በእምነታቸው ምሰሏቸው | ሣራ
“አንቺ በጣም ውብ ሴት ነሽ”
የሚያማምሩ ዓይኖች ያሏት አንዲት በመካከለኛው ምሥራቅ የምትኖር ሴት በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር። ሣራ ቤቷ ውስጥ ቆማ ዙሪያውን እያማተረች ነው። በዚህ ቤት ውስጥ ብዙ ታሪክ ያሳለፈች በመሆኑ ዓይኖቿ ላይ ሐዘን ቢነበብ የሚያስገርም አይሆንም። እሷና ውድ ባለቤቷ አብርሃም በዚያ ቤት ውስጥ ብዙ አስደሳች ትዝታዎችን አሳልፈዋል። * ይሁንና ይህን ብዙ የደከሙበትን የሞቀ ጎጇቸውን ትተው ሊሄዱ ነው።
አብርሃምና ሣራ የሚኖሩት በርካታ የዕደ ጥበብ ባለሙያዎችና ነጋዴዎች በሚኖሩባት ዑር የተባለች የበለጸገች ከተማ ነበር። በመሆኑም ብዙ ንብረት እንደነበራቸው አያጠራጥርም። ሆኖም ለሣራ፣ ቤቷ እንዲሁ ንብረቶቿን የምታስቀምጥበት ቦታ ብቻ አልነበረም። በዚያ እሷና ባለቤቷ ለበርካታ ዓመታት ክፉውንም ሆነ ደጉን አሳልፈዋል። በዚያ ሆነው ለሚወዱት አምላካቸው ለይሖዋ ብዙ ጊዜ ጸልየዋል። ሣራ ቤቷን እንድትወደው የሚያደርጓት ብዙ ምክንያቶች ነበሯት።
ይሁንና ሣራ ለረጅም ጊዜ የኖረችበትን አካባቢ ትታ ወደ ሌላ ቦታ ለመሄድ ፈቃደኛ ነበረች። በወቅቱ ሣራ 60 ዓመት ገደማ ሳይሆናት አይቀርም፤ በዚህ ዕድሜዋ ወደማታውቀው ቦታ ሄዳ በስጋትና በችግር የተሞላ ሕይወት ልትመራ ነው፤ ተመልሳ የመምጣት ተስፋም የላትም። በሕይወቷ ላይ እንዲህ ያለ ሥር ነቀል ለውጥ ሊከሰት የቻለው እንዴት ነው? እኛስ እሷ ካሳየችው እምነት ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?
‘ከአገርህ ውጣ’
ሣራ ያደገችው ዑር ውስጥ ሳይሆን አይቀርም። ዛሬ ይህቺ ከተማ የፍርስራሽ ክምር ሆና ቀርታለች። ሆኖም ሣራ በነበረችበት ዘመን የንግድ መርከቦች ከተለያዩ አካባቢዎች ውድ ዕቃዎችን ጭነው በኤፍራጥስ ወንዝ ላይ በመጓዝ ወደዚህች የበለጸገች ከተማ ይመጡ ነበር። ጠባብና ጠመዝማዛ የሆኑት የዑር መንገዶች በሰዎች የተሞሉ ነበሩ፤ ወደቦቿ በጀልባዎች ይጨናነቁ ነበር፤ እንዲሁም በርካታ ዕቃዎች ወደ ገበያ ቦታዎቿ ይጎርፉ ነበር። እንግዲህ ሣራ ያደገችው በዚህች ሞቅ ያለች ከተማ ውስጥ ነው ማለት ነው፤ መቼም በከተማዋ ውስጥ የሚኖሩ ብዙ ሰዎችን በስም ሳታውቅ አትቀርም። ሰዎቹም እሷን በደንብ እንደሚያውቋት መገመት እንችላለን፤ ምክንያቱም በጣም ውብ ሴት ነበረች። በተጨማሪም በርካታ ዘመዶቿ የሚኖሩት በዑር ነበር።
