በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ከግራ ወደ ቀኝ፦ አሌክሲ ቡደንቹክ፣ ኮንስታንቲን ባዤኖቭ፣ ፊሊክስ ማክሃማዲየቭ፣ አሌክሲ ሚረትስኪ፣ ሮማን ግሪዳሶቭ እና ጀናዲ ጀርመን ከመታሰራቸው በፊት

የካቲት 17, 2020
ሩሲያ

በኦረንበርግ፣ ሩሲያ የእስር ቤት ጠባቂዎች አምስት ወንድሞችን ደበደቡ

በኦረንበርግ፣ ሩሲያ የእስር ቤት ጠባቂዎች አምስት ወንድሞችን ደበደቡ

በኦረንበርግ፣ ሩሲያ የሚገኝ የአንድ እስር ቤት ጠባቂዎች የካቲት 6, 2020 አሌክሲ ቡደንቹክ፣ ጀናዲ ጀርመን፣ ሮማን ግሪዳሶቭ፣ ፊሊክስ ማክሃማዲየቭ እና አሌክሲ ሚረትስኪ የተባሉ አምስት ወንድሞቻችንን በዱላ ክፉኛ ደብድበዋቸዋል። ወንድም ማክሃማዲየቭ የጎድን አጥንቱ ተሰብሮ፣ ሳንባው ተቀድዶና ኩላሊቱ ላይ ጉዳት ደርሶበት ሆስፒታል ገብቷል። ወንድም ቡደንቹክ፣ ወንድም ጀርመን፣ ወንድም ግሪዳሶቭ እና ወንድም ሚረትስኪ ደግሞ ከተደበደቡ በኋላ በሐሰት ተከሰው ለቅጣት የተዘጋጀ ክፍል ውስጥ እንዲገቡ ተደርጓል። ከሐሰት ክሶቹ መካከል አንዱ ሲጋራ አጭሰዋል የሚል ነው፤ ሆኖም በይሖዋ ምሥክሮች እምነት መሠረት ሲጋራ ማጨስ አይፈቀድም።

ቀደም ሲል እንደተዘገበው በሳራቶቭ የሚገኘው የሌኒንስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት ዳኛ የሆኑት ዲሚትሪ ላሪን መስከረም 19, 2019 በአምስት ወንድሞቻችን ላይ እስራት ፈርደዋል፤ ኮንስታንቲን ባዤኖቭ የተባለ ስድስተኛ ወንድምም እስራት ተፈርዶበታል። እነዚህ ወንድሞች ከሁለት ዓመት አንስቶ እስከ ሦስት ዓመት ተኩል የሚደርስ እስራት ተፈርዶባቸው ነበር። ታኅሣሥ 20, 2019 የሳራቶቭ የክልል ፍርድ ቤት የይግባኝ ጥያቄያቸውን ውድቅ አደረገ። ከተወሰኑ ሳምንታት በኋላ ስድስቱም ወንድሞች እስር ቤት ገቡ። ወንድም ባዤኖቭ የታሰረው በኡልያኖቭስክ ክልል በሚገኝ እስር ቤት ውስጥ ስለነበረ ከተደበደቡት ወንድሞች መካከል አልነበረም።

አምስቱ ወንድሞች የካቲት 6, 2020 እስር ቤት እንደደረሱ ተደበደቡ። ሐኪሞች ምርመራ እንዲያደርጉላቸው የተፈቀደው በቀጣዩ ቀን ማለትም ወንድም ማክሃማዲየቭ ኃይለኛ ትኩሳት እንዳለውና ሽንቱ ደም የቀላቀለ እንደነበር ሲታወቅ ነው። የእስር ቤቱ አስተዳዳሪ አምቡላንስ የጠራው ወንድም ማክሃማዲየቭ “መታጠቢያ ቤት ውስጥ አዳልጦት እንደወደቀ” የሚገልጽ ሰነድ ላይ እንዲፈርም ካስገደደው በኋላ ነው። ወንድም ማክሃማዲየቭ ሳንባው ውስጥ የተጠራቀመውን ፈሳሽ ለማስወገድ ቀዶ ጥገና ተደረገለት። ምርመራው ወንድም ማክሃማዲየቭ በረሃብ እንደተጠቃም አሳይቷል፤ ይህ የሆነው ላለበት ሕመም ተብሎ የመጣለትን የተለየ ምግብ እንዳያገኝ የእስር ቤቱ ባለሥልጣናት ስለከለከሉት ነው።

ወንድሞቻችን እንዲህ ያለ የግፍና የጭካኔ ድርጊት እየደረሰባቸው በመሆኑ በጣም እናዝናለን። ሆኖም በታማኝነት እንዲጸኑ ይሖዋ እንደሚረዳቸው እንተማመናለን።—ፊልጵስዩስ 1:27, 28