በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መስከረም 19, 2019
ጋቦን

በጋቦን የተካሄደ ልዩ የስብከት ዘመቻ

በጋቦን የተካሄደ ልዩ የስብከት ዘመቻ

በጋቦን በሚገኙ እምብዛም ያልተሰበከባቸው ቦታዎች ላሉ ሰዎች ምሥራቹ እንዲደርስ ለማድረግ የካሜሩን ቅርንጫፍ ቢሮ ከሰኔ 1 እስከ ነሐሴ 31, 2019 ልዩ የስብከት ዘመቻ እንዲካሄድ ዝግጅት አድርጎ ነበር። የዘመቻው ዋና ዓላማ ብዙ ነዋሪዎች ባሉባቸው የጋቦን አሥር ከተሞች ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ምሥራቹን መስበክ ነው፤ ከተሞቹ ሊብረቪል፣ ላምባሪኒ፣ ሙዊላ፣ ማኮኩ፣ ሞዋንዳ፣ ቺባንጋ፣ ኦዬም፣ ኩላሙቱ፣ ፍራንስቪል እና ፑር ዠንቲ ናቸው። በዚህ ዘመቻ ከቤልጅየም፣ ከካናዳ፣ ከዩናይትድ ስቴትስ እና ከፈረንሳይ የመጡ 400 ፈቃደኛ ሠራተኞች ስለተካፈሉ ዘመቻው ዓለም አቀፋዊ ይዘት ነበረው።

ጋቦን ከሁለት ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ይኖሩባታል። ሰማንያ በመቶ ገደማ የሚሆነው የጋቦን ነዋሪ የአገሪቱ የሥራ ቋንቋ የሆነውን ፈረንሳይኛ መናገር ይችላል፤ ሠላሳ በመቶ ገደማ የሚሆነው ሕዝብ ደግሞ ከፈረንሳይኛ በተጨማሪ የአፍ መፍቻ ቋንቋው የሆነውን ፋንግ ይናገራል። በመሆኑም ዘመቻው የተካሄደው በሁለቱም ቋንቋዎች ነው።

ቢሲጌ በሚባለው የሊብረቪል ክፍል የሚኖርና ለመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ፍላጎት ያለው የፋንግ ተናጋሪ የሆነ አንድ ግለሰብ “የአምላክን መልእክት በራሴ ቋንቋ ስሰማ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር” ብሏል።

በዘመቻው የተካፈለች አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “ይህ ዘመቻ በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ያለው ፍቅርና አንድነት ጎልቶ እንዲታይ አድርጓል። ወንድሞችና እህቶች አሳቢ፣ እንግዳ ተቀባይ፣ ለጋስ፣ የሚያበረታቱና በጣም አፍቃሪ ናቸው። ሁኔታው፣ ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ጉባኤ ለነበሩት ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ከእነሱ ጋር ፍጹም አንድነት እንዳለውና አንድ ዓይነት አስተሳሰብ በመያዝ በአንድ ሐሳብና በአንድ ፍቅር እንደሚኖር የተናገረውን ሐሳብ እንዳስታውስ አድርጎኛል።”—ፊልጵስዩስ 2:2