በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ዬጎር ባራኖቭ እና እህት ዳርያ ዱሎቫ

መስከረም 8, 2020
ሩሲያ

ወጣቶቹ ወንድም ባራኖቭ እና እህት ዱሎቫ እምነትና ድፍረት አሳይተዋል

ወጣቶቹ ወንድም ባራኖቭ እና እህት ዱሎቫ እምነትና ድፍረት አሳይተዋል

ወንድም ዬጎር ባራኖቭ እና እህት ዳርያ ዱሎቫ የተባሉት በሩሲያ የሚኖሩ ውድ ወጣቶቻችን በወንጀል ሊፈረድባቸውና ለረጅም ጊዜ ሊታሰሩ እንደሚችሉ ቢያውቁም በድፍረት ጸንተዋል። በአሁኑ ወቅት ከፍርድ በፊት ታስሮ የሚገኘው ወንድም ባራኖቭ ገና የ19 ዓመት ወጣት ነው። እህት ዱሎቫ ደግሞ ፖሊሶች ቤቷን በበረበሩበት ወቅት ገና 18 ዓመቷ ነበር። ሩሲያ ውስጥ በእምነታቸው ምክንያት የወንጀል ክስ ከተመሠረተባቸው ከ380 የሚበልጡ ወንድሞችና እህቶች መካከል በዕድሜ ትናንሾቹ እነሱ ናቸው።

ወንድም ባራኖቭ ከግንቦት 27, 2020 አንስቶ በእስር ላይ ይገኛል። እህት ዱሎቫ ደግሞ ከሁለት የተለያዩ ክሶች ጋር በተያያዘ ፍርድ ቤት የሚያሳልፈውን ውሳኔ እየተጠባበቀች ነው። እነዚህ ወጣቶች ብዙ ፈተናዎች ቢያጋጥሟቸውም ለይሖዋ ታማኝ ለመሆን ቆርጠዋል።

መሣሪያ የታጠቁ የፌደራል ደህንነት አባላት ግንቦት 27 ወንድም ባራኖቭና እናቱ የሚኖሩበትን ቤት በረበሩ። በኋላም አሌክሲ ሻቲሎቭ የተባሉት ዳኛ ወንድማችን በአካባቢው ካሉ የይሖዋ ምሥክሮች “መሪዎች መካከል አንዱ” እንደሆነ በመግለጽ ከፍርድ በፊት በእስር እንዲቆይ አዘዙ።

ወንድም ባራኖቭ እንደገለጸው አስፈሪ በሆነው ብርበራ ወቅት መረጋጋት የቻለው ወደ ይሖዋ ከጸለየ በኋላ ነው። እንዲህ ብሏል፦ “ከፈታሾቹ መካከል አንዱ መረጋጋቴን አይቶ ‘ስትጠብቀን የነበረ ይመስላል’ አለኝ።”

ወንድም ባራኖቭ “ይሖዋ ይህ ሁኔታ እንዲደርስብኝ ከፈቀደ በጽናት ልወጣው እችላለሁ ማለት ነው” በማለት ሁልጊዜ እንደሚያስብ ገልጿል። አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ እንዲረዳኝና መንፈስ ቅዱስን እንዲሰጠኝ ሳላሰልስ መጸለዬ እንዳልፈራ ረድቶኛል። በተጨማሪም ወንጀለኛ እንዳልሆንኩ በእርግጠኝነት አውቃለሁ። ሕሊናዬ ንጹሕ ነው፤ ስደት የደረሰብኝ በእምነቴ የተነሳ ነው።”

ወንድም ባራኖቭ እስር ቤት ውስጥ ምንም ስጋት እንደማይሰማው ገልጿል። የታሰረው ዓመፀኛ ካልሆኑ እስረኞች ጋር እንደሆነና እስረኞቹ በአክብሮት እንደሚይዙት ብሎም እንደ ታናሽ ወንድማቸው እንደሚቆጥሩት ተናግሯል። “ለመታሰር የሚያበቃ ምንም ነገር እንዳልሠራሁ ያውቃሉ” ብሏል።

