ኅዳር 15, 2024
ዓለም አቀፋዊ ዜና
‘ምሥራቹን ስበኩ!’ የተባሉት የ2024 ልዩ የክልል ስብሰባዎች ሳንቲያጎ፣ ቺሊ ላይ ተደመደሙ
‘ምሥራቹን ስበኩ!’ ከተባሉት ልዩ የክልል ስብሰባዎች የመጨረሻው ከጥቅምት 18 እስከ 20, 2024 ተካሂዷል፤ የክልል ስብሰባው የተከናወነው ሳንቲያጎ፣ ቺሊ በሚገኘው ኤል ትሬቦል የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽ ነው። በስብሰባው ላይ በድምሩ 9,140 ሰዎች ተገኝተዋል፤ 59 ደግሞ ተጠምቀዋል። ይህ በዚህ ዓመት በሳንቲያጎ የተደረገ ሁለተኛው ልዩ የክልል ስብሰባ ሲሆን ከሰኔ እስከ ጥቅምት 2024 በዓለም ዙሪያ ከተደረጉት 15 ልዩ የክልል ስብሰባዎች ደግሞ የመጨረሻው ነው።
ከመላው ዓለም ለሚመጡ ወንድሞችና እህቶች አቀባበል ለማድረግ ልዩ የክልል ስብሰባ በተደረገበት በእያንዳንዱ ከተማ ወራት የፈጀ ዝግጅት ተደርጓል። በቺሊ ከ16 አገራት የተውጣጡትን 2,397 ልዑካን ለመቀበል በሺዎች የሚቆጠሩ ፈቃደኛ ሠራተኞች ያለመታከት ለፍተዋል። አንዲት እህት ብዙዎቹ ፈቃደኛ ሠራተኞች ለዚህ ሥራ እርዳታ ለማበርከት ሲሉ የሥራ ሰዓታቸውንና የግል ፕሮግራማቸውን እንዳስተካከሉ ከገለጸች በኋላ እንዲህ ብላለች፦ “እኔ መሥዋዕትነት ከፍያለሁ ለማለት እቸገራለሁ። ካሳለፍኩት የማይረሳ ጊዜና ካፈራኋቸው አዳዲስ ጓደኞች ጋር ሲተያይ፣ የሚሰማኝ ድካም ለንጽጽር እንኳ የሚበቃ አይደለም።”
ከዩናይትድ ስቴትስ የሄደ አንድ ወንድም በሳንቲያጎ በተካሄደው ልዩ የክልል ስብሰባ ላይ ስላሳለፈው ጊዜ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “አየር ማረፊያው ጋ ከደረስንባት ሰዓት ጀምሮ ወንድሞች እና እህቶች ያሳዩን ፍቅር ለማመን የሚከብድ ነው። በቃላት ልገልጸው አልችልም።” ከፔሩ የሄደች ሌላ እህት ደግሞ “በልዩ የክልል ስብሰባ ላይ ስገኝ የመጀመሪያዬ ነው። ሁሉም ነገር ከጠበቅሁት በላይ ነው የሆነው። ይሖዋ በዚህ ዝግጅት አማካኝነት አጠንክሮኛል እንዲሁም አበረታቶኛል” ብላለች።
በመላው ዓለም ያለን ወንድሞችና እህቶች ሁሉ፣ ይሖዋ በ2024 ‘ምሥራቹን ስበኩ!’ በሚል ርዕስ የተካሄዱትን ልዩ የክልል ስብሰባዎች ስለባረከልን እናመሰግነዋለን። ሕዝቡ፣ ቅዱስ ስሙን የሚያወድስባቸውንና ከፍ የሚያደርግባቸውን እነዚህን ዝግጅቶች ስላደረገም አመስጋኞች ነን!—መዝሙር 34:3
ከዚህ በታች ያሉት ፎቶግራፎች፣ በ2024 ‘ምሥራቹን ስበኩ!’ በሚል ርዕስ በተከናወኑት 15 ልዩ የክልል ስብሰባዎች ላይ ወንድሞችና እህቶች ያሳዩትን ፍቅር እንዲሁም ደስታቸውንና አንድነታቸውን የሚገልጹ ናቸው።
አሱንሲዮን፣ፓራጓይ
ቤይ ማዉ፣ ጓዴሎፕ
ቡዳፔስት፣ ሃንጋሪ
ሄልሲንኪ፣ ፊንላንድ
ሊዮን፣ ፈረንሳይ
ፊላደልፊያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ
ፕራግ፣ ቼክ ሪፑብሊክ
ሬይኪቪክ፣ አይስላንድ
ሳንቲያጎ፣ ቺሊ 1
ሳንቲያጎ፣ ቺሊ 2
ሳንቶ ዶሚንጎ፣ ዶሚኒካን ሪፑብሊክ
ሶፊያ፣ ቡልጋሪያ
ሱቫ፣ ፊጂ
ታምፓ፣ ዩናይትድ ስቴትስ
ዙሪክ፣ ስዊዘርላንድ