በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

“የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?” የሚል ርዕስ ያለው ቁጥር 2 2020 መጠበቂያ ግንብ በ2023 ዘመቻ ላይ በዓለም ዙሪያ ሲተዋወቅ

ኅዳር 29, 2023
ዓለም አቀፋዊ ዜና

መስከረም 2023 በተካሄደው ዘመቻ ላይ ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸው መልእክት በዓለም ዙሪያ ተዳረሰ

መስከረም 2023 በተካሄደው ዘመቻ ላይ ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸው መልእክት በዓለም ዙሪያ ተዳረሰ

መስከረም 2023 በዓለም ዙሪያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ስለ አምላክ መንግሥት ለማወጅ በአንድ ልዩ የስብከት ዘመቻ ተካፍለው ነበር። በዘመቻው ላይ “የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው?” የሚል ርዕስ ያለውን ቁጥር 2 2020 መጠበቂያ ግንብ ተጠቅመዋል። a ቀጣዮቹ ተሞክሮዎች ዘመቻው በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ምን ጥሩ ውጤት እንዳስገኘ ያሳያሉ።

ማላዊ

በማላዊ ሁለት እህቶቻችን ለአንድ የመንደር መሪ መጠበቂያ ግንቡን ካበረከቱለት በኋላ የአምላክ መንግሥት በቅርቡ መላዋን ምድር እንደሚያስተዳድር ገለጹለት። በዚህ ጊዜ የመንደሩ መሪ “ስለዚህ ሥልጣንህን የምታጣበት ቀን ይመጣል እያላችሁኝ ነው?” በማለት ጠየቃቸው። እህቶች ለሰው ልጆች ችግሮች ብቸኛው መፍትሔ የአምላክ መንግሥት እንደሆነ ከነገሩት በኋላ የመንደሩ መሪ እንዲህ አለ፦ “ይሄማ ምሥራች ነው። እኔ መሪ ብሆንም የአምላክ መንግሥት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ላሉ ሰዎች የሚያከናውናቸውን ነገሮች እኛ መሪዎች ማከናወን እንደማንችል አልክድም።” ከዚያም የመንደሩ መሪ መጠበቂያ ግንቡን ለሌሎች የመንደር መሪዎችም መስጠት ስለፈለገ ተጨማሪ አምስት ቅጂዎች እንዲሰጡት ጠየቀ። በተጨማሪም ወደፊት ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ መወያየት እንደሚፈልግ ተናገረ።

ሜክሲኮ

አንዲት እህት በፑዌብላ፣ ሜክሲኮ በአውቶቡስ እየተጓዘች ሳለ አንድን በዕድሜ የገፉ ሰውዬ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት መስማት ይፈልጉ እንደሆነ ጠየቀቻቸው። ሰውየው ፈቃደኛ መሆናቸውን ሲገልጹላት በማቴዎስ 6:9, 10 ላይ የሚገኘውን ኢየሱስ የተናገረውን ሐሳብ አነበበችላቸው። በዚህ ጊዜ ሰውየው “የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው? ከዚህ በፊት መጽሐፍ ቅዱስን አንብቤም ሆነ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተወያይቼ አላውቅም” አሏት። እህታችንም መጠበቂያ ግንቡን ሞባይሏ ላይ በማውጣት ለጥያቄያቸው መልስ ሰጠቻቸው። ሰውየው ተጨማሪ ጥያቄዎችን ስላነሱ እህታችን JW ላይብረሪ አፕሊኬሽንን ተጠቅመው ለጥያቄዎቻቸው መልስ ማግኘት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ አሳየቻቸው። ሆኖም ሞባይላቸው ላይ ያላቸው ቦታ በጣም ትንሽ እንደሆነ ሲያውቁ “ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ስለ አምላክ መንግሥት ማወቅ ነው” በማለት ከስልካቸው ላይ አንዳንድ ነገሮችን አጠፉ። መውረጃቸው ከመድረሱ በፊት ሙሉውን መጠበቂያ ግንብ አንብበው ጨረሱ፤ በተጨማሪም ለዘላለም በደስታ ኑር! በተባለው ብሮሹር ምዕራፍ አንድ ላይ የተወያዩ ሲሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር ተስማሙ። እህታችንን ደጋግመው ያመሰገኗት ከመሆኑም በላይ በስብሰባዎቻችን ላይ መገኘት እንደሚፈልጉ ገለጹ።

