በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ጆቪዶን ቦቦጆኖቭ

መጋቢት 31, 2020
ታጂኪስታን

በታጂኪስታን የሚኖረው ወንድም ጆቪዶን ቦቦጆኖቭ ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ሕሊናው ባለመፍቀዱ ምክንያት እስራት ሊፈረድበት ይችላል

በታጂኪስታን የሚኖረው ወንድም ጆቪዶን ቦቦጆኖቭ ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ሕሊናው ባለመፍቀዱ ምክንያት እስራት ሊፈረድበት ይችላል

የታጂኪስታን ዋና ከተማ በሆነችው በዱሻንበ ያለው ወታደራዊ ፍርድ ቤት በሕሊናው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆነውን የወንድም ጆቪዶን ቦቦጆኖቭን ጉዳይ ተመልክቶ ረቡዕ፣ ሚያዝያ 1, 2020 ውሳኔ ለማሳለፍ ቀጠሮ ይዟል። ወንድም ቦቦጆኖቭ ፍርድ ሳይበየንበት ለአምስት ወራት ያህል እጅግ አስከፊ በሆነ ሁኔታ ታስሮ ቆይቷል።

ጥቅምት 4, 2019 በኩጃንድ ከተማ ያሉ ወታደሮች የ19 ዓመቱን ወንድም ቦቦጆኖቭን አስገድደው ወደ ወትድርና አገልግሎት ቢሮ በመውሰድ አሰሩት። ከሁለት ቀናት በኋላ በሌኒን አውራጃ ወደሚገኝ ወታደራዊ ማሠልጠኛ በግዳጅ በባቡር ተወሰደ። በኋላም ወደ ወታደራዊ ቡድን ቁጥር 45075 በመውሰድ የወታደር ልብስ እንዲለብስና የውትድርና ቃለ መሐላ እንዲፈጽም ለማስገደድ ሞከሩ። ጥር 28, 2020 ክስ ተመሠረተበት።

የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑት የጆቪዶን ቦቦጆኖቭ ወላጆች የፕሬዚዳንት አስተዳደር ቢሮንና የእንባ ጠባቂ ተቋምን ጨምሮ ወደተለያዩ የታጂኪስታን ባለሥልጣናት አቤቱታ አስገብተዋል። የታጂኪስታን ባለሥልጣናት አገሪቱ አማራጭ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ሕግ ስለሌላት ወንድም ቦቦጆኖቭ ያደረገው ነገር እንደ ወንጀል እንደሚቆጠርና መታሰሩ አግባብነት እንዳለው ተናግረዋል።

ይሖዋ ወንድም ቦቦጆኖቭ ድፍረት በማሳየቱ እንደሚባርከውና ለእሱም ሆነ ለቤተሰቦቹ ጥንካሬና ሰላም እንደሚሰጣቸው እንተማመናለን።—መዝሙር 29:11