም ሃይማኖት ውስጥ በመሆኑ የምነግራትን ነገር ለመረዳት ተቸገረች።
በ2003 አንድ ቀን ሼሪ ፊልም እየሠራች ከነበረበት ከቫንኮቨር፣ ካናዳ ስልክ ደወለችልኝ። መኪና እየነዳች ስትሄድ በተፈጥሮው ውበት ከመደመሟ የተነሳ በድንገት ጮክ ብላ “እውነተኛው አምላክ ማን እንደሆንክ ንገረኝ። ስምህ ማን ነው?” ብላ መጸለይዋን በደስታ ስሜት ተውጣ ነገረችኝ። በዚያው ቅጽበት በአንድ የመንግሥት አዳራሽ በኩል ስታልፍ ይሖዋ የሚለውን ስም አየች። ይህም አምላክ ለጸሎቷ የሰጠው መልስ እንደሆነ ስለተሰማት በተቻለ ፍጥነት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መገናኘት ፈለገች። እኔም ሁኔታዎችን አመቻቸሁላትና ከጥቂት ቀናት በኋላ ቫንኮቨር ውስጥ በቻይንኛ ቋንቋ በሚካሄድ የጉባኤ ስብሰባ ላይ ተገኘች።
ከዚያም ሼሪ እንዲህ አለችኝ፦ “እዚህ ያገኘኋቸው ሰዎች ከልባቸው ያስቡልኛል፤ ስሜቴንም አውጥቼ ልነግራቸው እችላለሁ።” ሼሪ በፊልም ሥራ ላይ ሳለች አንድም ጓደኛ ኖሯት ስለማያውቅ ይህን መስማቴ በጣም
አስደሰተኝ። ሼሪ በስብሰባዎች ላይ መገኘቷን ቀጠለች። ይሁን እንጂ በ2005 ቻይና ውስጥ ሁለት ታሪካዊ ፊልሞችን ለማዘጋጀት ኮንትራት ፈርማ ስለነበረ ወደ ሆንግ ኮንግ መመለስ ነበረባት። ደስ የሚለው ነገር፣ በ2006 ሼሪ ሕይወቷን ለይሖዋ ወስና ሆንግ ኮንግ ውስጥ በአንድ የይሖዋ ምሥክሮች ትልቅ ስብሰባ ላይ ተጠመቀች። ይሖዋን ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ ማገልገል ብትፈልግም እንኳ በፊልም ኢንዱስትሪው ውስጥ ያላት ሥራ ነገሮችን ከባድ አደረገባት፤ ይህም ደስታ አሳጥቷት ነበር።ሌሎችን መርዳት የሚያስገኘው ደስታ
በ2009 የሼሪ ሕይወት ሙሉ በሙሉ ተለወጠ። ይሖዋን በተሟላ ሁኔታ ለማገልገል ስትል ከፊልም ኢንዱስትሪው ለመውጣት ወሰነች። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ብዙ አዳዲስ ጓደኞች አፈራች። ከዚያም የመንግሥቱ ምሥራች የሙሉ ጊዜ ሰባኪ ሆነች፤ ከዚህም የተነሳ ሰዎች የተሻለውን የሕይወት መንገድ እንዲያገኙ መርዳት የሚያስገኘውን እውነተኛ ደስታ ማጣጣም ቻለች።—ማቴዎስ 24:14
ከዚያም ሼሪ ሆንግ ኮንግ ውስጥ ቁጥሩ እየጨመረ የመጣውን በኔፓልኛ የሚካሄድ ቡድን ለመርዳት ስትል ቋንቋውን ለመማር ወሰነች። እዚህ ላይ አንድ ሳልጠቅሰው የማላልፈው ጉዳይ አለ፦ ሆንግ ኮንግ ውስጥ የሚኖሩ አብዛኞቹ ኔፓላውያን እንግሊዝኛ ወይም ቻይንኛ ብዙም ስለማይችሉ እንዲሁም ባሕላቸው የተለየ ስለሆነ ችላ ይባሉ አልፎ ተርፎም ይናቁ ነበር። ሼሪ እነዚህን ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ማስተማር ምን ያህል እንደሚያስደስታት ነገረችኝ። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ቀን ከቤት ወደ ቤት እያገለገለች ሳለ አንዲት ኔፓላዊት አገኘች፤ ይህች ሴት ስለ ኢየሱስ ጥቂት እውቀት ቢኖራትም እውነተኛ አምላክ ስለሆነው ስለ ይሖዋ ግን ምንም የምታውቀው ነገር አልነበረም። ሼሪ፣ ኢየሱስ በሰማይ ወዳለው አባቱ ይጸልይ እንደነበር ለሴትየዋ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አሳየቻት። ሴትየዋም ይሖዋ ተብሎ ወደሚጠራው ወደ እውነተኛው አምላክ መጸለይ እንደምትችል ስትገነዘብ ልቧን ከፍታ ምሥራቹን ተቀበለች። ብዙም ሳይቆይ ባለቤቷና ሴት ልጇ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመሩ።—መዝሙር 83:18፤ ሉቃስ 22:41, 42
ሼሪ የሙሉ ጊዜ ሰባኪ መሆኗ ምን ያህል ደስታ እንዳስገኘላት ስመለከት ‘እኔስ እሷ የምትሠራውን ነገር እንዳላደርግ ምን ያግደኛል?’ ብዬ ራሴን ጠየቅሁ። በዚህ ወቅት ተመልሼ በሆንግ ኮንግ መኖር ጀምሬ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በማስተማሩ ሥራ በተሟላ መንገድ መካፈል እንድችል በሕይወቴ ውስጥ ማስተካከያዎች ለማድረግ ወሰንኩ። ሰዎችን ማዳመጥና የአምላክን ቃል እንዲያውቁ መርዳት እውነተኛ ደስታ እንደሚያስገኝ መገንዘብ ችያለሁ።
የአምላክን ቃል እንዲያውቁ ሰዎችን መርዳት እውነተኛ ደስታ እንደሚያስገኝ መገንዘብ ችያለሁ
ለምሳሌ ያህል፣ ሁልጊዜ ሐዘንተኛ የነበረችና ብዙ ጊዜ የምታለቅስ አንዲት ቬትናማዊት መጽሐፍ ቅዱስ አስጠንቻለሁ። አሁን ለሕይወት አዎንታዊ አመለካከት ያላት ሲሆን ከጉባኤው ጋር ባላት ግንኙነትም በጣም ደስተኛ ነች።
እኔም ሆንኩ ሼሪ ታዋቂ ከመሆን የሚበልጥ ነገር አግኝተናል። በፊልም ኢንዱስትሪው ውስጥ መሆን የሚያስደስትና ዝና የሚያስገኝ ቢሆንም ሰዎችን ስለ ይሖዋ አምላክ ማስተማር ይበልጥ አርኪ ነው፤ ምክንያቱም ይህ ሥራ ለይሖዋ ክብር ያመጣል። በእርግጥም ኢየሱስ “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል” በማለት የተናገራቸውን ቃላት እውነተኝነት በራሳችን ሕይወት አይተናል።—የሐዋርያት ሥራ 20:35