መጋቢት 29, 2022
ቆጵሮስ
ከ1922-2022:- የቆጵሮስ የ100 ዓመት ክርስቲያናዊ ታሪክ
የይሖዋ ምሥክሮች የሜድትራንያን ደሴት በሆነችው በቆጵሮስ መስበክ ከጀመሩ 2022 ላይ 100 ዓመት ሞልቷቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያው የሚስዮናዊ ጉዞው ላይ የቆጵሮስ ተወላጅ ከሆነው ከበርናባስ ጋር ደሴቲቱን ጎብኝቶ ነበር። በዘመናችን የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ዘር የተዘራው ደግሞ በ1922 አንድ ቄስ ነፍስ ትሞታለች? የሚል ቡክሌት በተቀበለበት ጊዜ ነበር።
ከሁለት ዓመት በኋላ ሳይረስ ቻራላምቦስ የተባለ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ከዩናይትድ ስቴትስ ወደ ቆጵሮስ ተመለሰ። በዚያም በቅንዓት መስበክ የጀመረ ከመሆኑም ሌላ ቆጵሮስ ውስጥ ላለ ለእያንዳንዱ ከተማና መንደር ሙታን የት ናቸው? የሚለውን ትራክት በፖስታ ላከ።
ትራክቱ ወደ አንቶኒስ ስፔትሲዮቴስ እጅ ደረሰ። አንቶኒስ ያነበበው ነገር በጣም ስላስደነቀው ከጎረቤቱ ከአንድሬያስ ክሪስቶ ጋር ተወያየበት። በኋላም አንቶኒስ እና አንድሬያስ ያገኙትን እውቀት ለሌሎች መናገር ጀመሩ።
የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን፣ አንቶኒስ እና አንድሬያስ ለመስበክ ያደረጉትን ሙከራ ተቃወመች፤ ሁለቱም ከቤተ ክርስቲያኒቷ ተገለሉ። ያም ቢሆን መስበካቸውን አላቆሙም። እነሱ ያከናወኑት ሥራ በ1930ዎቹ በደሴቲቱ ላይ ክሲሎፋጉ በተባለች መንደር ውስጥ የመጀመሪያው ጉባኤ እንዲቋቋም አድርጓል።
በጊልያድ የሠለጠነው የመጀመሪያው ሚስዮናዊ የሆነው አንቶኒዮስ ካራንዲኖስ በ1947 ሲመጣ ሥራው ይበልጥ ተቀጣጠለ። በ1948 ደሴቲቱ ላይ በቅንዓት የሚሰብኩ 50 አስፋፊዎች ነበሩ፤ የመጀመሪያው ቅርንጫፍ ቢሮም ተቋቋመ። በ1960 ወንድሞች ሕጋዊ ማኅበር መሠረቱ። ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ የመጀመሪያው የስብሰባ አዳራሽ በኒኮሲያ ተገነባ። የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር እያደገ ሄደ፤ እንዲሁም ተለቅ ያለ አዲስ የቤቴል ሕንፃ በ1969 ተወሰነ።
እድገቱን ተከትሎ ግን ከባድ ስደት መጣ። በ1960ዎቹ አጋማሽ ላይ ወጣት ወንድሞች በውትድርና ለመካፈል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት ወህኒ ይወርዱ ጀመር። በዚህ ጊዜ አንዳንዶቹ ወጣቶች በጦር ሠራዊቱ ዘግናኝ ግፍ ተፈጽሞባቸዋል፤ ይህ የሆነው አቋማቸውን እንዲያላሉ ለማድረግ ሲባል ነው።
በ1974 በደሴቲቱ ላይ ጦርነት በተከሰተበት ጊዜ ሌላ ፈተና መጣ። ወደ 300 ገደማ የሚሆኑ ወንድሞቻችን አካባቢውን ለቀው ለመሰደድ ተገደዱ። የቤቴል ቤተሰብም ከቅርንጫፍ ቢሮው መውጣት ነበረበት። ሆኖም የወንድማማች ማኅበራችን በቆጵሮስ ለሚኖሩ ወንድሞቻችን የእርዳታ ቁሳቁሶች በመላክ ደርሶላቸዋል። ሁኔታቸው የሚፈቅድላቸው ወንድሞች የተሰደዱ የእምነት አጋሮቻቸውን በቤታቸው አስተናግደዋል።
በቀጣዮቹ ዓመታት የስብከቱ ሥራ ማበቡን ቀጠለ። በ2006 ሊማሶል ውስጥ “መዳናችን ቀርቧል!” የተባለው የአውራጃ ስብሰባ በተደረገበት ወቅት ደግሞ ታሪክ ተሠራ! ቆጵሮስ ውስጥ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች በሙሉ ከብዙ ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ላይ መሰብሰብ ቻሉ።
በአሁኑ ጊዜ ደሴቲቱ ላይ በ41 ጉባኤዎችና በ17 ቡድኖች ውስጥ በ14 ቋንቋዎች የሚያገለግሉ 2,866 አስፋፊዎች አሉ። በ2021 በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ላይ 5,588 ሰዎች ተገኝተው ነበር።
በቆጵሮስ ያሉ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ደስታ እንጋራለን። በይሖዋ እርዳታ በዚሁ ግሩም መንገድ መመላለሳቸውን እንደሚቀጥሉ እርግጠኞች ነን።—ፊልጵስዩስ 3:16