በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ታኅሣሥ 28, 2022
ዓለም አቀፋዊ ዜና

JW.ORG አሥር ዓመት አስቆጠረ—ክፍል 1

መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቪዲዮዎችንና ጽሑፎችን በዲጂታል ፎርማት ማግኘት ተቻለ

JW.ORG አሥር ዓመት አስቆጠረ—ክፍል 1

ከዚህ በፊት ሪፖርት እንደተደረገው የይሖዋ ምሥክሮች ይፋዊ ድረ ገጽ ከከፈቱ 2022 ላይ 25 ዓመት ሆኗቸዋል። ተሻሽሎ የቀረበው jw.org የተለቀቀው ግን የዛሬ አሥር ዓመት ነሐሴ 27, 2012 ነው። አዲሱ jw.org በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች ያስገኛቸውን ጥቅሞች በሦስት ተከታታይ ክፍሎች አጠናቅረን አቅርበናል።

ቪዲዮዎች፦ በ2012 በተደረጉ የክልል ስብሰባዎች ላይ የይሖዋ ወዳጅ ሁን የተባለው ተከታታይ ቪዲዮ ሁለት ክፍሎች በዲቪዲ ወጡ። ይሁንና ዲቪዲዎች ተመራጭነታቸው እየቀነሰ ሄደ፤ ለማዘጋጀት የሚያስፈልገው ወጪ ደግሞ ቀላል የሚባል አልነበረም። በአዲስ መልክ የቀረበው ድረ ገጽ በ2012 አጋማሽ ኢንተርኔት ላይ ሲለቀቅ ቪዲዮዎችን ለማሰራጨት የሚያስችል ይበልጥ ውጤታማ መድረክ ተገኘ። በመሆኑም ጥር 2013 ሁልጊዜ ጸልይ የሚል ርዕስ ያለው የይሖዋ ወዳጅ ሁን ቀጣይ ቪዲዮ የወጣው jw.org ላይ ነው። ከዚያ ጊዜ አንስቶ በዚህ ዓምድ ሥር ከ40 በላይ ቪዲዮዎች ተለቅቀዋል።

መጽሐፍ ቅዱስን መማር የሚኖርብን ለምንድን ነው? የተሰኘው ቪዲዮም በ2013 ኢንተርኔት ላይ ተለቀቀ። ይህ ቪዲዮ ለአገልግሎት የምንጠቀምበት ሁነኛ መሣሪያ ሆኗል፤ በኋላም በማስተማሪያ መሣሪያዎቻችን ውስጥ ተካትቷል። ይህ ቪዲዮ ከወጣ ወዲህ በ​jw.org የሚሰራጩ ቪዲዮዎች ለስብከቱ ሥራችን ትልቅ ግብአት ሆነዋል። ለምሳሌ ያህል ነሐሴ 2014 jw.org​ን የሚያስተዋውቅ ትራክት ለማሰራጨት በተደረገው ዘመቻ ወቅት 15 ሚሊዮን ገደማ ቪዲዮዎች ታይተዋል ወይም ከኢንተርኔት ላይ ወርደዋል።

jw.org​ን በማበልጸጉ ሥራ ከተካፈሉት ወንድሞች አንዱ እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ ወደፊት ለሚመጡ ነገሮች እንዴት እንደሚያዘጋጀን መመልከት እምነት የሚያጠናክር ነው። ቪዲዮዎችን ለማሰራጨት ብለን ያስጀመርነው አዲስ ዘዴ ወደፊት ምን ያህል ወሳኝ እንደሚሆን በወቅቱ የተገነዘብነው ነገር አልነበረም።” ለምሳሌ፣ ጥቅምት 2014 JW ብሮድካስቲንግ ተለቀቀ፤ በዚያ ወር ከ37 ሚሊዮን በላይ ቪዲዮዎች ወርደዋል። ኮቪድ-19 በ2020 ሲጀምር ደግሞ jw.org ላይ ቪዲዮ የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ጭማሪ አሳየ። በ2022 እስካሁን ድረስ በየወሩ በአማካይ ከ260 ሚሊዮን በላይ ቪዲዮዎች ከ​jw.org ላይ ይወርዳሉ።

