በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ሩስታም ሴድኩሌቭና ባለቤቱ ዩሊያ ሚያዝያ 7, 2023 ከእስር በተፈታበት ጊዜ

ጥቅምት 19, 2023
ሩሲያ

ወንድም ሩስታም ሴድኩሌቭ ከሩሲያ እስር ቤት ተፈትቶ ወደ ቱርክሜኒስታን ተላከ

ወንድም ሩስታም ሴድኩሌቭ ከሩሲያ እስር ቤት ተፈትቶ ወደ ቱርክሜኒስታን ተላከ

ሚያዝያ 7, 2023 ወንድም ሩስታም ሴድኩሌቭ ከሩሲያ እስር ቤት ተፈታ። መንግሥት የሩሲያ ዜግነቱን የነጠቀውሲሆን ከተወሰኑ ወራት ቆይታ በኋላ መስከረም 17, 2023 ወደ ቱርክሜኒስታን ልኮታል። ባለቤቱ ዩሊያ በቅርቡ አብራው እንደምትሆን ተስፋ ታደርጋለች።

ሩስታም ከ7 ወራት ለሚበልጥ ጊዜ በቁም እስረኛነት ወደ 23 ወራት ለሚጠጋ ጊዜ ደግሞ ወህኒ ቤት አሳልፏል። በዚህ ሁሉ ጊዜ ውስጥ አዎንታዊ አመለካከቱንና በይሖዋ ላይ ያለውን ጠንካራ እምነት ጠብቆ ቆይቷል። ሩስታም እስር ቤት ሳለ በጻፈው አንድ ደብዳቤ ላይ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሱ ምሳሌዎች እንዲጸና የረዱት እንዴት እንደሆነ ሲገልጽ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “የናቡቴና የሜፊቦስቴ ምሳሌነት በጣም አበረታቶኛል። ኢፍትሐዊ በሆነ መንገድ ቢከሰሱም ታማኝነታቸውን እና እምነታቸውን ጠብቀዋል። ይህም ያለሁበትን ሁኔታ መቋቋም እንድችልና በወደፊት ተስፋዬ ላይ እንዳተኩር ረድቶኛል።”

ሩስታም ወህኒ በነበረበት ጊዜ ዩሊያ እንድትጎበኘው የተፈቀደላት በሦስት ወር አንድ ጊዜ ብቻ ነበር። ሆኖም በየቀኑ በስልክ በመደዋወል እርስ በርስ ይበረታቱ እንዲሁም ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር ከተባለው ቡክሌት ላይ የዕለቱን ጥቅስ አብረው ያነብቡ ነበር።

ሩስታም እስር ቤት ከመግባቱ ጥቂት ቀደም ብሎ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ይሖዋ ሁሉንም ነገር እንደሚከታተልና እኛን ለመንከባከብ በተገቢው ጊዜና መንገድ እጁን እንደሚዘረጋ ተመልክቻለሁ። ስለዚህ በእሱ ሙሉ በሙሉ መመካቴን መቀጠሌ የግድ አስፈላጊ ነው።”

ሩስታም እና ዩሊያ ይሖዋን መጠጊያቸውና መሸሸጊያቸው ማድረጋቸውን ሲቀጥሉ የእሱ እንክብካቤ እንደማይለያቸው እርግጠኞች ነን።—መዝሙር 91:2