በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ሚያዝያ 20, 2022
ቤልጅየም

የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ከግብር ጋር በተያያዘ በቀረበው አቤቱታ በቤልጅየም ለሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ፈረደ

የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ከግብር ጋር በተያያዘ በቀረበው አቤቱታ በቤልጅየም ለሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ፈረደ

የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት (ECHR) የቤልጅየም መንግሥት በብራስልስ-ካፒታል አካባቢ ያሉ ዘጠኝ ጉባኤዎች ቀደም ሲል ተሰጥቷቸው የነበረውን ከንብረት ግብር ነፃ የመሆን መብት ማንሳቱ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ አድልዎ እንደፈጸመ የሚያሳይ መሆኑን በአንድ ድምፅ ወሰነ። ከሳሽ የይሖዋ ምሥክሮች ክርስቲያናዊ ማኅበርና ሌሎች፣ ተከሳሽ ቤልጅየም በተሰኘው ክስ ላይ ሚያዝያ 5, 2022 የተላለፈው ውሳኔ በቤልጅየም ብቻ ሳይሆን በሌሎች የአውሮፓ አገሮችም ሃይማኖታዊ ነፃነታችንን ይበልጥ ለማስከበር ሊረዳን ይችላል።

እስከ 2018 ድረስ በብራስልስ-ካፒታል አካባቢ ያሉት ሁሉም ሃይማኖቶች የአምልኮ ቦታዎቻቸው ከግብር ነፃ የመሆን መብት ተሰጥቷቸው ነበር። ሆኖም በዚያ ዓመት ክልሉ የግብር ሕጉን በማስተካከሉ ከግብር ነፃ የመሆን መብት የሚያገኙት “እውቅና ያገኙ” ስድስት ሃይማኖቶች ብቻ ሆኑ። በዚህም የተነሳ በብራስልስ ያሉ የስብሰባ አዳራሾች በዓመት በድምሩ 45,000 ዩሮ (49,025 የአሜሪካ ዶላር) ገደማ የሚሆን ከባድ ግብር ተጣለባቸው።

የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት፣ የብራስልስ-ካፒታል መስተዳድር በአካባቢው የሚገኙ በመንግሥት “እውቅና ያገኙ” ስድስት ሃይማኖቶች ብቻ ከግብር ነፃ እንዲሆኑ መወሰኑ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የተፈጸመ አድልዎ እንደሆነና የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነትን እንደሚጥስ የሚገልጽ ውሳኔ አሳልፏል።

ፍርድ ቤቱ፣ የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥትን እውቅና ለማግኘት ሊያመለክቱ እንደሚችሉ በመግለጽ ቤልጅየም ያነሳችውን ሐሳብም ውድቅ አድርጓል። ፍርድ ቤቱ፣ ቤልጅየም ውስጥ የመንግሥትን እውቅና ለማግኘት ሂደቱን ማስጀመር የሚችለው የፍትሕ ሚኒስትሩ ብቻ እንደሆነና እውቅና የማግኘቱ ጉዳይ ሙሉ በሙሉ የተመካው በመንግሥት ውሳኔ ላይ እንደሆነ ገልጿል።

ፍርድ ቤቱ፣ ቤልጅየም ውስጥ የመንግሥትን እውቅና የማግኘቱ ሂደት ወጥ የሆነ አሠራር እንደሌለው ገልጿል። በተጨማሪም ሃይማኖታዊ ቡድኖች ከንብረት ግብር ነፃ የመሆን መብት ለማግኘት ፍትሐዊ አሠራር በሌለበት ተቋም ውስጥ እውቅና ለማግኘት እንዲያመለክቱ መጠበቅ ምክንያታዊ እንዳልሆነ ተናግሯል። ከዚህም ሌላ ፍርድ ቤቱ፣ ቤልጅየም የይሖዋ ምሥክሮችን ጨምሮ የተለያዩ ሃይማኖታዊ ቡድኖችን “ገለልተኛና ከአድልዎ ነፃ” በሆነ መንገድ ልትይዝ እንደሚገባ ገልጿል።

የፍርድ ቤቱ ውሳኔ፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት የሃይማኖታዊ እምነቶችን ትክክለኛነት ወይም ሰዎች ሃይማኖታቸውን የሚያራምዱበትን መንገድ የመወሰን መብት እንደሌላቸው ጎላ አድርጎ ይገልጻል። በተጨማሪም ሌሎች የአውሮፓ አገሮችም በድርጅታችን ላይ ኢፍትሐዊ ጫና የሚያሳድሩ የግብር ሕጎችን ከማውጣት እንዲቆጠቡ ለማድረግ ያግዛል።

ይሖዋ ስሙን ከፍ ከፍ ለማድረግ የሚረዱንን ሕጋዊ ድሎች ስለሰጠን በጣም እናመሰግነዋለን።—ራእይ 15:4