መጽሐፍ ቅዱስ ሣራ ታላቅ እምነት የነበራት ሴት እንደሆነች ይናገራል፤ ሆኖም እምነቷ የተመሠረተው በዑር ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች በሚያመልኩት በጨረቃ አምላክ ላይ አልነበረም፤ ለዚህ አምላክ ተብሎ የተሠራ ረጅም ግንብ በከተማይቱ ውስጥ ጉብ ብሎ ይታይ ነበር። ሣራ ግን የምታመልከው እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ሣራ በይሖዋ ላይ እምነት ልታዳብር የቻለችው እንዴት እንደሆነ አይናገርም። አባቷ ቢያንስ በሆነ ወቅት ላይ ጣዖት አምላኪ ነበር። ያም ሆነ ይህ ሣራ የአሥር ዓመት ታላቋ የሆነውን አብርሃምን አገባች። * (ዘፍጥረት 17:17) አብርሃም ከጊዜ በኋላ “በእምነታቸው የተነሳ እንደ ጻድቃን ለተቆጠሩት ሁሉ አባት” ተብሎ ተጠርቷል። (ሮም 4:11) አብርሃምና ሣራ አንዳቸው ለሌላው አክብሮት በማሳየት፣ ጥሩ የሐሳብ ልውውጥ በማድረግና ችግሮች ሲያጋጥሙ ችግሮቹን ለመፍታት አብረው በመሥራት ጠንካራ የሆነ ትዳር መገንባት ችለዋል። ከምንም በላይ አንድነታቸውን ያጠናከረው ግን ለአምላካቸው ያላቸው ፍቅር ነው።
ሣራ ባሏን በጣም ትወደው የነበረ ሲሆን ባልና ሚስቱ በዑር በዘመዶቻቸው ተከበው ይኖሩ ነበር። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ ያልጠበቁት ሁኔታ ገጠማቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ሣራ “መሃን ነበረች፤ ልጅም አልነበራትም” በማለት ይናገራል። (ዘፍጥረት 11:30) በዚያ ዘመን ሰዎች ከነበራቸው አመለካከት አንጻር መሃን መሆን በጣም ፈታኝ ነበር። ነገር ግን ሣራ ለአምላኳና ለባሏ ታማኝ ሆናለች። የአብርሃም የወንድም ልጅ የሆነው ሎጥ አባቱ ሞቶበት ስለነበር እንደ ልጃቸው አድርገው ያሳደጉት አብርሃምና ሣራ ሳይሆኑ አይቀሩም። በዚህ ሁኔታ እየኖሩ ሳሉ ከዕለታት አንድ ቀን ሁሉም ነገር ተለወጠ።
አብርሃም በደስታ ተሞልቶ ወደ ሣራ መጣ። የገጠመውን ሁኔታ ማመን አልቻለም። የሚያመልኩት አምላካቸው በመልአኩ አማካኝነት ተገልጦለት አነጋገረው! ሣራ ባሏን ዓይን ዓይኑን እያየች “ምን አለህ? እባክህ ንገረኝ!” በማለት ስትጠይቀው በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። አብርሃም ምናልባትም መጀመሪያ ላይ አረፍ ብሎ ሐሳቡን ሰብሰብ ካደረገ በኋላ ይሖዋ ምን እንዳለው ነገራት፦ “ከአገርህ ወጥተህ፣ ከዘመዶችህም ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ሂድ።” (የሐዋርያት ሥራ 7:2, 3) ትንሽ ከተረጋጉ በኋላ ግን ይሖዋ በሰጣቸው መመሪያ ላይ በቁም ነገር ማሰብ ጀመሩ። የተደላደለና የተመቻቸ ኑሯቸውን ትተው የዘላን ዓይነት ሕይወት ሊኖሩ ነው! ሣራ ምን ምላሽ ትሰጥ ይሆን? አብርሃም የሣራን ምላሽ ለመስማት ጓጉቶ እንደሚሆን አያጠራጥርም። አብርሃም ሕይወታቸውን የሚለውጥ እንዲህ ያለ ከባድ ውሳኔ ሲያደርግ በፈቃደኝነት ትተባበረው ይሆን?
