በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በሞስኮ ክልል የሚገኘው የቼኮቭ ከተማ ፍርድ ቤት

ግንቦት 21, 2021
ሩሲያ

ወንድም ክሩትያኮቭና ባለቤቱ እንዲሁም ወንድም ኒኪፎሮቭ እና ወንድም ዠረብትሶቭ በፈተና ወቅት በይሖዋ ታምነዋል

ወንድም ክሩትያኮቭና ባለቤቱ እንዲሁም ወንድም ኒኪፎሮቭ እና ወንድም ዠረብትሶቭ በፈተና ወቅት በይሖዋ ታምነዋል

ወቅታዊ መረጃ | የሩሲያ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ሁለተኛውን ይግባኝ ውድቅ አደረገ

ጥር 13, 2022 የመጀመሪያ ደረጃ አጠቃላይ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ወንድም ዩሪ ክሩትያኮቭና ባለቤቱ ዚናይዳ እንዲሁም ወንድም ቪታሊ ኒኪፎሮቭ እና ወንድም ኮንስታንቲን ዠረብትሶቭ ያቀረቡትን ሁለተኛ ይግባኝ ውድቅ አደረገ። እርግጥ አሁን ወህኒ አይወርዱም።

ሐምሌ 20, 2021 የሞስኮ ክልላዊ ፍርድ ቤት በዩሪ፣ በዚናይዳ፣ በቪታሊ እና በኮንስታንቲን ላይ ቀደም ሲል የተበየነባቸው የገደብ እስራት እንዲጸና ወስኗል።

ግንቦት 24, 2021 በሞስኮ ክልል የሚገኘው የቼኮቭ ከተማ ፍርድ ቤት ዩሪ፣ ዚናይዳ፣ ቪታሊ እና ኮንስታንቲን ጥፋተኛ ናቸው የሚል ውሳኔ አስተላልፏል። ፍርድ ቤቱ በዩሪ ላይ የስድስት ዓመት የገደብ እስር በይኗል። ዚናይዳ፣ ቪታሊ እና ኮንስታንቲን ደግሞ የሁለት ዓመት የገደብ እስራት ተፈርዶባቸዋል።

አጭር መግለጫ

ዩሪ ክሩትያኮቭ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1952 (ኒዥኒ፣ ኖቭጎሮድ)

  • ግለ ታሪክ፦ የኢንዱስትሪያል እና የሲቪል መሐንዲስ ነው። ንድፍ አውጪ እና ፎርማን ሆኖ ሠርቷል። ለበርካታ ዓመታት የሕይወትን ትርጉም ሲፈልግ ቆይቷል። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ሲያጠና ለጥያቄዎቹ መልስ አገኘ። በ1998 ተጠመቀ

    በ2012 ከዚናይዳ ጋር ትዳር መሠረተ። ባልና ሚስቱ ምግብ ማብሰልና ሙዚቃ ማዳመጥ ይወዳሉ

ዚናይዳ ክሩትያኮቫ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1958 (ኒዥኔዴቪትስክ)

  • ግለ ታሪክ፦ ሴት ልጇን ያሳደገችው ብቻዋን ነው። መሐንዲስ ነበረች፤ በዋነኝነት የሠራችው በሴራሚክና ሙቀት በሚቋቋሙ ቁሳቁሶች ምርት ላይ ነው። አሁን ጡረታ ወጥታለች

    በዓለም ላይ በሚታየው የፍትሕ መጓደል የተነሳ ግራ ትጋባ ነበር። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ስታጠና አጥጋቢ መልስ አገኘች። በ2003 ተጠመቀች። በ2012 ከዩሪ ጋር ትዳር መሠረተች

ቪታሊ ኒኪፎሮቭ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1968 (ኔቬል፣ ፐስኮቭ ክልል)

  • ግለ ታሪክ፦ በልጅነቱ ሒሳብ ጎበዝ ነበር፤ እንዲሁም ስፖርት ይወድ ነበር። በሩሲያ አየር ኃይል ውስጥ የአውሮፕላን ቴክኒሺያን ሆኖ ሠርቷል

    በ2005 ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። በ2007 ከጦር ሠራዊቱ ጡረታ ወጣ። በ2012 ተጠመቀ

ኮንስታንቲን ዠረብትሶቭ

  • የትውልድ ዘመን፦ 1973 (ቱርክሜኒስታን)

  • ግለ ታሪክ፦ በወጣትነቱ ክብደት ማንሳትና ቴምብር መሰብሰብ ይወድ ነበር። ከቴክኒክ ትምህርት ቤት የተመረቀ ሲሆን የኤሌክትሪክ ባለሙያ ሆኖ ሠርቷል። ከ2003 ወዲህ ለኑክሌር የኃይል ጣቢያዎች የሚሆኑ ማሽኖች በሚያመርት ፋብሪካ ውስጥ ሠርቷል

    በ1994 ከናታልያ ጋር ትዳር መሠረተ። ሁለቱም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን አጠኑ። በ2016 ተጠመቁ

የክሱ ሂደት

መስከረም 30, 2019 በሞስኮ ክልል የሚገኘው የሩሲያ ምርመራ ኮሚቴ በወንድም ቪታሊ ኒኪፎሮቭ፣ በወንድም ኮንስታንቲን ዠረብትሶቭ፣ በወንድም ዩሪ ክሩትያኮቭ እና በባለቤቱ በእህት ዚናይዳ ክሩትያኮቫ ላይ የወንጀል ክስ መሠረተ። ከሁለት ቀናት በኋላ ባለሥልጣናቱ የሁሉንም ቤት በረበሩ።

ቪታሊ፣ ኮንስታንቲን እና ዚናይዳ ለረጅም ሰዓት ምርመራ ከተደረገባቸው በኋላ ሌሊቱን ማረፊያ ቤት ቆዩ። ከዚያም በቁም እስር እንዲቆዩ ተደረገ።

መጋቢት 5, 2020 ዩሪ ማረፊያ ቤት ተወሰደ። ከዚያ ወዲህ ወደ ሦስት የተለያዩ ማረፊያ ቤቶች ተወስዷል። አሁንም በማረፊያ ቤት ይገኛል።

ኮንስታንቲን የደረሰበትን ፈተና ለመቋቋም የረዳው ጸሎት እንደሆነ ገልጿል። ቤቱ በተፈተሸበት ምሽት ይሖዋ ጭንቀቱን ለመቋቋም እንዲረዳው ጸልዮ ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “እኔና ቤተሰቤ ባለሥልጣናቱን በእርጋታና በአክብሮት መያዛችን ምሥክርነት ሰጥቷል፤ የአምላክ ሕዝቦች ሰላማዊ እና ሕግ አክባሪ እንደሆኑ ማየት ችለዋል።”

ኮንስታንቲን አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ሁኔታው ከባድ ሲሆንብኝ በዘካርያስ 2:8 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ያበረታታኛል፤ እንዲሁም ያጠነክረኛል። ይሖዋ እንደሚያስብልኝና ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተኝ ያስታውሰኛል፤ እንደ ዓይኑ ብሌን እንደሚጠብቀኝ ማረጋገጫ ሰጥቶኛል።”

ሦስቱ ወንድሞቻችን እና ውድ እህታችን ሸክማቸውን በይሖዋ ላይ ጥለዋል፤ ይሖዋም እነሱን መደገፉን እንደሚቀጥል እርግጠኞች ነን።—መዝሙር 55:22