ክርስቲያናዊ ሕይወት
አምላክን ስማ የተባለውን ብሮሹር መጠቀም የሚቻልበት መንገድ
አምላክን ስማ የተባለው ብሮሹር የተዘጋጀው በደንብ ማንበብ የማይችሉ ሰዎች ሥዕሎችን በማየት መሠረታዊ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን እንዲያውቁ ለመርዳት ታስቦ ነው። ሁለት ገጽ የሚይዘው እያንዳንዱ ትምህርት በጥንቃቄ ታስቦባቸው የተዘጋጁ ሥዕሎችን ይዟል፤ ከሥዕሎቹ አጠገብ የሚገኙት ቀስቶች በሥዕሎቹ ላይ የምትወያዩበትን ቅደም ተከተል ይጠቁሟችኋል።
አምላክን ስማ የዘላለም ሕይወት ታገኛለህ የተባለው ብሮሹር አምላክን ስማ ከተባለው ብሮሹር ጋር ተመሳሳይ ሥዕሎች ቢኖሩትም ተጨማሪ ጽሑፍ አለው፤ በመሆኑም የተሻለ የማንበብ ችሎታ ያላቸውን ጥናቶች ለማስጠናት ልንጠቀምበት እንችላለን። አንዳንድ አስፋፊዎች ጥናት በሚመሩበት ወቅት፣ ጥናታቸው አምላክን ስማ የተባለውን ብሮሹር እነሱ ደግሞ አምላክን ስማ የዘላለም ሕይወት ታገኛለህ የተባለውን ብሮሹር መጠቀማቸው የተሻለ እንደሆነ አስተውለዋል። በአብዛኞቹ ገጾች ላይ የተማሪውን ችሎታ ግምት ውስጥ በማስገባት ልትወያዩባቸው የምትችሉ ተጨማሪ መረጃ የያዙ ሣጥኖች ይገኛሉ።
በወሩ ውስጥ የሚበረከተው ጽሑፍ ሌላ ቢሆንም እንኳ እነዚህን ብሮሹሮች ልታበረክቱ ትችላላችሁ። ጥናት ስትመሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን ለማብራራት በሥዕላዊ መግለጫዎቹ ተጠቀሙ። ተማሪው በጥናቱ ወቅት ተሳትፎ እንዲያደርግ ለማበረታታት እንዲሁም ትምህርቱ ገብቶት እንደሆነ ለማወቅ ጥያቄዎችን ጠይቁ። በእያንዳንዱ ገጽ ግርጌ ላይ ያሉትን ጥቅሶች አንብባችሁ ተወያዩባቸው። ተማሪው ብሮሹሩን አጥንቶ ሲጨርስ ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? ወይም መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምረናል? የተባለውን መጽሐፍ መቀጠል ትችላላችሁ፤ ይህም ተማሪው እድገት አድርጎ እንዲጠመቅ ይረዳዋል።