በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የምታደርጉት መዋጮ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው እንዴት ነው?

“ለብሔራት ሁሉ ምሥክር” የሚሆኑ የጽሑፍ ጋሪዎች

“ለብሔራት ሁሉ ምሥክር” የሚሆኑ የጽሑፍ ጋሪዎች

ሚያዝያ 1, 2023

 የጽሑፍ ጋሪዎች፣ ባለፉት አሥር ዓመታት ለአገልግሎታችን መስህብ ሆነው ቆይተዋል። እነዚህ ጋሪዎች በዓለም ዙሪያ መታወቂያችን ሆነዋል። ዲዛይናቸው ማራኪ ብቻ ሳይሆን ለአጠቃቀምም ምቹ ነው። አሰናታ የተባለች የፖላንድ እህት የተናገረችው ነገር የብዙዎችን ስሜት ይገልጻል ብለን እናምናለን፤ እንዲህ ብላለች፦ “የጋሪዎቹ ዲዛይን ቀላልና ያልተወሳሰበ ነው፤ ሆኖም ለእይታ ማራኪ ነው። ጋሪዎቹን አንድ ቦታ ላይ ማቆምም ሆነ ከቦታ ቦታ ማንቀሳቀስ ምቹ ነው።”

 የእነዚህ ጋሪዎች ዲዛይን የወጣውና የተመረቱት እንዴት እንደሆነ ማወቅ ትፈልጋለህ?

ግሩም ዲዛይን

 በ2001 በበላይ አካሉ ፈቃድ የፈረንሳይ ወንድሞችና እህቶች የተለያዩ የአደባባይ ምሥክርነት ዘዴዎችን መሞከር ጀመሩ፤ ከእነዚህ መካከል የጽሑፍ ጋሪዎች ይገኙበታል። የተለያዩ ዲዛይኖች ተሞክረዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በተጎታች ሻንጣዎችና በሱፐር ማርኬት ጋሪዎች ላይ የተወሰነ ማሻሻያ በማድረግ ጽሑፎቻችንን ለማስተዋወቅና ለማስቀመጥ የሚያስችል ጋሪ ለመሥራት ሞክረዋል። መጨረሻ ላይ የፈረንሳይ ቅርንጫፍ ቢሮ አንድ ዲዛይን መረጠ፤ አስፋፊዎች ለበርካታ ዓመታት በዚህ ዲዛይን የተሠራውን ጋሪ ሲጠቀሙበት ቆይተዋል።

የቀድሞ የጽሑፍ ጋሪ፣ ፈረንሳይ፣ 2005

 የፈረንሳይ ወንድሞች በአደባባይ ምሥክርነት ጥረታቸው ያገኙት ውጤት አመርቂ ነበር። በመሆኑም በ2011 የበላይ አካሉ ይህ የአደባባይ ምሥክርነት ኒው ዮርክ ሲቲ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በሙከራ ደረጃ እንዲጀመር ፈቃድ ሰጠ፤ በፕሮግራሙ የተካፈሉት አቅኚዎች ጋሪዎችና ጠረጴዛዎች ይጠቀሙ ነበር። በኋላ ላይ እንዳስተዋሉት ግን ጋሪዎቹ በብዙ አቅጣጫዎች የተሻለ ጠቀሜታ አላቸው፤ አንደኛው ጥቅሙ፣ ከቦታ ቦታ ለማንቀሳቀስ ምቹ መሆኑ ነው። አቅኚዎቹ የጋሪዎቹን ዲዛይን ለማሻሻል ሌሎች ተጨማሪ ሐሳቦችም አቀረቡ። መጀመሪያ ላይ የነበሩት የእንጨት ጋሪዎች ከባድ ነበሩ፤ እነሱን ይዞ ደረጃ መውጣትና መውረድ አስቸጋሪ ነበር። ስለዚህ ቀለል እንዲሉ የዲዛይን ማሻሻያ ተደረገባቸው፤ በሌላ በኩል ግን ነፋስ የሚወስዳቸው ያህል እስኪሆኑ ድረስ ቀላል መሆን የለባቸውም። አዲሱ ዲዛይን ሰፋ ያሉና በቀላሉ የማይጎዱ ጎማዎችንም ያካተተ ነው፤ ይህም ወጣ ገባ መንገድ ላይ ጋሪዎቹን ለማጓጓዝ ያስችላል። በተጨማሪም ትርፍ ጽሑፎች ለመያዝ የሚያስችል አነስተኛ ሣጥን ተገጠመላቸው።

 የሙከራ ፕሮግራሙ የተሳካ ነበር! በመሆኑም የበላይ አካሉ በ2012 የጽሑፍ ጋሪዎቹ በዓለም ዙሪያ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ፈቃድ ሰጠ። ቀላል ክብደት ያላቸው ሆኖም ቻይ የሆኑ ጥሬ ዕቃዎችን ተጠቅሞ ጋሪዎቹን በብዛት እንዲያመርትልን ከአንድ ድርጅት ጋር ተዋዋልን።

