ሚያዝያ 21, 2020
ዓለም አቀፋዊ ዜና
የ2020 የመታሰቢያው በዓል አከባበር—በJW.ORG
የድረ ገጻችን ጎብኚዎች ቁጥር በእጅጉ ጨምሯል
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዓለም ዙሪያ መስፋፋቱ እንዲሁም የይሖዋ ምሥክሮች በመታሰቢያው በዓል ወቅት እንቅስቃሴያቸውን ማፋፋማቸው በርካታ ሰዎች መንፈሳዊ መጽናኛ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት እንዲሁም ዜና ለማግኘት jw.orgን እንዲመለከቱ አድርጓቸዋል። በመጋቢት ወር ድረ ገጹን የጎበኙ ሰዎች ቁጥር ካለፈው ወር ጋር ሲወዳደር የ50 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ጥያቄ በሚያቀርቡ ሰዎች ረገድም አዲስ ከፍተኛ ቁጥር ተመዝግቧል።
ወረርሽኙ ከጀመረ በኋላ jw.orgን የሚጎበኙ ሰዎች ቁጥር እያደገ መጥቷል። እንዳለፉት ወራት ሁሉ የካቲት ውስጥም በየቀኑ ሁለት ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ድረ ገጹን ይጎበኙ ነበር። መጋቢት ውስጥ ግን ይህ አኃዝ ጨምሮ በቀን ከሦስት ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ድረ ገጻችንን መጎብኘት ጀመሩ፤ ከኮሮና ቫይረስ ጋር የተያያዙ ልዩ ዜናዎች በሚወጡበት ቀን ደግሞ ይህ አኃዝ ከአራት ሚሊዮን ተኩል አልፏል። የ2020 የመታሰቢያው በዓል በተከበረበት በሚያዝያ 7 ድረ ገጹ ከሰባት ሚሊዮን የሚበልጡ ጎብኚዎችን አስተናግዷል፤ ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ ድረ ገጹን የጎበኙት ለዚያ ቀን የተዘጋጀውን ልዩ የማለዳ አምልኮ ፕሮግራምና የመታሰቢያውን በዓል ንግግር ለመመልከት ነው።
በዎርዊክ፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ውስጥ የሜፕስ ፕሮግራሚንግ ዲፓርትመንት የበላይ ተመልካች ሆኖ የሚያገለግለው ወንድም ካላይቭ ማርቲን እንዲህ ብሏል፦ “በየዓመቱ በመታሰቢያው በዓል ወቅት ብዙ ሰዎች በዓሉ የሚከበርባቸውን ቦታዎች ለማወቅ jw.orgን ይጎበኛሉ። ዘንድሮ ግን ፍላጎት ያሳዩ በርካታ ሰዎች ከጉባኤዎች ጋር አንድ ላይ ተሰብስበው በዓሉን ማክበር ስለማይችሉ የ2020 ልዩ ንግግርና የመታሰቢያው በዓል ንግግር ከ500 በሚበልጡ ቋንቋዎች ድረ ገጹ ላይ እንዲወጣ አደረግን። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች እነዚህ ፕሮግራሞች ተመልክተዋል ወይም አውርደዋል። በዚህ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ወቅት ድረ ገጹን የሚጎበኙ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ መጨመሩ ለይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ሰዎችም ጭምር መንፈሳዊ ትምህርትና መጽናኛ በመስጠት ረገድ jw.org ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ያሳያል።”
አብዛኞቹ ሰዎች ድረ ገጹን የሚጎበኙት ከጤና፣ በሽታን ከመከላከል እንዲሁም ከውጥረትና ከጭንቀት ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ለማግኘት ነው፤ ደግሞም ይህ የሚያስገርም አይደለም። ከመጨረሻዎቹ ቀናትና በራእይ ምዕራፍ 6 ላይ ከተጠቀሱት አራት ፈረሰኞች ጋር የተያያዘ መረጃ ለማግኘት ድረ ገጹን የጎበኙ ሰዎችም ብዙ ናቸው።
መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ጥያቄ በሚያቀርቡ ሰዎች ቁጥር ረገድ የታየው ጭማሪም ትኩረት የሚስብ ነው። በአብዛኛው በቀን 250 የሚያህል ጥያቄ ይቀርባል። በመጋቢት ወር ግን የ40 በመቶ ጭማሪ በማሳየት በቀን 350 ጥያቄዎች ቀርበዋል፤ ይህ ሲባል በወር 11,000 ጥያቄዎች ቀርበዋል ማለት ነው። በመታሰቢያው በዓል ቀንና በማግስቱ ማለትም በ48 ሰዓት ውስጥ ከ1,000 የሚበልጡ ጥያቄዎች ቀርበዋል።
ኢየሱስ መንፈሳዊ ነገሮችን የተጠሙ ሰዎች ደስተኛ እንደሚሆኑ ተናግሯል። (ማቴዎስ 5:3) ብዙ ሰዎች በዚህ አስጨናቂ ጊዜ መጽናኛና መንፈሳዊ ድጋፍ ለማግኘት ወደ ይሖዋና ወደ ድርጅቱ ዘወር በማለታቸው በጣም ተደስተናል።—2 ቆሮንቶስ 1:3, 4