ኅዳር 4, 2019
ዓለም አቀፋዊ ዜና
የይሖዋ ምሥክሮች የስብከት ሥራ አዲስ ምዕራፍ ላይ ደረሰ—JW.ORG ላይ የሚወጡ ነገሮች የሚተረጎሙበት ቋንቋ 1,000 አለፈ
የበላይ አካሉ ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት ለማድረግ የምናከናውነው ሥራ አዲስ ምዕራፍ ላይ እንደደረሰ ሲገልጽ ታላቅ ደስታ ይሰማዋል። በአሁኑ ጊዜ የተለያዩ ርዕሶችን፣ ቪዲዮዎችን እና ኦዲዮዎችን JW.ORG ላይ በ1,000 ቋንቋዎች ማግኘት የሚቻል ሲሆን ይህም 100 የምልክት ቋንቋዎችን ይጨምራል።
የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ጌሪት ሎሽ እንዲህ ብሏል፦ “የትርጉም ሥራችን ከ1800ዎቹ መጨረሻ አንስቶ ረጅም ዘመናትን አስቆጥሯል፤ ሆኖም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአስገራሚ ሁኔታ እድገት እያሳየ ነው።” የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ጄፍሪ ጃክሰን ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “ጥር 2013 ላይ የትርጉም ሥራችን ወደ 508 ቋንቋ ደርሶ ነበር፤ እዚህ ለመድረስ ከመቶ ዓመት በላይ ፈጅቶብናል። ሆኖም ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ ብቻ ይህ ቁጥር በእጥፍ ጨምሮ ከ508 ወደ 1,000 መድረሱ በጣም የሚያስገርም ነው።”
ከድረ ገጹ ላይ ጽሑፎችን፣ ኦዲዮዎችንና ቪዲዮዎችን በ1,000 ቋንቋዎች ማውረድ ይቻላል። በተጨማሪም የjw.org ዋና ገጽም ሆነ በውስጡ የሚገኙ የተለያዩ ገጾች ወደ 821 ቋንቋዎች ተተርጉመዋል፤ በመላው ዓለም የjw.orgን ያህል በስፋት የተተረጎመ ድረ ገጽ የለም። አብዛኛውን የትርጉም ሥራ የሚያከናውኑት በዓለም ዙሪያ በሚገኙ 350 ገደማ የሚሆኑ የርቀት የትርጉም ቢሮዎች ውስጥ የሚያገለግሉ በደንብ የሠለጠኑ ተርጓሚዎች ናቸው።
በዎርዊክ፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት ውስጥ የትርጉም አገልግሎት ክፍል የበላይ ተመልካች ሆኖ የሚያገለግለው ወንድም ኢሳክ መሬ እንዲህ ብሏል፦ “ጽሑፎችን በብዙ ቋንቋዎች ለመተርጎምና ለማተም ብዙ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን ማለፍ አስፈልጎናል። አንዳንድ ጊዜ፣ ብዙም በማይታወቁ ቋንቋዎች ጽሑፎች ለማተም ብንፈልግም የእነዚህን ቋንቋዎች ፊደላት በኮምፒውተር ፕሮግራሞቻችን ውስጥ አናገኝም። በመሆኑም ላለፉት በርካታ ዓመታት የተለያዩ ቋንቋዎችን ፊደላት ለኮምፒውተር ፕሮግራማችን አዘጋጅተናል፤ ይህም በመቶዎች በሚቆጠሩ ቋንቋዎች ጽሑፎችን ለማተም አስችሎናል። ጽሑፎቻችን jw.org ላይ በብዙ ቋንቋዎች እንዲወጡ ማድረግም ቢሆን ቀላል አልነበረም። እንዲያውም jw.org ላይ ከሚገኙት 1,000 ቋንቋዎች መካከል ብዙዎቹ ከእኛ ጽሑፎች ውጭ ኢንተርኔት ላይ የሚገኝ ሌላ ጽሑፍ የላቸውም።”
የሜፕስ ፕሮግራሚንግ ዲፓርትመንት የበላይ ተመልካች የሆነው ወንድም ክላይቭ ማርቲን እንዲህ ብሏል፦ “በድረ ገጹ ላይ የሚወጣው እያንዳንዱ ጽሑፍ የተለያየ ፊደልና የአጻጻፍ ዘይቤ ባላቸው የተለያዩ ቋንቋዎች እንዲወጣ ማድረግ ተፈታታኝ ሆኖብን ነበር። ለምሳሌ ድረ ገጹ ላይ ካሉ ቋንቋዎች መካከል ሃያ አንዱ ከቀኝ ወደ ግራ የሚጻፉ ናቸው። ድረ ገጹ ላይ ላሉት 100 የሚያህሉ የምልክት ቋንቋዎች ደግሞ መስማት የተሳናቸው ሰዎች በቀላሉ መጠቀም እንዲችሉ ለየት ያለ ንድፍ አዘጋጅተናል።”
ለንግድ ዓላማ የሚውሉ አብዛኞቹ ድረ ገጾች የሚተረጎሙት ከፍተኛ ትርፍ ወደሚያስገኙ ቋንቋዎች ብቻ ነው። እኛ የይሖዋ ምሥክሮች ግን ፍላጎታችን ትርፍ ማግኘት አይደለም። ዓላማችን የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት የመስማት ጉጉት ያላቸው ሰዎች መልእክቱን ቀላልና ማራኪ በሆነ መልኩ ማግኘት እንዲችሉ መርዳት ነው።
ይሖዋ “ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት” ለማድረግ የምናከናውነውን ትጋት የተሞላበት ሥራ ስለባረከልን እናመሰግነዋለን። ይሖዋ ሥራው እስኪጠናቀቅ ድረስ የመንግሥቱን ምሥራች ልበ ቅን ለሆኑ ሰዎች ለማዳረስ የሚያስፈልገንን ማንኛውንም ነገር እንደሚሰጠን እንተማመናለን።—ማቴዎስ 28:19, 20