ነቅታችሁ ጠብቁ!
አርማጌዶን የሚጀምረው እስራኤል ውስጥ ነው?—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው አርማጌዶን አካባቢያዊ ግጭት ሳይሆን ሁሉም ሰብዓዊ መንግሥታት ከአምላክ ጋር የሚዋጉበት ዓለም አቀፋዊ ጦርነት ነው።
“በአጋንንት መንፈስ የተነገሩ ቃላት . . . ሁሉን ቻይ በሆነው አምላክ ታላቅ ቀን ወደሚካሄደው ጦርነት ሊሰበስቧቸው ወደ ዓለም ነገሥታት ሁሉ ይወጣሉ። . . . እነሱም ነገሥታቱን በዕብራይስጥ አርማጌዶን ወደሚባል ስፍራ ሰበሰቧቸው።”—ራእይ 16:14, 16
“አርማጌዶን” የሚለው ቃል ሐርማጌዶን ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል የተገኘ ሲሆን “የመጊዶ ተራራ” የሚል ትርጉም አለው። መጊዶ በጥንቷ እስራኤል ውስጥ የምትገኝ ከተማ ነበረች። በዚህም ምክንያት አንዳንድ ሰዎች የአርማጌዶን ጦርነት የሚካሄደው እስራኤል ውስጥ እንደሆነ ያምናሉ። ይሁንና በመጊዶ ተራራ ላይም ሆነ በመካከለኛው ምሥራቅ በሚገኝ በሌላ በማንኛውም አካባቢ ‘የዓለም ነገሥታት ሁሉ’ ከነሠራዊታቸው ሊሰበሰቡ አይችሉም።
የራእይ መጽሐፍ የተጻፈው “በምልክቶች” ወይም በምሳሌያዊ አገላለጽ ነው። (ራእይ 1:1) በመሆኑም አርማጌዶን የሚያመለክተው ቃል በቃል አንድን ቦታ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ መንግሥታት በሙሉ በአንድነት ሆነው የአምላክን አገዛዝ ለመጨረሻ ጊዜ የሚቃወሙበትን ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ያመለክታል።—ራእይ 19:11-16, 19-21