ሣራን ያጋጠማት ሁኔታ እኛን እንደማያጋጥመን ይሰማን ይሆናል። ‘መቼም አምላክ እኔን ወይም ባለቤቴን እንዲህ ዓይነት ነገር እንድናደርግ ጠይቆን አያውቅም!’ ብለን እናስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ውሳኔ ማድረግ የሚጠይቅ ሁኔታ ሊያጋጥመን ይችላል። የምንኖርበት ዓለም ለቁሳዊ ነገሮች ከልክ ያለፈ ቦታ የሚሰጥ ዓለም ነው፤ እኛንም ቢሆን ለምቾታችን፣ ለንብረቶቻችን ወይም የተረጋጋ ሕይወት ለመኖር ቅድሚያ እንድንሰጥ ተጽዕኖ ሊያሳድርብን ይችላል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ የተለየ ውሳኔ እንድናደርግ ይኸውም ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ እንድንሰጥና ራሳችንን ከማስደሰት ይልቅ አምላክን ለማስደሰት ጥረት እንድናደርግ ያበረታታናል። (ማቴዎስ 6:33) ሣራ ባደረገችው ውሳኔ ላይ ስናሰላስል ‘እኔስ በሕይወቴ ውስጥ ምን ዓይነት ውሳኔዎችን አደርጋለሁ?’ ብለን ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን።
ከአገራቸው ወጡ
ሣራ ጓዟን በምትሸክፍበት ወቅት የቱን ይዛ የቱን እንደምትተው ግራ ሳይገባት አይቀርም። አህዮች ወይም ግመሎች ሊሸከሙት የማይችሉት ወይም ለዘላን ዓይነት ኑሮ የማይመች ትልቅ ዕቃ መያዝ አትችልም። በመሆኑም አብዛኞቹን ንብረቶቻቸውን መሸጥ ወይም ለሰው መስጠት እንደነበረባቸው ጥርጥር የለውም። ከዚህ በኋላ በከተማ ውስጥ ያለው ዓይነት የተመቻቸ ኑሮ አይኖራቸውም፤ እህል፣ ሥጋ፣ ፍራፍሬ፣ ልብስና ሌላ የሚያስፈልጋቸውን ነገር መግዛት የሚችሉበት ገበያ በቅርባቸው ማግኘት አይችሉም።
ሆኖም ሣራን ይበልጥ የከበዳት ቤቷን ትታ መሄዷ ሳይሆን አይቀርም። የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች በዑር የሚገኙ አንዳንድ
ቤቶች በርካታ ክፍሎች፣ ለመጠጥነት የሚያገለግል የውኃ ምንጭ እንዲሁም የቧንቧ መስመር እንደነበራቸው ይናገራሉ። አብርሃምና ሣራ ይኖሩበት የነበረውም ቤት እንዲህ ዓይነት ከነበረ ሣራ እንዲህ ያለውን ቤት ትቶ መሄድ መሥዋዕት መክፈል ጠይቆባት እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። እዚህ ግባ የማይባለው አነስተኛ ቤት እንኳ ጣሪያ፣ ግድግዳና መቀርቀሪያ ያለው በር ይኖረዋል። ታዲያ ከዚህ በኋላ የሚኖሩበት ድንኳን እንደ ቤት ሌቦች እንዳይገቡ ሊከላከል ይችላል? ደግሞስ በዚያ ዘመን በአካባቢው በብዛት ይገኙ ከነበሩት አንበሶች፣ ነብሮች፣ ድቦች ወይም ተኩላዎች ሊከላከል ይችላል?ሣራ ስለምትለያቸው ቤተሰቦቿስ ምን ማለት ይቻላል? አምላክ ‘ከአገራቸው ወጥተው፣ ከዘመዶቻቸውም ተለይተው እንዲሄዱ’ የሰጣቸው ትእዛዝ በተለይ ለሣራ ከባድ ሆኖባት መሆን አለበት። አፍቃሪ ሴት እንደመሆኗ መጠን በጣም የምትቀርባቸው ወንድሞች፣ እህቶች፣ የወንድምና የእህት ልጆች እንዲሁም አክስቶችና አጎቶች ይኖሯት ይሆናል፤ እነዚህን በሙሉ ዳግመኛ ላታያቸው ትችላለች። ቢሆንም፣ ሣራ ያላንዳች ማመንታት ለጉዞው ዝግጅት ማድረጓን ቀጠለች።