ኤሌክትሮኒክ ጽሑፎች፦ ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ፣ ብዙ ሰዎች በወረቀት ከማንበብ ይልቅ ኢንተርኔት ላይ ወይም የሞባይል አፕሊኬሽኖችን ተጠቅመው ማንበብን ምርጫቸው አድርገዋል። ድረ ገጹ በ2012 ይፋ ከመሆኑ በፊት ሰዎች መጽሔቶቻችንን በአብዛኛው የሚያገኙት በወረቀት ታትመው ነው፤ ከዚያ ወዲህ ግን አንባቢዎች ኢንተርኔት ላይ እነዚህን ጽሑፎች ማንበብ ችለዋል። የኤሌክትሮኒክ ጽሑፎችን ለማዘጋጀት የሚከናወነው ሥራ በኋላ ላይ በ2013 ለጀመረው የ​JW ላይብረሪ አፕሊኬሽን መንገድ ከፈተ። አፕሊኬሽኑ ከድረ ገጹ ጋር ተመሳስሎ የተሠራ ሲሆን ኤሌክትሮኒክ ጽሑፎችን ለማንበብና ለማጥናት በጣም ምቹ ነው።

ቀደም ሲል በክልል ስብሰባዎች ላይ የሚለቀቁ ጽሑፎች ድረ ገጹ ወይም አፕሊኬሽኑ ላይ የሚወጡት በቀጣዩ ዓመት ጥር ወር ላይ ነበር። በ2015 በተካሄዱት የክልል ስብሰባዎች ላይ ግን አዲስ የወጡትን ጽሑፎች ኤሌክትሮኒክ ቅጂ ወዲያውኑ ማውረድ እንደሚቻል የሚገልጽ አስደሳች ማስታወቂያ ተነገረ፤ ይህን ተከትሎም ተሰብሳቢዎች በዚያ ዓመት የወጡትን ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት እና ወደ ይሖዋ ተመለስ የተሰኙትን ጽሑፎች እንዲሁም እውነተኛ ፍቅር ምንድን ነው? የተሰኘውን ቪዲዮ ወዲያው ማውረድ ችለዋል። በቀጣዩ ዓመት በግንቦት 2016 የ​JW ብሮድካስቲንግ ፕሮግራም ላይ ወንድም አንቶኒ ሞሪስ ወጣቶች የሚጠይቋቸው 10 ጥያቄዎችና መልሶቻቸው (እንግሊዝኛ) የሚለው ብሮሹር መውጣቱን ሲያበስር ኤሌክትሮኒክ ቅጂው ኢንተርኔት ላይ መለቀቁንና አንባቢዎች ወዲያውኑ ማውረድ እንደሚችሉ አሳውቆ ነበር። ዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር በተመሳሳይ ቀንና ሰዓት አዲስ ጽሑፍ ሲያገኝ ይህ የመጀመሪያው ነው።

የይሖዋ ድርጅት ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን ለማቀላጠፍ ሲል ዘመኑ የወለደውን ቴክኖሎጂ ሲጠቀም ኖሯል። አሁንም ‘በተገቢው ጊዜ ምግብ’ ለማቅረብ jw.org ድረ ገጽን እንዴት ውጤታማ በሆነ መንገድ እየተጠቀመበት እንዳለ ማየት ያስደንቃል።—ማቴዎስ 24:45

  • በየወሩ የወረዱ ቪዲዮዎች

  • ዕለታዊ የድረ ገጹ ጎብኚዎች (የየወሩ)

  • ሁልጊዜ ጸልይ ተለቀቀ፣ ጥር 2013

  • JW ላይብረሪ አፕሊኬሽን ተለቀቀ፣ ጥቅምት 2013

  • jw.org​ን የሚያስተዋውቅ ትራክት ለማሰራጨት ዓለም አቀፍ ዘመቻ ተካሄደ፣ ነሐሴ 2014

  • JW ብሮድካስቲንግ ተለቀቀ፣ ጥቅምት 2014

  • የክልል ስብሰባዎች ላይ የሚወጡ አዳዲስ ነገሮች ወዲያው ኢንተርኔት ላይ መለቀቅ ጀመሩ፣ ግንቦት 2015

  • ወጣቶች የሚጠይቋቸው 10 ጥያቄዎችና መልሶቻቸው (እንግሊዝኛ) በዓለም ዙሪያ በአንድ ቀን ተለቀቀ፣ ግንቦት 2016