ታይዋን

በታይዋን የሚኖሩ ሁለት እህቶች በሃዋይ በተከሰተው ሰደድ እሳት በጣም ያዘነ ሰው አገኙ። አንዷ እህት ወደፊት ምድር ገነት ስትሆን የሚኖረውን ሁኔታ የሚያሳይ ሥዕል ከመጠበቂያ ግንቡ ላይ አሳየችው። በዚህ ጊዜ ሰውየው እንዲህ አለ፦ “ምድር እዚህ ሥዕል ላይ እንዳለው ብትሆን እንዴት ጥሩ ነበር። መጥፎ ነገር ብቻ በሚሰማበት በዚህ ዓለም ውስጥ ይህን መጽናኛና ተስፋ የሚሰጥ መልእክት መስማት በጣም ደስ ይላል።”

ኒው ዚላንድ

በኒው ዚላንድ የሚኖር ቤን የተባለ ወንድም ከቤት ወደ ቤት ሲያገለግል ለአንዲት ወጣት እናት የአምላክ መንግሥት በአስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ ላሉ ሁሉ በቅርቡ እፎይታ እንደሚያስገኝ ገለጸላት። በዚህ ጊዜ እንዲህ አለች፦ “እዚህ መምጣትህ በጣም የሚያስደንቅ ነው! ትናንት ማታ ስለ ወደፊቱ ጊዜ በጣም ከመጨነቄ የተነሳ እንቅልፍ አልወስድ ብሎኝ ነበር።” ቤን ራእይ 21:4⁠ን አንብቦ የአምላክ መንግሥት ሕመምንና ሞትን እንደሚያስወግድ ሲነግራት እንባዋ ዱብ ዱብ ማለት ጀመረ። መጠበቂያ ግንቡን በደስታ ከተቀበለች በኋላ ለማንበብና ይበልጥ ለማወቅ እንደምትጓጓ ገለጸች።

ኢንዶኔዥያ

ፍሬድሪክ የተባለ ወንድም በኢንዶኔዥያ ባለ የጤና ማዕከል ውስጥ ወረፋ እየጠበቀ ሳለ ከልጁ ጋር አብሮ ወረፋ ከሚጠብቅ ሰው ጋር ውይይት ይጀምራል። በጨዋታቸው መሃል ፍሬድሪክ በቅርቡ ሕመምና መከራ የማይኖርበት ጊዜ እንደሚመጣ ስለሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ለሰውየው ይነግረዋል። በማቴዎስ 6:9, 10 ላይ ኢየሱስ ስለ አምላክ መንግሥት የተናገረውን ሐሳብ ካሳየው በኋላ “ስለዚህ መከራ የሚወገደው እንዴት ነው?” በማለት ጠየቀው። ሰውየውም “በአምላክና በመንግሥቱ አማካኝነት” በማለት በትክክል መለሰ። ከዚያም ሰውየው ስለ አምላክ መንግሥት ምንነት ጠየቀ፤ ሆኖም ልክ በዚያ ሰዓት ወረፋቸው ደርሶ የልጅየው ስም ስለተጠራ መሄድ ነበረባቸው። በመሆኑም ፍሬድሪክ ቶሎ ብሎ አድራሻውንና መጠበቂያ ግንቡን ለሰውየው ሰጠው። የሚገርመው በቀጣዩ ቀን ጠዋት የልጁ አባትና እናት የአምላክ መንግሥት ስለሚያመጣቸው በረከቶች ይበልጥ ማወቅ ስለፈለጉ የፍሬድሪክ ቤት ድረስ ቀጥ ብለው ሄዱ። ፍሬድሪክም በጣም ተደስቶ ውይይቱን ለመቀጠል ዝግጅት አደረገ።

