ጥቅምት 17, 2024
ዩናይትድ ስቴትስ
ፍሎሪዳ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ሚልተን በተባለው አውሎ ነፋስ ተመታች
ጥቅምት 9, 2024 ሚልተን የተባለውና እርከን 3 ደረጃ የተሰጠው አውሎ ነፋስ በዩናይትድ ስቴትስ የፍሎሪዳን ባሕረ ሰላጤ የመታ ሲሆን በመላው የፍሎሪዳ ግዛት ላይ ጉዳት አድርሷል። ይህ ኃይለኛ አውሎ ነፋስ የተከሰተው ኸሊን የተባለችው አውሎ ነፋስ ይህንኑ ክልል ካጠቃች ሁለት ሳምንት እንኳ ሳይሞላ ነው፤ ሚልተን ተጨማሪ መጥለቅለቅና ውድመት አስከትሏል። ሚልተን በሰዓት 289 ኪሎ ሜትር የሚጓዝ ነፋስ አስነስቷል። በባሕሩ ዳርቻ በሚገኙ በበርካታ አካባቢዎች፣ የዝናቡ መጠን እስከ 45 ሴንቲ ሜትር በመድረሱና 3 ሜትር ድረስ ከፍታ የነበረው ማዕበል በመነሳቱ ኃይለኛ የጎርፍ መጥለቅለቅ ተከስቷል።
በተጨማሪም፣ ሚልተን በደቡባዊና ማዕከላዊ ፍሎሪዳ፣ ሌሎች ከ38 ያላነሱ ኃይለኛ ነፋሶችን በማስነሳት መጠነ ሰፊ ውድመት አስከትሏል። ወደ 80,000 የሚጠጉ ሰዎች ኤሌክትሪክ ተቋርጦባቸዋል፤ እንዲሁም ቢያንስ 24 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ላይ የደረሰ ጉዳት
በአደጋው የሞተ ወንድም ወይም እህት የለም
2 አስፋፊዎች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል
4 አስፋፊዎች መጠነኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል
9,949 አስፋፊዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል
16 ቤቶች ወድመዋል
235 ቤቶች ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል
1,398 ቤቶች ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል
1 የስብሰባ አዳራሽ ቀላል ጉዳት ደርሶበታል
30 የስብሰባ አዳራሾች ኤሌክትሪክ ተቋርጦባቸዋል እንዲሁም አገልግሎት መስጠት አይችሉም
የእርዳታ እንቅስቃሴ
ሚልተን አካባቢውን ከመምታቱ ከሁለት ቀናት በፊት የዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ቢሮ፣ አውሎ ነፋሱ በሚጓዝበት አቅጣጫ ላይ ለሚገኙ ከ800 የሚበልጡ ጉባኤዎች ደብዳቤ ልኮ ነበር። ደብዳቤው አካባቢውን ለቅቀው መውጣት ለሚፈልጉ የሚጠቅሙ መረጃዎችን የያዘ ነበር
የወረዳ የበላይ ተመልካቾችና በአካባቢው ያሉ ሽማግሌዎች ኸሊን እና ሚልተን በተባሉት አውሎ ነፍሶች ለተጎዱት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መንፈሳዊና ቁሳዊ ድጋፍ እያደረጉ ነው
በሁለቱም አውሎ ነፋሶች ለደረሰው አደጋ የሚከናወነውን የእርዳታ ሥራ የሚያስተባብሩ 3 የአደጋ ጊዜ እርዳታ ኮሚቴዎች ተቋቁመዋል
በጆርጂያ እና በሳውዝ ካሮላይና፣ ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች የተፈናቀሉ ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን ተቀብለው በማስተናገድ ፍቅራቸውን አሳይተዋቸዋል
ይሖዋ በቅርቡ በተከሰቱት በእነዚህ አውሎ ነፋሶች ጉዳት ለደረሰባቸው ሁሉ ምንጊዜም “መጠጊያና መሸሸጊያ” ያዘጋጅላቸው ዘንድ መላው የወንድማማች ማኅበራችን ይጸልያል።-ኢሳይያስ 4:6