ጥር 24, 2024
ጀርመን
ሲሞን አርኖልድ ሊብስተር ወጣቶችን ለማስተማር ላደረገችው ጥረት የጀርመን መንግሥት የአገሪቱን ከፍተኛ ሽልማት ሰጣት
ታኅሣሥ 15, 2023 እህት ሲሞን አርኖልድ ሊብስተር፣ ከጀርመን ፌዴራል ሪፑብሊክ ሽልማት ተቀብላለች። ይህ ሽልማት፣ የጀርመን መንግሥት በማኅበረሰቡ ውስጥ ብዙዎችን የሚጠቅም ተግባር ላከናወኑ ሰዎች የሚሰጠው ሽልማት ነው። በሻንቤሪ፣ ፈረንሳይ በተካሄደው ሥነ ሥርዓት ላይ ሽልማቱን ለሲሞን ያበረከቱላት ቆንስላ ጄኔራል ቶማስ ፕርብስት ናቸው። አሁን የ93 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ የሆነችው ሲሞን ይህ እውቅና የተሰጣት የናዚ የግፍ ድርጊትም ሆነ የዚህን ሥርዓት የጥላቻና የጭካኔ ርዕዮተ ዓለም የተቃወሙት ሰዎች እንዳይረሱ ላደረገችው ጥረት ነው።
ሲሞን እስከ ዛሬ ድረስ በ25 አገራት ውስጥ ንግግር አቅርባለች። ወደ 65,000 የሚጠጉ ታዳሚዎች በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ የተገኙ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ተማሪዎችና መምህራን ይገኙበታል። ሲሞን ዕድሜዋ ቢገፋም በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ንግግር ማቅረቧን ቀጥላለች፤ ከወጣት ታዳሚዎች ለሚነሱላት ጥያቄዎች መልስ ትሰጣለች እንዲሁም በእነሱ ዕድሜ ሳለች የተገነዘበቻቸውን ቁም ነገሮች ታካፍላቸዋለች። ከእነዚህ ስብሰባዎች በአንዱ ላይ የተገኘ ተማሪ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “የሲሞን ታሪክ፣ አንድን ነገር ከልባችን ማመናችን ከፍተኛ ኃይልና ብርታት እንደሚሰጠን አስተምሮኛል።”
ቆንስላ ጄኔራል ቶማስ ፕርብስት ለሲሞን ሽልማቱን ባበረከቱበት ወቅት እንዲህ በማለት ተናግረዋል፦ “ስለደረሰብሽ ከባድ መከራ ለሌሎች መተረክ ብርታት የሰጠሽ መሆኑ እጅግ የሚያስደንቅ ነው። ሁልጊዜም ታሪክሽን የምትናገሪው በሐቀኝነት፣ በደግነትና ለወደፊቱ ጊዜ ተስፋ በሚሰጥ መንገድ ነው። በመሆኑም ለአንቺ ታላቅ አክብሮት አለኝ።”
በናዚ አገዛዝ ወቅት፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች እንዳጋጠማቸው ሁሉ ሲሞንና ቤተሰቧም አሰቃቂ መከራ ደርሶባቸዋል። ሲሞን 12 ዓመት ሲሆናት ከቤተሰቧ ተነጥላ በኮንስታንዝ፣ ጀርመን ወደሚገኘው ፎን ቨሰንበርግ ጠባይ ማረሚያ ተላከች። ሆኖም ናዚዎች በዚህ የተሃድሶ ትምህርት ቤት ውስጥ አቋሟን ለማስለወጥ ያደረጉት ጥረት አልተሳካም። ሲሞን የገለልተኝነት አቋሟን ለማላላት ፈቃደኛ ባለመሆኗ ውርደት ደርሶባታል፣ ምግብ ተከልክላለች፣ የጉልበት ሥራ እንድትሠራ ተደርጋለች እንዲሁም ለሁለት ዓመት ገደማ ከማንም ጋር እንዳትነጋገር ታግዳለች። ሲሞን ስለዚያ ጊዜ ስትናገር “ይሖዋ ደግፎ ስላቆመኝ ፍጹም አቋሜን መጠበቅ ቻልኩ” ብላለች።
ሲሞን ያስመዘገበችውን የታማኝነት ታሪክ እና ለአባታችን ለይሖዋ አምላክ ክብር ለማምጣት የምታደርገውን ጥረት በእጅጉ እናደንቃለን።—ማቴዎስ 5:16