ኅዳር 1, 2021 | የታደሰው፦ የካቲት 7, 2024
ሩሲያ
ወቅታዊ መረጃ—ወንድም ታሰረ | ወንድም ዲሚትሪ ባርማኪን ለረጅም ጊዜ በማረፊያ ቤት ቢቆይም ደስታውን ጠብቋል
የካቲት 6, 2024 በቭላዲቮስቶክ የሚገኘው የፕሪሞርይስ ክልላዊ ፍርድ ቤት፣ ወንድም ዲሚትሪ ባርማኪን የተሻረለትን የቀድሞ ብይን አጽንቶታል፤ የተላለፈበት የስምንት ዓመት እስራት ተፈጻሚ እንዲሆን ወስኗል። ዲሚትሪ ከፍርድ ቤት ወዲያውኑ ወደ ወህኒ ተወስዷል።
ነሐሴ 8, 2023 የፕሪሞርይስ ክልላዊ ፍርድ ቤት፣ ወንድም ዲሚትሪ ባርማኪን ያቀረበውን ይግባኝ ተቀብሎታል፤ ጥፋተኛ ነው የሚለውን ብይንም ሽሮታል። ዲሚትሪ ወዲያውኑ ከወህኒ ተፈትቷል። ሆኖም ክሱ ወደ አቃቤ ሕጉ የተመለሰ ሲሆን ለሦስተኛ ጊዜ ይታያል።
ሚያዝያ 27, 2023 በቭላዲቮስቶክ፣ ፕሪሞርይስ ክልል የሚገኘው የፐርቮርቸንስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት፣ ዲሚትሪ ጥፋተኛ ነው የሚል ብይን አስተላልፏል፤ የስምንት ዓመት እስራትም ፈርዶበታል። ከፍርድ ቤት ወዲያውኑ ወደ ወህኒ ተወስዷል።
ሚያዝያ 8, 2022 የፕሪሞርይስ ክልላዊ ፍርድ ቤት፣ ዲሚትሪ ጥፋተኛ አይደለም በሚል የተላለፈውን ውሳኔ ቀልብሷል። ክሱ በድጋሚ ይታያል።
የክሱ ሂደት
ኅዳር 22, 2021 በቭላዲቮስቶክ፣ ፕሪሞርይስ ክልል የሚገኘው የፐርቮርቸንስኪ አውራጃ ፍርድ ቤት ዲሚትሪ ጥፋተኛ አይደለም የሚል ውሳኔ አስተላልፏል፤ በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ፣ ወንድም ዲሚትሪን ከቀረበበት የወንጀል ክስ ሙሉ በሙሉ ነፃ አድርጎታል። ፍርድ ቤቱ፣ በሩሲያ የወንጀለኛ መቅጫ አንቀጽ 282.2(1) [የጽንፈኛ ድርጅትን እንቅስቃሴ ማደራጀትን የሚመለከት ሕግ ነው] የተከሰሰን አንድ የይሖዋ ምሥክር አስመልክቶ ጥፋተኛ አይደለም የሚል ውሳኔ ሲያስተላልፍ ይህ የመጀመሪያ ጊዜ ነው። ፍርድ ቤቱ በወንድም እንቅስቃሴዎች ላይ የተጣሉትን ገደቦችም ያነሳል። የአቃቤ ሕግ ቢሮ ይግባኝ ካልጠየቀ፣ ውሳኔው ታኅሣሥ 3, 2021 ተግባራዊ ይሆናል።
ሚያዝያ 20, 2021
ጉዳዩ በድጋሚ መታየት ጀመረ
ታኅሣሥ 18, 2020
የወንጀል ክሱ በማስረጃ እጥረት ምክንያት ወደ አቃቤ ሕጉ ተመለሰ። ሆኖም በእንቅስቃሴዎቹ ላይ በተጣለው ገደብ ላይ ለውጥ አልተደረገም
ጥቅምት 18, 2019
ከ447 ቀናት በኋላ ዲሚትሪ ከማረፊያ ቤት ተለቀቀ፤ ሆኖም በእንቅስቃሴዎቹ ላይ ጥብቅ ገደብ ተጣለበት። ፍርድ ቤቱ የዲሚትሪን የማረፊያ ቤት ቆይታ አሥር ጊዜ አራዝሞታል
ሐምሌ 28, 2018
ሐምሌ 28, 2018 ከጠዋቱ 1:00 ላይ መሣሪያ የታጠቁና ጭምብል ያጠለቁ ሰዎች ዲሚትሪና የሌና ወዳሉበት ቤት ሰብረው ገቡ፤ በወቅቱ ዲሚትሪና የሌና፣ የ90 ዓመት አዛውንት የሆኑትን የየሌናን አያት ለመንከባከብ እሳቸው ቤት ነበሩ። ዲሚትሪና የሌና 177 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኘው የመኖሪያ ከተማቸው ወደ ቭላዲቮስቶክ ተወሰዱ። ዲሚትሪ ወዲያውኑ በቁጥጥር ሥር ውሎ ማረፊያ ቤት እንዲገባ ተደረገ
ሐምሌ 27, 2018
በወንድም ዲሚትሪ ባርማኪን ላይ የወንጀል ክስ ተመሠረተ
ጥቅምት 2017
ለፌዴራል ደህንነት ቢሮ የምትሠራ አንዲት የ30 ዓመት ሴት ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ማወቅ የምትፈልግ መስላ ቀረበች። ከተለያዩ ወንድሞችና እህቶች ጋር ያደረገችውን ውይይት በድብቅ ቀረጸች።
አጭር መግለጫ
ዲሚትሪ እና የሌና በእስር ምክንያት ድጋሚ ሊለያዩ ቢችሉም እነዚህ ባልና ሚስት ‘የይሖዋን ደስታ ምሽጋቸው በማድረግ’ ግሩም ምሳሌ ትተዋል።—ነህምያ 8:10