ሣራ ተፈታታኝ ሁኔታዎቹን በሙሉ በመቋቋም በታቀደው ዕለት ጓዟን ሸካክፋ ለጉዞ ተዘጋጀች። ታራ በወቅቱ ዕድሜው 200 ዓመት ገደማ ቢሆንም እንኳ የቤተሰብ ራስ እንደመሆኑ መጠን ከአብርሃምና ከሣራ ጋር አብሯቸው ተጓዘ። (ዘፍጥረት 11:31) ሣራ በዕድሜ የገፋውን አባቷን ለመንከባከብ ብዙ መልፋት ይጠበቅባት እንደነበር ጥርጥር የለውም። ይሖዋን በመታዘዝ ‘ከከለዳውያን አገር ሲወጡ’ ሎጥም አብሯቸው ተጉዟል።—የሐዋርያት ሥራ 7:4
በመጀመሪያ የኤፍራጥስን ወንዝ ተከትለው በስተ ሰሜን ምዕራብ 960 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቃ ወደምትገኘው ወደ ካራን ተጓዙ። ቤተሰቡ ለተወሰነ ጊዜ ያህል በካራን ኖረ። ምናልባትም በዚህ ወቅት ታራ በጣም ከመድከሙ የተነሳ ጉዞ መቀጠል አልቻለ ይሆናል። ታራ በ205 ዓመቱ እስኪሞት ድረስ በካራን ቆዩ። ጉዟቸውን ከመቀጠላቸው በፊት በዚያ እያሉ ይሖዋ በሆነ ወቅት ላይ ለአብርሃም ተገልጦለት ከዚያ ተነስቶ እሱ ወደሚያሳየው ምድር እንዲሄድ በድጋሚ ነገረው። ሆኖም በዚህ ወቅት አምላክ “ታላቅ ብሔር አደርግሃለሁ” በማለት አስደሳች ቃልም ገብቶለታል። (ዘፍጥረት 12:2-4) ከካራን በወጡበት ወቅት አብርሃም 75 ዓመቱ ሲሆን ሣራ ደግሞ 65 ዓመቷ ነበር፤ ሆኖም ልጅ አልነበራቸውም። ታዲያ አብርሃም ታላቅ ብሔር ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? ሌላ ሚስት ማግባት ያስፈልገው ይሆን? በወቅቱ ከአንድ በላይ ሚስት ማግባት የተለመደ ነገር ስለነበር ሣራ ይህን ጉዳይ አስባበት ሊሆን ይችላል።
ያም ሆነ ይህ፣ ካራንን ለቀው መጓዝ ጀመሩ። ሆኖም በዚህ ወቅት እነማን አብረዋቸው ይጓዙ እንደነበር ልብ በል። ዘገባው አብርሃምና ቤተሰቡ ያፈሩትን ንብረትና “በካራን አብረዋቸው የነበሩትን ሰዎች በሙሉ” ይዘው እንደሄዱ ይናገራል። (ዘፍጥረት 12:5) እነዚህ ሰዎች እነማን ናቸው? አገልጋዮቻቸው ሳይሆኑ አይቀሩም። ይሁንና አብርሃምና ሣራ ለመስማት ፈቃደኛ ለሆነ ሰው ሁሉ ስለ እምነታቸው ተናግረው እንደሚሆን አያጠራጥርም። በመሆኑም አይሁዶች ያዘጋጇቸው በዚህ ጥቅስ ላይ ትንታኔ የሚሰጡ አንዳንድ ጥንታዊ ጽሑፎች እዚህ ላይ የተጠቀሱት ሰዎች ከአብርሃምና ከሣራ ጋር አብረው ይሖዋን ማምለክ የጀመሩ ሰዎችን እንደሚያመለክቱ ይናገራሉ። እንደዚያ ከሆነ፣ ሣራ ያላት ጠንካራ እምነት ለሰዎች ስለ አምላኳና ስለተስፋዋ ስትናገር አሳማኝ በሆነ መንገድ እንድትናገር አድርጓት መሆን አለበት። የምንኖረው እምነትና ተስፋ በጠፋበት ዘመን እንደመሆኑ መጠን ሣራ በተወችው ምሳሌ ላይ ማሰላሰላችን ይጠቅመናል። ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማርከውን ነገር ለሌሎች ትናገራለህ?
