ኅዳር 20, 2020
ሩሲያ
ወንድም ሰርጌ ለደንዮቭ ሩሲያ ውስጥ የስድስት ዓመት እስራት ሊፈረድበት ይችላል
የፍርድ ውሳኔ የሚሰጥበት ቀን
ኅዳር 24, 2020 a በካምቻትካ ክልል የሚገኘው የፔትሮፓቭሎቭስክ-ካምቻትስኪ ከተማ ፍርድ ቤት ከወንድም ሰርጌ ለደንዮቭ ጋር በተያያዘ በተመሠረተው ክስ ላይ ውሳኔውን እንደሚያሳውቅ ይጠበቃል። ወንድም ሰርጌ የስድስት ዓመት እስር ሊፈረድበት ይችላል።
አጭር መግለጫ
ሰርጌ ለደንዮቭ
የትውልድ ዘመን፦ 1974 (ኦሶራ፣ ካምቻትካ ክልል)
ግለ ታሪክ፦ ለወላጆቹ ከስድስት ልጆች መካከል አንዱ ነው። ሥዕል መሣልና ፎቶ ማንሳት ይወዳል። በግንባታ መስክ ጡብ የመደርደርና ታይል የማነጠፍ ሥራ ይሠራል። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት ከመጀመሩ በፊት መጽሐፍ ቅዱስ ከሳይንስ ጋር የሚጋጭና ጊዜ ያለፈበት መጽሐፍ እንደሆነ ይሰማው ነበር። በ2017 ባለቤቱን አናን አገባ። ሰርጌ የመጽሐፍ ቅዱስን ምክሮች በሕይወቱ ውስጥ ተግባራዊ ማድረጉ ታጋሽ፣ አሳቢና አፍቃሪ ባል እንዲሆን እንደረዳው አና ትናገራለች
የክሱ ሂደት
ታኅሣሥ 2, 2018 የታጠቁና ጭንብል የለበሱ ፖሊሶች በፔትሮፓቭሎቭስክ-ካምቻትስኪ የሚገኘውን የወንድም ለደንዮቭን መኖሪያ ሰብረው ገቡ። ከዚያም ወንድም ለደንዮቭን የያዙት ሲሆን በሩሲያ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቀጽ 282.2 መሠረት ከሰሱት። የክስ ሂደቱ ኅዳር 28, 2019 ጀመረ።
በካምቻትካ ክልል የሚገኘው የፔትሮፓቭሎቭስክ-ካምቻትስኪ ከተማ ፍርድ ቤት ታኅሣሥ 12, 2019 ላይ ክሱን ወደ አቃቤ ሕግ መለሰው። አብዛኛውን ጊዜ ፍርድ ቤቱ እንዲህ የሚያደርገው ከተመሠረተው ክስ ጋር በተያያዘ ከባድ ችግር ሲያገኝ ለምሳሌ በቂ ማስረጃ ሳይኖር ሲቀር ነው። ሆኖም የካቲት 4, 2020 ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔውን በመቀልበስ የክስ ሂደቱ እንዲቀጥል አደረገ። ይህን ተከትሎ ክሱ በተሰማበት ዕለት ባለሥልጣናቱ የወንድም ለደንዮቭ ባለቤትና ሌላ እህት በወንድም ለደንዮቭ ላይ በሐሰት እንዲመሠክሩ ለማስገደድ ሞክረው ነበር። ሆኖም ሁለቱም እህቶች በሐሰት ለመመሥከር ፈቃደኛ አልሆኑም።
የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ የወንድም ለደንዮቭ ዘመዶች፣ ወንድም ለደንዮቭ በእምነቱ ምክንያት ይህን ያህል ስደት እየደረሰበት ያለው ለምን እንደሆነ መረዳት ከብዷቸዋል።
ወንድም ለደንዮቭና ባለቤቱ ውሳኔውን እየተጠባበቁ ባሉበት በዚህ ጊዜ በጸሎት እናስባቸዋለን። የይሖዋ መንፈስ በእነሱ ላይ እንደሚያርፍ እርግጠኞች ነን።—1 ጴጥሮስ 4:14
a ቀኑ ሊቀየር ይችላል።.