መጋቢት 18, 2021
ሩሲያ
ወቅታዊ መረጃ—ይግባኙ ውድቅ ተደረገ | በሩሲያ ሩቅ ምሥራቃዊ ክፍል የሚኖሩ ሁለት ወንድሞች በእምነታቸው የተነሳ እስከ 12 ዓመት የሚደርስ እስራት ሊፈረድባቸው ይችላል
ጥቅምት 18, 2022 ዘጠነኛው ጠቅላይ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ወንድም ዩሪ ቤሎስሉድትስዬቭ እና ወንድም ሰርጌ ሰርጌዬቭ ለሁለተኛ ጊዜ ያቀረቡትን ይግባኝ ውድቅ አደረገ። እርግጥ አሁን ወህኒ አይወርዱም።
ሚያዝያ 21, 2022 የፕሪሞርይስ ክልላዊ ፍርድ ቤት ዩሪ እና ሰርጌ ያቀረቡትን ይግባኝ ውድቅ አደረገ።
ጥር 31, 2022 በፕሪሞርይስ ክልል የሚገኘው የፖዣርስኪይ አውራጃ ፍርድ ቤት ዩሪ እና ሰርጌ ጥፋተኛ ናቸው የሚል ብይን አስተላለፈ። ሁለቱም ወንድሞች የስድስት ዓመት የገደብ እስራት ተፈርዶባቸዋል።
አጭር መግለጫ
ዩሪ ቤሎስሉድትስዬቭ
የትውልድ ዘመን፦ 1964 (ስሚዶቪች፣ የአይሁዳውያን ራስ ገዝ ክልል)
ግለ ታሪክ፦ ያሳደጉት አያቱ ሲሆኑ ያደገው በትንሽ መንደር ውስጥ ነው። በኃይል ማሰራጫ ድርጅት ውስጥ መሐንዲስ ሆኖ ሠርቷል። ዓሣ ማጥመድና በረዶ ላይ መንሸራተት ይወዳል
በ1985 ከየሌና ጋር ትዳር መሠረተ። ሁለቱም አምላክ ክፋትንና መከራን እንደሚያስወግድ በገባው ቃል ልባቸው ተነካ። ሁለቱም የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች መፈጸማቸው በጣም አስገረማቸው። እነዚህን እውነቶች ማወቃቸው መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት አነሳሳቸው። በ1994 ተጠመቁ
ሰርጌ ሰርጌዬቭ
የትውልድ ዘመን፦ 1955 (ዱሆቭኒትስኮዬ፣ ሳራቶቭ ክልል)
ግለ ታሪክ፦ ጡረታ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ በድንጋይ ከሰል ማውጫ ውስጥ ሠርቷል። ከኔሊ ጋር በ1991 ትዳር መሠረተ። ሁለት ሴቶች ልጆችና አንድ ወንድ ልጅ አፍርተዋል። ባልና ሚስቱ ውሾች ይወዳሉ
ከተጋቡ ብዙም ሳይቆይ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመሩ። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ማግኘታቸውና መጽሐፍ ቅዱስ የያዘው ጠቃሚ ምክር ልባቸውን ነካው። በ1996 ተጠመቁ
የክሱ ሂደት
መጋቢት 17, 2019 የፌዴራል ደህንነት አባላት በሉችዬጎርስክ፣ ፕሪሞርይስ ክልል የጅምላ ፍተሻ አካሄዱ። ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የወንጀል ምርመራ ተደረገባቸው፤ አንዳንዶቹን ለሰባት ሰዓታት ያህል ፖሊሶች በጥያቄ አፋጠዋቸዋል። ዩሪና ሰርጌ በቁጥጥር ሥር ዋሉ።
ከሁለት ቀን በኋላ ሁለቱም ወንድሞች ወደ ማረፊያ ቤት ተወሰዱ፤ በዚያም ከስድስት ወር በላይ ቆይተዋል። መስከረም 2019 ከማረፊያ ቤት ከወጡ በኋላ ለአምስት ወራት ያህል በቁም እስር ቆይተዋል።
ሁለቱም በማረፊያ ቤት የነበረውን አስከፊ ሁኔታ ለመቋቋም የረዳቸው ጸሎት መሆኑን ገልጸዋል። ሰርጌ መጽሐፍ ቅዱስም አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝ እንደረዳው ተናግሯል። እንዲህ ብሏል፦ “ኢየሱስ ‘እኔን ስደት አድርሰውብኝ ከሆነ እናንተንም ስደት ያደርሱባችኋል’ ያለው ትዝ አለኝ። (ዮሐንስ 15:20) በዚህ ጊዜ ‘የሚገርም ነው! በእኛ ላይ የደረሰው ነገር በኢየሱስ ክርስቶስ፣ በደቀ መዛሙርቱና በሐዋርያቱ ላይም ደርሷል። ይሖዋ እዚህ ጥሩ ምሥክርነት መስጠት እንደምችል ይሰማዋል ማለት ነው’ ብዬ አሰብኩ። እንዲህ ያሉ ነገሮችን ማሰቤና ይሖዋ ጸሎቴን ሲመልስልኝ መመልከቴ አበረታቶኛል እንዲሁም ደስተኛ እንድሆን ረድቶኛል።”
ዩሪ ቀደም ሲል መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበብ ይቸገር እንደነበር ገልጿል። ሆኖም አንድ ወንድም በዚህ ረገድ ማሻሻያ እንዲያደርግ ረዳው። ይህ ልማድ ማረፊያ ቤት በነበረበት ጊዜ በእጅጉ ጠቅሞታል። እንዲህ ብሏል፦ “ቀደም ሲል ያጠናኋቸውን በመጽሐፍ ቅዱስና በጽሑፎቻችን ውስጥ ያሉ ምሳሌዎች አስታውስ ነበር። ይህም ብርታት ሰጥቶኛል፤ እንዲሁም ደስተኛ እንድሆን ረድቶኛል። በተጨማሪም ከልክ በላይ እንዳልጨነቅ ረድቶኛል።”
ይሖዋ በሩሲያ ለሚኖሩ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ‘በጭንቅ ጊዜ መጠጊያቸውና ብርታታቸው’ እንደሚሆንላቸው በመተማመን እንጸልይላቸዋለን።—መዝሙር 46:1