‘ወደ ግብፅ ወረዱ’
ጊዜው ኒሳን 14, 1943 ዓ.ዓ. ሳይሆን አይቀርም፤ የኤፍራጥስን ወንዝ ከተሻገሩ በኋላ ይሖዋ እንደሚሰጣቸው ቃል ወደገባላቸው ምድር ለመሄድ ወደ ደቡብ አቀኑ። (ዘፀአት 12:40, 41) ሣራ በአካባቢው ውበትና ጥሩ የአየር ፀባይ ተማርካ ወዲያና ወዲህ ስታማትር በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። ሴኬም አካባቢ ወደሚገኙት የሞሬ ትላልቅ ዛፎች አቅራቢያ ሲደርሱ ይሖዋ በድጋሚ ለአብርሃም ተገልጦ “ይህችን ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ” አለው። “ዘር” የሚለው ቃል ለአብርሃም ትልቅ ትርጉም ያዘለ ነው! ይሖዋ አንድ ዘር ሰይጣንን እንደሚያጠፋ በኤደን ገነት የተናገረውን ትንቢት አስታውሶት መሆን አለበት። ይሖዋ ለአብርሃም ከእሱ የሚገኘው ብሔር፣ የምድር ሕዝቦች በሙሉ በረከት እንዲያገኙ መንገድ እንደሚከፍት ነግሮት ነበር።—ዘፍጥረት 3:15፤ 12:2, 3, 6, 7
ይሁንና ይህ ቤተሰብ በዓለም ላይ ካሉት ችግሮች ነፃ አልነበረም። በመሆኑም በከነአን ምድር ረሃብ ሲከሰት አብርሃም ቤተሰቡን ይዞ በስተ ደቡብ ወደሚገኘው ወደ ግብፅ ለመሄድ ወሰነ። ነገር ግን በዚያ አካባቢ አንድ ለየት ያለ ችግር ሊገጥመው እንደሚችል ተገንዝቦ ነበር። ስለዚህ ሣራን እንዲህ አላት፦ “እባክሽ ስሚኝ፤ አንቺ በጣም ውብ ሴት ነሽ። ስለሆነም ግብፃውያን አንቺን ሲያዩ ‘ይህች ሚስቱ ናት’ ማለታቸው አይቀርም። ከዚያም እኔን ይገድሉኛል፤ አንቺን ግን ይተዉሻል። በአንቺ የተነሳ መልካም እንዲሆንልኝ እባክሽ፣ እህቴ እንደሆንሽ አድርገሽ ተናገሪ፤ ዘፍጥረት 12:10-13) አብርሃም እንዲህ እንድታደርግ የጠየቃት ለምንድን ነው?
እንዲህ ካደረግሽ ሕይወቴ ይተርፋል።” (አብርሃም አንዳንድ ተቺዎች እንደሚሉት ውሸታምም ሆነ ፈሪ አልነበረም። ሣራ በእርግጥም ግማሽ እህቱ ነበረች። ደግሞም አብርሃም እንዲህ ዓይነት ጥንቃቄ ማድረጉ ተገቢ ነበር። አብርሃምና ሣራ፣ አምላክ በአብርሃም አማካኝነት ልዩ ዘርና ብሔር ለማስገኘት ያለው ዓላማ ከሁሉ የላቀ ቦታ የሚሰጠው ነገር እንደሆነ ተገንዝበው ነበር፤ በመሆኑም አብርሃም ደህንነቱ መጠበቁ በጣም አስፈላጊ ጉዳይ ነው። በተጨማሪም አርኪኦሎጂያዊ ግኝቶች እንደሚያሳዩት በወቅቱ በግብፅ የነበሩ ኃያል ሰዎች የአንድን ሰው ሚስት ጠልፈው በመውሰድ ባልየውን የመግደል ልማድ ነበራቸው። ስለዚህ አብርሃም ‘እህቱ ነኝ በይ’ ማለቱ የጥበብ እርምጃ ነው፤ ሣራም በትሕትና የባሏን ውሳኔ ደግፋለች።
ብዙም ሳይቆይ አብርሃም የፈራው ነገር ደረሰ፤ አንዳንድ የፈርዖን መኳንንት ሣራ ዕድሜዋ ቢገፋም እንኳ በጣም ውብ እንደሆነች ተመለከቱ። ከዚያም ስለ እሷ ለፈርዖን ነገሩት፤ እሱም ሣራን እንዲያመጧት አዘዘ! አብርሃም ምን ያህል ደንግጦ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም፤ ሣራም ብትሆን በጣም ፈርታ መሆን አለበት። ይሁንና ከዘገባው መረዳት እንደሚቻለው ሣራን የተቀበሏት እንደ እስረኛ ሳይሆን እንደተከበረ እንግዳ ነበር። ምናልባትም ፈርዖን እሷን በማግባባትና በሀብቱ በማስደመም “ከወንድሟ” ጋር ተነጋግሮ ሚስቱ ሊያደርጋት አስቦ ሊሆን ይችላል።—ዘፍጥረት 12:14-16
ሣራ በረንዳ ላይ ሆና ወይም በመስኮት በኩል የግብፅን መልክዓ ምድር ስትመለከት በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። ለረጅም ጊዜ በድንኳን ከኖረች በኋላ በሚያምር ቤት ውስጥ ሆና ጣፋጭ ምግቦች ሲቀርቡላት ምን ተሰምቷት ይሆን? በዑር ሳለችም እንኳ አይታው የማታውቀው እንዲህ ያለው የቅንጦት ሕይወት ፈተና ሆኖባት ይሆን? አብርሃምን ትታ የፈርዖን ሚስት ብትሆን ሰይጣን ምን ያህል እንደሚደሰት አስበው! ሣራ ግን እንዲህ ያለ ነገር አላደረገችም። ለባሏ፣ ለትዳሯና ለአምላኳ ታማኝ ነበረች። ሥነ ምግባር በጎደለው በዚህ ዓለም ውስጥ እያንዳንዱ ባለ ትዳር እንዲህ ዓይነቱን ታማኝነት ቢያሳይ ምንኛ መልካም ነበር! አንተስ ከቤተሰብህና ከጓደኞችህ ጋር ባለህ ግንኙነት ሣራ የተወችውን የታማኝነት ምሳሌ ትከተላለህ?
