ሚያዝያ 15, 2020
ዓለም አቀፋዊ ዜና
ልጆች በወረርሽኙ መሃል አዳዲስ የስብከት ዘዴዎችን እየተጠቀሙ ነው
በዓለም ዙሪያ ያሉ የይሖዋ ምሥክር ልጆች በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መሃል ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ ይዘው ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል፤ እነዚህ ልጆች ለመስበክና የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ለማበረታታት የሚያስችሉ አዳዲስ ዘዴዎችን እየፈለጉ ነው።
ኒው ዚላንድ ውስጥ አንዳንድ ሰዎች በሰፈር የሚያልፉትን ሕፃናት ለማዝናናት ሲሉ መስኮታቸው ላይ አሻንጉሊቶችንና ሥዕሎችን ያስቀምጣሉ። በበርካታ ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙ ልጆች ይህን አጋጣሚ በመጠቀም የካሌብንና የሶፊያን ሥዕል እንዲሁም “jw.org ላይ ልታዩን ትችላላችሁ” የሚል ጽሑፍ የያዘ ፖስተር ሠርተው መስኮታቸው ላይ ያንጠለጥላሉ።
በስዊዘርላንድ የምትኖር ኤሚሊያ የተባለች የዘጠኝ ዓመት ልጅ በሽታ የመከላከል አቅሟን የሚያዳክም የጤና እክል አለባት። ኤሚሊያ በአንድ የአረጋውያን መጦሪያ ተቋም ለሚኖሩ ሰዎች ደብዳቤ ለመጻፍ ወሰነች፤ ይህ ተቋም ጠያቂዎችን ማስገባት አቁሟል። ኤሚሊያ በደብዳቤዋ ውስጥ የኖኅንና እሱ የሠራውን መርከብ ሥዕል አካትታ ነበር። ኖኅና ቤተሰቡ መርከቡ ውስጥ በነበሩበት ወቅት እንደፈለጉ መንቀሳቀስ እንደማይችሉ ከገለጸች በኋላ እንዲህ ማድረጋቸው ሕይወታቸውን እንዳተረፈላቸው ጻፈች። ከዚያም የተቋሙን ነዋሪዎች ‘እንደ ኖኅ ሳይወጡ እንዲቆዩ’ አበረታታቻቸው። ኤሚሊያ ወረርሽኙ ካለፈ በኋላ የተቋሙን ነዋሪዎች ሄዳ ለመጠየቅ ታስባለች።
አንዳንድ ሰዎች ለኤሚሊያ ደብዳቤ ምላሽ የሰጡ ሲሆን እሷም በድጋሚ ጽፋላቸዋለች። አንድ ጋዜጠኛ ስለ ኤሚሊያ በመስማቱ ያደረገችውን ነገር በአንድ የጋዜጣ ዓምድ ላይ ዘግቦታል።
ፔይተን ኬምፍ እና ኤላ ኬምፍ የተባሉ በኦንታሪዮ፣ ካናዳ የሚኖሩ ሁለት እህትማማቾች በወረርሽኙ ምክንያት ከጉባኤያቸው ወንድሞችና እህቶች ጋር በአካል ቢራራቁም በተለያዩ መንገዶች መገናኘታቸውን ቀጥለዋል። አባታቸው ጃሬድ እንዲህ ብሏል፦ “ልናነጋግራቸው የምንፈልጋቸውን ወንድሞችና እህቶች ስም ዝርዝር በቤተሰብ አምልኳችን ወቅት ከልጆቻችን ጋር ሆነን ጻፍን።” እናታቸው ጄሲካ ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “ወንድሞችንና እህቶችን እንዲሁም ቤተሰቦቻችንንና ጓደኞቻችንን እንደምናስታውሳቸው ማሳየት አስፈላጊ መሆኑን ለልጆቻችን ማስተማር እንፈልጋለን።”
በተመሳሳይም በኮሎራዶ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የምትኖረው የዘጠኝ ዓመቷ ስቴላና እናቷ በጉባኤያቸው ውስጥ ያሉ አረጋውያን ወንድሞችና እህቶችን ለማነጋገር ጥረት አድርገዋል። የወንድሞችን ስም ዝርዝር ካዘጋጁ በኋላ ሁሉም ጋ አንድ በአንድ ደወሉ።
ጆናታን ማካምፕሰን እና ሾን ማካምፕሰን የተባሉ የ12 እና የ15 ዓመት ወንድማማቾች ከወላጆቻቸው ጋር በአሪዞና በሚገኝ የቻይንኛ ጉባኤ ውስጥ ያገለግላሉ። እነዚህ ወንድማማቾች ሁልጊዜ ጠዋት ትምህርት ከመጀመራቸው በፊት በቻይንኛ ደብዳቤ በመጻፍ ይሰብካሉ። ገና ቋንቋውን እየተማሩ ስለሆነ ደብዳቤ ለመጻፍ ብዙ ጊዜ ይወስድባቸዋል። ያም ቢሆን ለቻይንኛ ተናጋሪዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለማወጅ ቆርጠዋል።
በምዕራባዊ ሚሺገን የሚኖሩ ከ2 እስከ 15 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ስድስት ልጆች ከእናታቸውና ከአንዲት አቅኚ እህት ጋር አዘውትረው ወደ አንድ የአረጋውያን መጦሪያ ተቋም ይሄዱ ነበር። ሆኖም ባለሥልጣናት በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የተነሳ ጎብኚዎች ወደ ተቋሙ እንዳይመጡ ከለከሉ። በመሆኑም ልጆቹ መዝሙር ሲዘምሩ ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ሲያነቡ ወላጆቻቸው ቪዲዮ ይቀርጿቸውና ለተቋሙ ነዋሪዎች ይልካሉ። ከተቋሙ ሠራተኞች አንዱ፣ አንድ አረጋዊ በኮሮና ቫይረስ ስለሞቱ ሰዎች የሚገልጽ ዜና ካዩ በኋላ በመንፈስ ጭንቀት ተውጠው እንደነበርና የልጆቹን ቪዲዮ ካዩ በኋላ ግን እንደተረጋጉ ለልጆቹ አባት ነግሮታል።
ይሖዋ እነዚህ ልጆች ለሰዎች ፍቅር ለማሳየትና በተለያዩ መንገዶች በመስበክ እሱን ለማወደስ የሚያደርጉትን ጥረት ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው እርግጠኞች ነን።—መዝሙር 148:12, 13