በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ታኅሣሥ 24, 2020
አዘርባጃን

በአዘርባጃን የአምልኮ ነፃነት ይበልጥ እንዲከበር ያደረጉ የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት በቅርቡ ያስተላለፋቸው ውሳኔዎች

በአዘርባጃን የአምልኮ ነፃነት ይበልጥ እንዲከበር ያደረጉ የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት በቅርቡ ያስተላለፋቸው ውሳኔዎች

በጥቅምት እና በኅዳር 2020፣ የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት በአዘርባጃን የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችን የሚደግፉ ውሳኔዎች አስተላልፏል። ፍርድ ቤቱ ብይን ያስተላለፈው ግሪድኔቫ፣ ሻቬሊ እና ሼንጌላያ፣ ጃፋሮፍ እንዲሁም ታጊዬፍ በአዘርባጃን መንግሥት ላይ የመሠረቱትን ክስ ተመልክቶ ነው። የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ያስተላለፋቸው እነዚህ ውሳኔዎች፣ የወንድሞቻችንን የመስበክ፣ ለአምልኮ የመሰብሰብና ጽሑፎችን ወደ አዘርባጃን የማስገባት ሕጋዊ መብታቸውን የሚያስከብሩ ናቸው።

ክሶቹ ለፍርድ ቤቱ የቀረቡት በ2011 እና በ2012 ነው። ግሪድኔቫ እንዲሁም ሻቬሊ እና ሼንጌላያ በአዘርባጃን መንግሥት ላይ ክሶች የመሠረቱት ፖሊሶች የጉባኤ ስብሰባዎችን በኃይል በማስተጓጎላቸውና የስብከት እንቅስቃሴያችንን ለማስቆም እንቅፋት በመፍጠራቸው ነው። ጃፋሮፍ እና ታጊዬፍ በአዘርባጃን መንግሥት ላይ ክሶች የመሠረቱት ደግሞ መንግሥት ጽሑፎች ወደ አገሪቱ እንዳይገቡ በመከልከሉ ወይም የተወሰነ ገደብ በመጣሉ የተነሳ ነው።

የሚገርመው ነገር፣ ከአራቱ ክሶች በሦስቱ (የግሪድኔቫ፣ የጃፋሮፍ እና የታጊዬፍ ክሶች) የአዘርባጃን መንግሥት ጥፋተኛ መሆኑን አምኖ የተቀበለ ሲሆን በአጠቃላይ 10,500 ዩሮ (12,880 የአሜሪካ ዶላር) የካሳ ክፍያ ለመስጠት ተስማምቷል።

ሻቬሊ እና ሼንጌላያ በአዘርባጃን መንግሥት ላይ ያቀረቡት ክስ ደግሞ በወረዳ ሥራ ላይ ያሉ ባልና ሚስትን የሚመለከት ነው፤ እነዚህ ባልና ሚስት ምንም ጥፋት ባይሠሩም በቁጥጥር ሥር እንዲውሉና ከአገር እንዲባረሩ ተደርጓል፤ ለዚህም የአዘርባጃን መንግሥት ለባልና ሚስቱ 3,000 ዩሮ (3,680 የአሜሪካ ዶላር) ካሳ እንዲከፍል ፍርድ ቤቱ ወስኗል።

የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት፣ ባስተላለፈው ውሳኔ ላይ እንዲህ የሚል መግለጫ ሰጥቷል፦ “በመጸለያቸው ወይም ሃይማኖታቸው በሚጠይቀው መሠረት አምልኮ በማካሄዳቸው ብቻ [በባልና ሚስቱ ላይ] ቅጣት መበየን [የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች] ድንጋጌን የሚጻረር ነው። ይህን አለመቀበል በመንግሥት ያልተመዘገቡ አናሳ ሃይማኖታዊ ተቋማት እንዲገለሉ ያደርጋል፤ ይህ ደግሞ አንድ ሰው ምን እንደሚያምን የሚወስንለት መንግሥት ነው ከማለት አይተናነስም።”

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ፣ የአዘርባጃን ባለሥልጣናት ለይሖዋ ምሥክሮች ጥሩ አመለካከት እንዳላቸው የሚያሳዩና መብቶቻቸው እንዲከበሩ የሚያደርጉ እርምጃዎችን መውሰድ ጀምረዋል። የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት በቅርቡ ያስተላለፋቸው እነዚህ ውሳኔዎች፣ የወንድሞቻችን ሃይማኖታዊ ነፃነት እንዲከበር ተጨማሪ አስተዋጽኦ ስለሚያደርጉ አመስጋኞች ነን። ከሁሉ በላይ ሊመሰገን የሚገባው ግን “መጠጊያችንና ብርታታችን” የሆነው አምላካችን ይሖዋ ነው።—መዝሙር 46:1