ሐምሌ 19, 2019
ዴንማርክ
ቲኦክራሲያዊ እመርታ፦ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በአይስላንድኛ ወጣ
የበላይ አካል አባል የሆነው ወንድም ስቲቨን ሌት ሐምሌ 19, 2019 በኮፐንሃገን፣ ዴንማርክ በተደረገው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ላይ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በአይስላንድኛ መውጣቱን ሞቅ ባለ መንገድ አበሰረ።
ስብሰባው በተካሄደበት ቀን ዓርብ ጠዋት ላይ ሊቀ መንበሩ በአይስላንድኛ ቋንቋ የሚያገለግሉ በሙሉ ምሳ ሰዓት ላይ በስታዲየሙ ውስጥ በሚገኝ አንድ ክፍል በሚደረገው ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ጋብዟቸው ነበር። በዚህ ልዩ ስብሰባ ላይ ወንድም ሌት 341 ለሚያህሉት ወንድሞችና እህቶች አዲሱን መጽሐፍ ቅዱስ ሰጥቷቸዋል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሥራ በአይስላንድ ውስጥ ለበርካታ መቶ ዓመታት ትልቅ ቦታ ሲሰጠው ኖሯል። በ1540 ኦዱር ጎትስካልክሰን የመጀመሪያውን የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም በአይስላንድኛ አሳተመ። አይስላንድኛ የሚናገሩ የእምነት አጋሮቻችን ከ2010 ወዲህ የሚጠቀሙት በአይስላንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ድርጅት የታተመውን የ21ኛው ክፍለ ዘመን መጽሐፍ ቅዱስ ነበር። አሁን ግን በአይስላንድኛ ጉባኤዎች ውስጥ ያሉ ወንድሞችና እህቶች በክልላቸው ውስጥ ላሉት ከ300,000 በላይ የሚሆኑ የቋንቋው ተናጋሪዎች ምሥራቹን ሲሰብኩ አዲሱን መጽሐፍ ቅዱስ ለመጠቀም ጓጉተዋል።
በትርጉም ቡድኑ ውስጥ የነበረ አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን ወደ አይስላንድኛ የመተርጎሙ ሥራ አራት ዓመት ገደማ ወስዷል። ይህን ትርጉም ልዩ የሚያደርገው የይሖዋን ስም ወደ ትክክለኛው ቦታ መልሶ ማስገባቱ ነው። ይህም በዮሐንስ 17:26 ላይ ከሚገኘው ኢየሱስ ‘ስምህን አሳውቄአቸዋለሁ፤ ደግሞም አሳውቃለሁ’ በማለት ካቀረበው ጸሎት ጋር የሚስማማ ነው።”
ምሥራቹን በመላው ምድር እንድንሰብክ የተሰጠንን ተልእኮ ስንወጣ የይሖዋ በረከት ያልተለየን በመሆኑ አመስጋኞች ነን፤ የትርጉም ሥራችን ይህን ኃላፊነት ለመወጣት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ወደፊትም በርካታ ሰዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ “ስለ አምላክ ታላቅ ሥራ” ለማወቅ እንዲነሳሱ እንጸልያለን።—የሐዋርያት ሥራ 2:11