መልካም በማድረግ ብቸኝነትን ማስታገስ—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
በዓለም ዙሪያ፣ ብዙ ሰዎች ብቸኛ እንደሆኑና ፈላጊ እንደሌላቸው ይሰማቸዋል። ለእንዲህ ዓይነቱ ስሜት አንዱ መድኃኒት ለሌሎች መልካም ማድረግ እንደሆነ አንዳንድ የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ።
“የተቸገሩትን መርዳት፣ ሕይወት ትርጉም ያለው እንዲሆን ያደርጋል፤ የብቸኝነትና የመገለል ስሜትን ለማስታገስም ይረዳል።”—የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የጤና ተቋም
መጽሐፍ ቅዱስ ሌሎችን መርዳት የምንችልባቸውን መንገዶች ይጠቁመናል። ምክሩን ተግባራዊ ማድረጋችን ብቸኝነትን ለማሸነፍ ይረዳናል።
ምን ማድረግ ትችላለህ?
ለጋስ ሁን። ከሰዎች ጋር ተገናኝተህ ለመጨዋወት አጋጣሚ ፈልግ፤ በተለይ ደግሞ በአካል ቢሆን ይመረጣል። ያለህን አካፍል። እንዲህ ማድረግህ ምስጋናቸውን እንዲገልጹ ያነሳሳቸዋል፤ ይህም ወዳጅነታችሁን ያጠናክረዋል።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ለሰዎች ስጡ፤ እነሱም ይሰጧችኋል።”—ሉቃስ 6:38
በችግራቸው ድረስላቸው። አስጨናቂ ሁኔታ ያጋጠማቸውን ሰዎች መርዳት የምትችልበትን መንገድ ፈልግ። ለምሳሌ፣ ከልብህ አዳምጣቸው፤ ወይም በአንዳንድ ሥራዎች በማገዝ ሸክማቸውን አቅልልላቸው።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ወዳጆች . . . በችግር ጊዜ [ይረዳዳሉ]።”—ምሳሌ 17:17 የ1980 ትርጉም
ማኅበራዊ ግንኙነትህን ለማሻሻል የሚረዱ ተጨማሪ ሐሳቦች ማግኘት ከፈለግህ “የቤተሰብ ሕይወትና ጓደኝነት” የሚለውን ርዕስ አንብብ።