የካቲት 7, 2023
ስሪ ላንካ
በሲንሃላ ቋንቋ ጽሑፎች ማተም ከጀመርን ሰባ አምስት ዓመታት ተቆጠሩ
የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ወደ ሲንሃላ ቋንቋ መተርጎም ከጀመሩ 2023 ላይ 75 ዓመት ሆኗቸዋል፤ ሲንሃላ፣ ስሪ ላንካ ውስጥ አብላጫ ተናጋሪ ያለው ቋንቋ ነው።
ስሪ ላንካ በቅኝ ግዛት ሥር በነበረችበት ወቅት የአገሪቱ የሥራ ቋንቋ እንግሊዝኛ ነበር፤ በመሆኑም መጀመሪያ ላይ ጽሑፎቻችን የሚገኙት በእንግሊዝኛ ብቻ ነበር። በ1948 ግን የመጀመሪያው የሲንሃላ ጽሑፍ ወጣ፤ ጽሑፉ የሕዝቦች ሁሉ ደስታ የተሰኘው ቡክሌት ነው። ቡክሌቱ በወጣ በዓመቱ የስሪ ላንካ የአስፋፊዎች ቁጥር ከ12 ተነስቶ 25 ደረሰ።
በ1953 በአዲሱ ዓለም ለማመን የሚያበቃ መሠረት የተሰኘው ቡክሌትና ነፃ የሚያወጣው እውነት የተባለው መጽሐፍ በሲንሃላ ወጣ። ከዚያም በጥቂት ዓመታት ውስጥ ብቻ የትርጉም ሥራው ወደ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋገረ፤ መጋቢት 1958 መጠበቂያ ግንብ ለመጀመሪያ ጊዜ በሲንሃላ ወጣ።
በሲንሃላ ቋንቋ የሚከናወነው የትርጉም ሥራ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ የደረሰው በ2009 ነው። የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ስቲቨን ሌት በዚህ ዓመት ስሪ ላንካን ጎበኘ፤ ከዚያም አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ በሲንሃላ መውጣቱን አበሰረ።
መጽሐፍ ቅዱስ መውጣቱ በተበሰረበት ዕለት ፕሮግራሙን የታደመ አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “አዲስ ዓለም ትርጉም በሲንሃላ ቋንቋ እጄ ሲገባ ልቤ ለታላቁ አስተማሪ ለይሖዋ ባለኝ አድናቆት ተሞላ። ይህ ትርጉም ለማንበብም ሆነ ለመረዳት ቀላል ነው፤ ይህም ትምህርቱን በሕይወቴ ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ የምችልበትን መንገድ ማስተዋል ቀላል እንዲሆንልኝ አድርጓል።”
ይሖዋ በሲንሃላ በሚመሩ 63 ጉባኤዎች ውስጥ የሚያገለግሉ 4,839 አስፋፊዎችንም ሆነ በስሪ ላንካ ያሉትን 7,121 አስፋፊዎች እየባረከ እንዳለ ግልጽ ነው። ‘ንጹሑን ቋንቋ’ ለመናገርም ሆነ ለማስተማር ጥረት ሲያደርጉ የይሖዋ በረከት እንደማይለያቸው እርግጠኞች ነን።—ሶፎንያስ 3:9