 በቀጣዮቹ ዓመታት በጋሪዎቹ ላይ አነስተኛ ማሻሻያዎች ስናደርግ ቆይተናል። ለምሳሌ ያህል፣ በ2015 ከፊት ለፊት ጽሑፎቹን የሚያሳይ ፕላስቲክ ያለው የዝናብ መከለያ ተሠራ። በጆርጂያ የምትኖረው ዲና ይህ መደረጉ አስደስቷታል። “አሁን ጋሪው ‘የዝናብ ጃኬት’ ስላለው ጽሑፎቻችን አይበላሹም” ብላለች። በ2017 ደግሞ በአንዳንድ ቋንቋዎች በማግኔት የሚለጠፉ ፖስተሮች ይዘጋጁ ጀመር። በፖላንድ የሚኖረው ቶማሽ እንዲህ ብሏል፦ “ቀደም ሲል ፖስተሮቹን አንስቶ መለጠፍ ቀላል ሥራ አልነበረም። አሁን በማግኔት ከሆኑ በኋላ ግን ሥራችን ቀልሎልናል።” በ2019 ጋሪዎቹ ይበልጥ ረዘም ላለ ጊዜ ማገልገል እንዲችሉ በጥሬ ዕቃዎቹም ሆነ በምርት ሂደቱ ላይ ተጨማሪ ማሻሻያዎች ተደርገዋል።

የጽሑፍ ጋሪዎችን ማምረት

 የጽሑፍ ጋሪዎቹን የሚያመርትልን ድርጅት አንድ ነው፤ ከዚያም በዓለም ዙሪያ ይሰራጫሉ። በአሁኑ ወቅት አንድ ጋሪ 43 የአሜሪካ ዶላር ያወጣል፤ ይህም ማጓጓዣና ሌሎች ወጪዎችን ሳይጨምር ነው። እስካሁን ድረስ እነዚህን ጋሪዎች ለመግዛት ከ16 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ አውጥተናል፤ ከ420,000 በላይ የሚሆኑ ጋሪዎችን በዓለም ዙሪያ ላሉ ጉባኤዎች አሰራጭተናል።

 በመዋጮ የተገኘውን ገንዘብ በአግባቡ ለመጠቀም ሲባል የጽሑፍ ጋሪዎችን የምናዘው በብዛት ነው። በተጨማሪም ጉባኤዎች ጋሪ ሲበላሽባቸው በአዲስ መተካት አያስፈልጋቸውም፤ ምክንያቱም አሁን መለዋወጫዎችን አዘው የተበላሸውን መጠገን ይችላሉ።

ጋሪ ተጠቅሞ መመሥከር

 በዓለም ዙሪያ ያሉ አስፋፊዎች፣ ምሥክርነት መስጫ ጋሪዎቹን በጣም ወደዋቸዋል። ማርቲና ከጋና እንዲህ ብላለች፦ “በአብዛኞቹ የአገልግሎት ዘርፎች ወደ ሰዎቹ የምንሄደው እኛ ነን። በጋሪ መመሥከር የሚያስደስተኝ አንዱ ነገር ግን ሰዎቹ ናቸው ወደ እኛ የሚመጡት። ጋሪውን አልፎ የሚሄድ ሰውም እንኳ ምሥክርነት ይሰጠዋል።”

 በሌላ አፍሪካ አገር ያጋጠመውን ደግሞ እንመልከት፤ አንድ ሰው ወደ ጋሪው መጣና በራሱ ቋንቋ ጽሑፍ ወሰደ። ከሳምንት በኋላ ተመልሶ መጣና ወንድሞችን እንዲህ አላቸው፦ “ሁሉንም ጽሑፎች አንብቤያቸዋለሁ። ወሳኝ መረጃ ነው የያዙት። ገጠር ወዳሉ ቤተሰቦቼ ሄጄ ጽሑፎቹን ልሰጣቸው እፈልጋለሁ።” ቤተሰቦቹ የሚገኙት 500 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀው ነው። ከሁለት ወር በኋላ ተመልሶ መጥቶ ወንድሞችን እንዲህ አላቸው፦ “በመንደራችን ያሉ ሰዎች በሙሉ ጽሑፎቹን አንብበዋቸዋል፤ በያዙት መረጃም በጣም ተደስተዋል። የይሖዋ ምሥክሮች መሆን ይፈልጋሉ። ግን አንዳንድ ጥያቄዎች አሏቸው። ለምሳሌ ጥምቀት የሚደረገው ውኃ ውስጥ በመጥለቅ እንደሆነ ገብቷቸዋል፤ ሆኖም እኛ መንደር አካባቢ ወንዝ የለም። ታዲያ ለመጠመቅ የግድ እዚህ መምጣት አለብን ማለት ነው?” ወንድሞች ይህን ሰው የእሱን ቋንቋ ከሚናገር አቅኚ ጋር አገናኙት። አሁን በቋሚነት ውይይት እያደረጉ ነው።

 የጽሑፍ ጋሪዎች “የመንግሥቱ ምሥራች ለብሔራት ሁሉ ምሥክር እንዲሆን” እያደረጉት ያለውን አስተዋጽኦ መመልከት በእርግጥም አስደሳች ነው። (ማቴዎስ 24:14) ታዲያ የምርት ወጪያቸው የሚሸፈነው እንዴት ነው? ለዓለም አቀፉ ሥራ በሚደረገው መዋጮ አማካኝነት ነው፤ ብዙዎች ይህን መዋጮ የሚያደርጉት donate.dan124.com​ን ተጠቅመው ነው። ለልግስናችሁ ከልብ እናመሰግናለን!