ይሖዋ በጉዳዩ ጣልቃ ገብቶ በፈርዖንና በቤተሰቡ ላይ መቅሰፍት በማምጣት ለሣራ ጥበቃ አደረገላት። ፈርዖን፣ ሣራ የአብርሃም ሚስት መሆኗን ሲረዳ ወደ ባሏ መለሳት፤ ከዚያም ቤተሰቡ በሙሉ ግብፅን ለቆ እንዲሄድ አደረገ። (ዘፍጥረት 12:17-20) አብርሃም ውድ ባለቤቱን መልሶ ሲያገኝ ምንኛ ተደስቶ ይሆን! ሣራን “አንቺ በጣም ውብ ሴት ነሽ” ብሏት እንደነበር አስታውስ። ሆኖም አብርሃም ከውጫዊ ውበቷ ይበልጥ ያደነቀው ውስጣዊ ውበቷን ነበር። ሣራ፣ ይሖዋ ከፍ አድርጎ የሚመለከተው ዓይነት እውነተኛ ውስጣዊ ውበት ነበራት። (1 ጴጥሮስ 3:1-5) እንዲህ ዓይነቱን ውበት ሁላችንም ማዳበር እንችላለን። ከቁሳዊ ነገሮች ይልቅ ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ ከሰጠን፣ ስለ አምላክ ያለንን እውቀት ለሌሎች ለማካፈል ጥረት ካደረግን እንዲሁም ፈተና ቢያጋጥመንም እንኳ የይሖዋን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ካከበርን ሣራ የተወችውን የእምነት ምሳሌ መከተል እንችላለን።
^ አን.3 መጀመሪያ ላይ አብራምና ሦራ በመባል ይጠሩ ነበር፤ ነገር ግን ይበልጥ የሚታወቁት በኋላ ላይ ይሖዋ ባወጣላቸው አብርሃምና ሣራ በሚለው ስማቸው ነው።—ዘፍጥረት 17:5, 15
^ አን.8 ሣራ ለአብርሃም ግማሽ እህቱ ነበረች። ሁለቱም የታራ ልጆች ነበሩ፤ ሆኖም የአንድ እናት ልጆች አልነበሩም። (ዘፍጥረት 20:12) በዛሬው ጊዜ እንዲህ ያሉ የቅርብ ዘመዳሞች መጋባታቸው ተገቢ አይደለም፤ ነገር ግን በወቅቱ የነበረው ሁኔታ ከአሁኑ ይለይ እንደነበር ማስታወስ ያስፈልጋል። አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከሠሩ በኋላ እነሱም ሆኑ ዘሮቻቸው ፍጽምናን ያጡ ቢሆንም በዚያ ዘመን የነበሩ ሰዎች ከአሁኑ በተሻለ ለፍጽምና የቀረቡ ነበሩ። ሰዎች ጠንካራና ጤናማ ስለነበሩ የቅርብ ዘመዳሞች ቢጋቡም እንኳ ልጆቹ በዚህ ምክንያት የሚመጣ የጤና ችግር አይገጥማቸውም ነበር። ከ400 ዓመታት ገደማ በኋላ ግን የሰዎች የዕድሜ ርዝማኔ በእኛ ዘመን ካሉ ሰዎች ዕድሜ ጋር ተመሳሳይ ሆኖ ነበር። በዚያ ጊዜ የሙሴ ሕግ የቅርብ ዘመዳሞች የፆታ ግንኙነት መፈጸም እንደሌለባቸው ደነገገ።—ዘሌዋውያን 18:6