እንግሊዝ

በሳውዝፖርት፣ እንግሊዝ የሚኖሩት ማርክ እና የአሥር ዓመት ወንድ ልጁ ፍሊን በዘመቻው ወቅት ከቤት ወደ ቤት ገና የመጀመሪያውን በር ሲያንኳኩ በመካከለኛ የዕድሜ ክልል ውስጥ የምትገኝ አንዲት ሴት አገኙ። ሴትየዋ መጠበቂያ ግንቡን ከማርክ እጅ በደስታ ከወሰደች በኋላ ሽፋኑ ላይ ያለውን ጥያቄ በተመለከተ እንዲህ አለች፦ “ዛሬ መምጣታችሁ በጣም ነው የሚገርመው! የአሁኑን ያህል የዚህን ጥያቄ መልስ ማወቅ የፈለግኩበት ጊዜ የለም።” ከዚያም ልጇ በቅርቡ እንደሞተባትና ማጽናኛ እየፈለገች እንደነበር እያለቀሰች ነገረቻቸው። ማርክም ወዲያውኑ ስለ ትንሣኤ ተስፋ ነገራት። በሰማችው ነገር ልቧ በጥልቅ ስለተነካ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ጠየቀች። ማርክ እና ፍሊን ተመልሰው ሲሄዱ ሴትየዋና ባለቤቷ ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለውን ብሮሹር በደስታ ተቀብለው መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመሩ።

ደቡብ ሱዳን

በደቡብ ሱዳን ባለ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ ስለ አምላክ መንግሥት የማወቅ ጉጉት ያላቸው ብዙ ሰዎች ተገኝተዋል። የሚገርመው በሁለት ሰዓት ውስጥ ብቻ ይህን መጠበቂያ ግንብ ጨምሮ ወደ 1,000 የሚጠጉ ጽሑፎች ተበርክተዋል። አንድ ስደተኛ “የመጣችሁት ልክ በትክክለኛው ጊዜ ላይ ነው። የሚያስፈልገን ይሄ ነበር” በማለት ተናግሯል። ሌላ ስደተኛ ደግሞ ወንድሞቻችንን እንዲህ ብሏቸዋል፦ “ስለ እኛ ስላሰባችሁ በጣም እናመሰግናችኋለን። ከሩቅ ቦታ እንደምትመጡ እናውቃለን፤ ግን እባካችሁ ተመልሳችሁ ኑ።”

ሁላችንም በዚህ ዓለም አቀፍ ዘመቻ በመካፈል በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ላሉ ሰዎች የእውነተኛ መጽናኛና ተስፋ ምንጭ ስለሆነው ስለ አምላክ መንግሥት የመናገር መብት በማግኘታችን በጣም ተደስተናል።—ሮም 15:4

ከታች ያሉት ፎቶግራፎች በተለያዩ አገራት ያሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በዓለም አቀፉ የስብከት ዘመቻ በደስታ ሲካፈሉ የሚያሳዩ ናቸው።

a በዚህ ርዕስ ውስጥ መጠበቂያ ግንብ የሚለው አገላለጽ የቁጥር 2 2020⁠ን መጠበቂያ ግንብ ያመለክታል።

 

ቡርኪና ፋሶ

ኮስታ ሪካ

ኢትዮጵያ

ጆርጂያ

ኢንዶኔዥያ

ጣሊያን

ኬንያ

ሜክሲኮ

ኒው ዚላንድ

ፓናማ

ፖላንድ

ስኮትላንድ

ደቡብ ኮሪያ

ታይዋን

ቶጎ

ዌልስ