የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ታካሚዎች በአብዛኛው ቶሎ ያገግማሉ
አውስትራሊያ፦ “በሃይማኖታቸው ምክንያት ደም የማይወስዱ የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ታካሚዎች ከሌሎች ታካሚዎች ይበልጥ ቶሎ ያገግማሉ።”—ዘ ሲድኒ ሞርኒንግ ሄራልድ ጥቅምት 2, 2012 እትም
እዚህ ጋዜጣ ላይ የወጣው ሪፖርት በሲድኒ ዩኒቨርሲቲ፣ የሲድኒ የሕክምና ኮሌጅ ውስጥ የሚሠሩት ፕሮፌሰር ጄምስ ኢዝቢስተር የተናገሩትን ሐሳብ ጠቅሷል። ሪፖርቱ እንዲህ ይላል፦ “ፕሮፌሰር ኢዝቢስተር እንደተናገሩት ሐኪሞች የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ታካሚዎችን ሲያክሙ ብዙ ደም እንዳይፈስ ይበልጥ ይጠነቀቃሉ። በዚህም የተነሳ የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ታካሚዎች፣ በቀዶ ጥገና ወቅት ደም ከሚወስዱ ታካሚዎች አንጻር ሲታይ በሕይወት የመትረፍ አጋጣሚያቸው ሰፊ ነው፤ ሆስፒታል ውስጥ እና የጽኑ ሕሙማን ክፍል ውስጥ የሚቆዩበት ጊዜም አጭር ነው።”
እንዲህ ዓይነት አመለካከት ያላቸው ፕሮፌሰር ኢዝቢስተር ብቻ አይደሉም። የልብ ቀዶ ሕክምና ያደረጉ የይሖዋ ምሥክር ታካሚዎችን በተመለከተ አርካይቭስ ኦቭ ኢንተርናል ሜዲሲን የተባለው መጽሔት የነሐሴ 13-27, 2012 እትም እንዲህ ይላል፦ “ደም ከወሰዱ ታካሚዎች አንጻር የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ታካሚዎች ከሕክምናው ጋር ተያይዘው የሚፈጠሩ ከባድ ችግሮች ብዙ ጊዜ አያጋጥሟቸውም፤ የሆስፒታል ቆይታቸውም ቢሆን አጭር ነው።”