ነሐሴ 1, 2018 ፖሊሶች እህት ዱሎቫና እናቷ የሚኖሩበትን ቤት በረበሩ። እህት ዱሎቫ ቤቷ መበርበሩና መታሰሯ ስሜቷን ቢረብሸውም እምነቷ ጽኑ እንደሆነ ገልጻለች። እንዲህ ብላለች፦ “ምንጊዜም ለይሖዋ ታማኝ ለመሆን ቆርጫለሁ። ምንም ይምጣ ምን እስከ መጨረሻው ይሖዋን አገለግላለሁ።”

ከእህት ዱሎቫ ጋር በተያያዘ የተመሠረተው ክስ በስቬርድሎቭስክ ክልል በሚገኘው የካርፒንስኪ ከተማ ፍርድ ቤት መስከረም 2019 መታየት ጀመረ። ፍርድ ቤት በቀረበችበት ወቅት ሰዎች የሚያስደስታቸውን ነገር ለሌሎች መናገራቸው የተለመደ ነገር እንደሆነ ገልጻ ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “ለምሳሌ አምላክ በቅርቡ ምድርን ገነት እንደሚያደርጋት አውቃለሁ፤ ያን ጊዜ የሚኖረን የደስታ እንባ ብቻ ነው። ታዲያ ይህን አስደሳች ነገር ማወቄ ለጎረቤቶቼ ለመናገር ሊያነሳሳኝ አይገባም?”

እህት ዱሎቫ ይህን አሳማኝ መከራከሪያ በድፍረት ብታቀርብም ጥር 27, 2020 ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ እንደሆነች በየነ። የአንድ ዓመት እስር በገደብ ተፈረደባት። ከዚያም ጠበቃዋ ይግባኝ ጠየቀ።

ነሐሴ 6, 2020 የስቬርድሎቭስክ የክልል ፍርድ ቤት በእህት ዱሎቫ ላይ የተላለፈውን ፍርድ ቀለበሰ። ክሱ በሌላ ዳኛ እንዲታይ ወደ ካርፒንስኪ ከተማ ፍርድ ቤት ተመለሰ። ጉዳዩ የሚታይበት ቀን ገና አልተወሰነም። የዚህን ክስ ውጤት እየተጠባበቀች ባለችበት በዚህ ወቅት በእሷ፣ በእናቷና በሌሎች ሦስት ወንድሞች ላይ ሌላ የወንጀል ምርመራ እየተካሄደ ነው።

ወንድም ባራኖቭና እህት ዱሎቫ ከደረሰባቸው ፈተና ብዙ ትምህርት አግኝተዋል።

እህት ዱሎቫ ምን እንደረዳት ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ፣ ለጉባኤ ስብሰባዎች በመዘጋጀትና የመንግሥት መዝሙሮቻችንን በመማር መንፈሳዊነታችሁን አጠናክሩ። ጭንቀታችሁንና ፍርሃታችሁን እንድታሸንፉ በሚረዷችሁ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይ አሰላስሉ።”

ወንድም ባራኖቭ ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “እንዲህ ያለውን ሁኔታ በጽናት ለመቋቋም ከአምላክ ጋር የጠበቀ ዝምድና መመሥረት ያስፈልጋል። ጊዜያችሁን አታባክኑ። ከይሖዋ ጋር ያላችሁን ወዳጅነት ከአሁኑ አጠናክሩ።”

ይሖዋ ታማኝ ወጣቶችን ደፋር እንዲሆኑ እንደሚረዳቸው የሚያሳዩ በርካታ ምሳሌዎችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እናገኛለን። በሩሲያ ውስጥም ሆነ በሌሎች የዓለም ክፍሎች ስደት እየደረሰባቸው ያሉ ወጣቶችን መደገፉን እንደሚቀጥል እንተማመናለን።—1 ሳሙኤል 1:20፤ 16:18፤ 2 ነገሥት 5:1-3፤ ዳንኤል 1:14-17፤ 3:17-27