ነቅታችሁ ጠብቁ!
ከባድ ድርቅ—መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
“ቻይና በዚህ ዓመት እጅግ ሞቃታማውንና እስካሁን ከተመዘገቡት ሁሉ በድርቀቱ ሦስተኛ የሆነውን ወቅት አስመዝግባለች።”—ዘ ጋርዲያን፣ መስከረም 7, 2022
“በአፍሪካ ቀንድ ያለው ድርቅ ለአምስተኛ ዓመት እንደሚቀጥል ይጠበቃል።”—የተመድ ዜና፣ ነሐሴ 26, 2022
“ሁለት ሦስተኛ የሚሆነው የአውሮፓ ክፍል በድርቅ የመጠቃት አደጋ ተደቅኖበታል፤ ይህ ድርቅ ባለፉት 500 ዓመታት ከተከሰቱት ድርቆች የከፋው እንደሚሆን ይጠበቃል።”—BBC ዜና፣ ነሐሴ 23, 2022
በርካታ ባለሙያዎች እንዲህ ያለው ድርቅ መከሰቱን እንደሚቀጥልና እየተባባሰ እንደሚሄድ ይጠብቃሉ። ታዲያ የተሻለ ጊዜ ይመጣ ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
ድርቅ እና የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት
ድርቅ እየተባባሰ የመጣው ለምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ፣ ድርቅ እየተባባሰ የመጣበትን ዋነኛ ምክንያት ይናገራል። እንዲህ ይላል፦
“ሰው . . . አካሄዱን እንኳ በራሱ አቃንቶ መምራት አይችልም።”—ኤርምያስ 10:23
ሰዎች ‘አካሄዳቸውን አቃንተው መምራት’ ማለትም ራሳቸውን በተሳካ ሁኔታ ማስተዳደር አይችሉም። የሚያደርጓቸው መጥፎ ውሳኔዎች ብዙውን ጊዜ ለድርቅና ለውኃ እጥረት መንስኤ ይሆናሉ።
የሰው ልጆች የሚያደርጉት ነገር ለዓለም ሙቀት መጨመር መንስኤ እንደሆነና በዓለም ዙሪያ ድርቅ እየተባባሰ እንዲሄድ እንዳደረገ በርካታ ሳይንቲስቶች ይስማማሉ።
የሰዎች ስግብግብነት እንዲሁም አርቆ አሳቢነት የማይንጸባረቅባቸው ፖሊሲዎች ለደን መመንጠር፣ ለብክለት እንዲሁም ለተፈጥሮ ሀብት መመናመን ምክንያት ሆነዋል፤ እነዚህ ነገሮች ደግሞ የውኃ አካላትን አደጋ ላይ ይጥላሉ።
ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ይሰጠናል።
ወደፊት የተሻለ ጊዜ ይመጣ ይሆን?
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ በአሁኑ ጊዜ ያለውን የውኃ እጥረት እንደሚያስወግድ ይናገራል። ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው?
1. አምላክ ‘ምድርን እያጠፉ ያሉትን ያጠፋል።’ (ራእይ 11:18) የአካባቢ ብክለት የሚፈጥሩትን ክፉና ስግብግብ ሰዎች በማጥፋት ለውኃ እጥረት መንስኤ የሆነውን አንዱን ችግር ያስወግዳል።—2 ጢሞቴዎስ 3:1, 2
2. “በሐሩር የተቃጠለው ምድር ቄጠማ የሞላበት ኩሬ . . . ይሆናል።” (ኢሳይያስ 35:1, 6, 7) አምላክ ድርቅ ያስከተለውን ጉዳት በመቀልበስ ምድራችንን ውኃ የጠገበች ገነት ያደርጋታል።
3. “ምድርን እጅግ ፍሬያማ በማድረግና በማበልጸግ ትንከባከባታለህ።” (መዝሙር 65:9) በአምላክ በረከት፣ ምድር ገንቢ ምግብና ንጹሕ ውኃ የሚትረፈረፍባት ቦታ ትሆናለች።