ጥር 5, 2024
ደቡብ አፍሪካ
የዛሬ 50 ዓመት በደቡብ አፍሪካ በዘር ክፍፍል ላይ የተገኘ “መለኮታዊ ድል”
የይሖዋ ምሥክሮች እሁድ፣ ጥር 6, 1974 በደቡብ አፍሪካ ታሪካዊ የሆነ ትልቅ ስብሰባ አድርገው ነበር። ከተለያየ ዘር የተውጣጡ 33,408 ተሰብሳቢዎች “መለኮታዊ ድል” በተባለው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ የመጨረሻ ፕሮግራም ላይ ለመታደም በጆሃንስበርግ በሚገኘው ራንድ ስታዲየም ተሰበሰቡ። ይህ ስብሰባ የተደረገው የዛሬ 50 ዓመት ነበር።
ከ1948 ጀምሮ በደቡብ አፍሪካ ሥራ ላይ የዋለው የአፓርታይድ ሕግ የተለያየ ዘር ያላቸው ሰዎች እንዳይቀላቀሉ ያዝዝ ነበር። ይህም የይሖዋ ምሥክሮች ለሳምንታዊና ለትላልቅ ስብሰባዎች በሚሰበሰቡበት መንገድ ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል። በአሁኑ ጊዜ የደቡብ አፍሪካ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል ሆኖ የሚያገለግለው ወንድም አልፍሬድ ፋትስዋና በ1974 ገና የአሥር ዓመት ልጅ ነበር። በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ሲያስታውስ “በአፓርታይድ ዘመን፣ የተለያየ ዘር ያላቸውን ሰዎች አንድ ላይ ማየት እንግዳ ነገር ነበር” በማለት ተናግሯል።
ብሔራት አቀፍ ስብሰባው የተደረገው ከጥር 2 እስከ 6, 1974 ነበር። የተለያየ ዘር ያላቸው ሰዎች እንዳይቀላቀሉ በሚያዝዘው ሕግ ምክንያት፣ ሙሉውን ፕሮግራም አንድ ቦታ ላይ ማድረግ አልተቻለም። ለአራት ቀን ተኩል ያህል፣ ተሰብሳቢዎች እንደየዘራቸውና እንደየቋንቋቸው በአነስተኛ ቡድኖች ተከፋፍለው በተለያዩ ቦታዎች ስብሰባውን ተካፈሉ። ሆኖም እሁድ ከሰዓት ማለትም በስብሰባው የመጨረሻ ክፍል ላይ ሁሉም ተሰብሳቢዎች በራንድ ስታዲየም አንድ ላይ እንዲሰበሰቡ ፈቃድ ተሰጠ፤ የተለያየ ዘር ያላቸው ሰዎች በጆሃንስበርግ አንድ ላይ እንዲሰበሰቡ የሚፈቀድበት ብቸኛው ቦታ ይህ ነበር።
እሁድ ከ6 ሰዓት ጀምሮ በተለያዩ ቦታዎች የነበሩት ተሰብሳቢዎች በአውቶቡስ፣ በመኪናና በባቡር ተሳፍረው ወደ ራንድ ስታዲየም መጉረፍ ጀመሩ። ፕሮግራሙ በእንግሊዝኛ እንዲቀርብና በተመሳሳይ ጊዜ ወደ ሴሶቶ፣ አፍሪካንስ፣ ዙሉ እና ፖርቱጋልኛ እንዲተረጎም ዝግጅት ተደረገ።
ስታዲየሙ ከመሙላቱ የተነሳ ብዙዎች ሙሉውን ፕሮግራም የተከታተሉት ቆመው ነው። የደቡብ አፍሪካ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ኬዝ ዊጊል በዚህ ስብሰባ ላይ በተገኘበት ጊዜ 23 ዓመቱ ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “በጣም አስደናቂ ስብሰባ ነበር፤ ብዙዎች ሁላችንም አንድ ላይ ለአምልኮ እንድንሰበሰብ ያቀርቡ ለነበሩት ጸሎት መልስ አገኙ። በእምነት አንድ ነን፤ በተመሳሳይ መሠረታዊ ሥርዓቶች እንመራለን፤ በስብሰባው ወቅት ደግሞ እርስ በርስ ከፋፍሎን ከነበረው ሕግ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ነፃ መሆን ቻልን። ከወንድሞቼና ከእህቶቼ ጋር በእርግጥም አንድ እንደሆንኩ ተሰማኝ።”
“መለኮታዊ ድል” የተባለው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ በ1974 በተካሄደበት ወቅት በደቡብ አፍሪካ 25,000 ገደማ አስፋፊዎች ነበሩ። በዛሬው ጊዜ በመላው አገሪቱ ያሉ ወደ 100,000 የሚጠጉ ወንድሞችና እህቶች ይሖዋን በአንድነት እያመለኩ ነው። ከ1974 አንስቶ በደቡብ አፍሪካ በርካታ ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች ተደርገዋል። ከእነዚህ መካከል በቅርቡ ማለትም በ2019 የተደረገው “ፍቅር ለዘላለም ይኖራል”! የተባለው ስብሰባ ይገኝበታል። በዚህ ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ የተለያየ ቋንቋና ባሕል ያላቸው ወደ 60,000 የሚጠጉ ሰዎች ተገኝተዋል።
በ1974 የተደረገውን በዘርና በኢኮኖሚ ክፍፍል ላይ ድል የተገኘበት ታሪካዊ ስብሰባ መለስ ብለን ማስታወሳችን ደስታ ይሰጠናል። ከአድልዎ ነፃ ለሆነው ለአምላካችን ለይሖዋ በአንድነት ውዳሴ በሚያቀርብ ዓለም አቀፋዊ የወንድማማች ማኅበር ውስጥ መታቀፋችን ልዩ መብት እንደሆነ ይሰማናል።—የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35