የካቲት 19, 2021
ቱርክሜኒስታን
የ20 ዓመቱ ወንድም አዛማትጃን ናርኩሊዬቭ ከእስር ከተፈታ ከአንድ ዓመት በኋላ በድጋሚ ታሰረ
የፍርድ ውሳኔ
ጥር 18, 2021 የቱርክሜኒስታን ፍርድ ቤት ከወንድም አዛማትጃን ናርኩሊዬቭ ክስ ጋር በተያያዘ ውሳኔውን አሳወቀ። አዛማትጃን በሕሊናው ምክንያት በወታደራዊ አገልግሎት ለመካፈል ፈቃደኛ ባለመሆኑ፣ ጥብቅ ቁጥጥር በሚደረግበት እስር ቤት ውስጥ የሁለት ዓመት እስራት ተፈርዶበታል። በገለልተኝነት አቋሙ ምክንያት ሲታሰር ይህ ሁለተኛ ጊዜው ነው።
አጭር መግለጫ
አዛማትጃን ናርኩሊዬቭ
የትውልድ ዘመን፦ 2000
ግለ ታሪክ፦ በ2018 ተጠመቀ። ትሑት፣ ልኩን የሚያውቅ እና ቀናተኛ ክርስቲያን በመሆኑ ይታወቃል። እናቱና ሁለት እህቶቹም የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው
የክሱ ሂደት
የ20 ዓመቱ አዛማትጃን በሕሊናው ምክንያት በወታደራዊ አገልግሎት ለመካፈል ፈቃደኛ ባለመሆኑ መጀመሪያ ላይ የተፈረደበትን የአንድ ዓመት እስር ያጠናቀቀው ጥር 7, 2020 ነበር። ቱርክሜኒስታን ውስጥ በሕሊናቸው ምክንያት በወታደራዊ አገልግሎት ለመካፈል ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች ለሁለተኛ ጊዜ ክስ ሊመሠረትባቸው ይችላል፤ በመሆኑም ወታደራዊ መኮንኖች ከአምስት ወራት በኋላ አዛማትጃንን በድጋሚ መለመሉት። አዛማትጃን ጦር ሠራዊቱን ለመቀላቀልም ሆነ መሣሪያ መታጠቅን በማይጠይቁ የውትድርና አገልግሎቶች ለመካፈል ፈቃደኛ አለመሆኑን በጽሑፍ ገለጸ፤ ሆኖም አቋሙ ተቀባይነት አላገኘም።
ታኅሣሥ 20, 2020 አቃቤ ሕጉ የወንጀል ክስ መሠረተበት። ባለሥልጣናቱ ፓስፖርቱንም ቀሙት።
አዛማትጃን እና ቤተሰቡ ታማኝ ለመሆን ባደረጉት ውሳኔ እንደሚባረኩ በመተማመን ለእነሱ መጸለያችንን እንቀጥላለን። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ “ታማኝ ለሆነ ሰው ታማኝ” እንደሚሆን ዋስትና ይሰጠናል።—መዝሙር 18:25