ለቤተሰብ | የወላጅ ሚና
ልጃችሁ ሕይወቷን የማጥፋት ሐሳብ ቢኖራት
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ፣ ሕይወታቸውን ማጥፋት የሚፈልጉ ታዳጊዎች ቁጥር በአንዳንድ አገራት በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ ነው። ምክንያቱ ምን ይሆን? የእናንተስ ልጅ እንዲህ የማድረግ ሐሳብ ይኖራት ይሆን? a
በዚህ ርዕስ ውስጥ
ወላጆች ይህ ጉዳይ ሊያሳስባቸው የሚገባው ለምንድን ነው?
ከ2009 እስከ 2019 ባሉት ዓመታት ውስጥ በዩናይትድ ስቴትስ፣ የመንፈስ ጭንቀት ምልክቶች የሚታዩባቸው የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ቁጥር በ40 በመቶ አሻቅቧል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ሕይወታቸውን ያጠፉ ሰዎች ቁጥርም ጨምሯል። b የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) በ2021 ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው ደግሞ “በላቲን አሜሪካና በካሪቢያን አገራት በየቀኑ ከ10 የሚበልጡ ታዳጊዎች ራሳቸውን ያጠፋሉ።”
“በዛሬ ጊዜ ያሉ ወጣቶች ከዚህ ቀደም ያልነበሩ ተፈታታኝ ሁኔታዎች እያጋጠሟቸው ነው። . . . እነዚህ ተፈታታኝ ሁኔታዎች በአእምሮ ጤንነታቸው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደሩ ነው።”—ቪቬክ ሙርቲ፣ የአሜሪካ የማኅበረሰብ ጤና ባለሥልጣን
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “የተደቆሰ መንፈስ . . . ኃይል ያሟጥጣል።”—ምሳሌ 17:22
ልጃችሁ እንዲህ ዓይነት ሐሳብ ካላት ማወቅ የምትችሉት እንዴት ነው?
ከዚህ በታች የቀረቡትን ነጥቦች አስቡባቸው።
ያጋጠሟት ነገሮች። ልጃችሁ በሕይወቷ ውስጥ ከባድ ነገር አጋጥሟታል? ለምሳሌ ጓደኞቿ ትተዋታል? ከፍቅር ጓደኛዋ ተለያይታለች? ያሰበችው ሳይሳካ ቀርቷል? ወይስ የምትወደውን ሰው በሞት አጥታለች? ከሆነ ምናልባት ይህ ነገር እናንተ ከምታስቡት በላይ ስሜቷን ጎድቶት ይሆን?
የባሕርይ ለውጥ። ልጃችሁ ከጓደኞቿ ወይም ከቤተሰቧ መራቅ ጀምራለች? በፊት ትወዳቸው የነበሩ ነገሮች ብዙም አያስደስቷትም? የምትወዳቸውን ዕቃዎቿን ለሌሎች ሰጥታለች?
የምትናገራቸው ነገሮች። ልጃችሁ ስለ ሞት ማውራት ጀምራለች? አሊያም “ብሞት ይሻለኛል” እንደሚሉ ዓይነት አገላለጾችን ትጠቀማለች? በእናንተ ላይ ሸክም መሆን እንደማትፈልግ ትናገራለች?
በእርግጥ አንዳንዱ ነገር እንዲሁ ‘እንዳመጣላት’ የተናገረችው ሊሆን ይችላል። (ኢዮብ 6:3) ሆኖም የምትናገረው ነገር እርዳታ እንደሚያስፈልጋት የሚጠቁም ምልክትም ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ልጃችሁ ስለ ሞት የምትናገረውን ማንኛውንም ነገር አቅልላችሁ አትመልከቱት።
ልጃችሁ ራሷን ለማጥፋት አስባ እንደምታውቅ ከነገረቻችሁ “ይህን እርምጃ መቼ ለመውሰድ ነው ያሰብሽው? በምን መንገድ ሕይወትሽን እንደምታጠፊስ አስበሻል?” ብላችሁ ጠይቋት። የምትሰጠው መልስ ቶሎ እርምጃ መውሰድ እንዳለባችሁ የሚጠቁማችሁ ሊሆን ይችላል።
“እንደ ወላጅ መጠን ልጆቻችን ያልጠበቅነውን መልስ እንዳይሰጡን ስለምንፈራ ጥያቄዎችን ከመጠየቅ ወደኋላ እንል ይሆናል። ሆኖም የሚነግሩን ዓይነት ስሜት ውስጣቸው ካለ፣ ብናውቀው የተሻለ እንደሆነ ጥርጥር የለውም።”—ሳንድራ
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “የሰው ሐሳብ በጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ እንዳለ ውሃ ነው፤ ይሁን እንጂ ማስተዋል ያለው ሰው ይቀዳዋል።”—ምሳሌ 20:5 የ1980 ትርጉም
ልጃችሁ ራሷን ለማጥፋት እንደምታስብ ብታውቁ ምን ማድረግ ትችላላችሁ?
ልጃችሁ ስሜቷን አውጥታ እንድትነግራችሁ በትዕግሥት ጥረት አድርጉ። በመጀመሪያ እውነቱን ስለነገረቻችሁ አመስግኗት። ከዚያም እንዲህ ልትሏት ትችላላችሁ፦ “እስቲ ምን እንዳጋጠመሽ ንገሪኝ? ሰሞኑን ምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ነሽ? ይህ የፈጠረብሽን ስሜት ልታስረጂኝ ትችያለሽ?”
ልጃችሁ የምትሰጠውን ምላሽ በትዕግሥት አዳምጡ። ያስጨነቃት ነገር፣ ያን ያህል የሚያሳስብ እንዳልሆነ ወይም በቀላሉ መፍትሔ እንደሚያገኝ ከመናገር ተቆጠቡ።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገየና ለቁጣ የዘገየ መሆን አለበት።”—ያዕቆብ 1:19
የልጃችሁን ሕይወት ለመታደግ ዕቅድ አውጡ። ልጃችሁ የሚከተሉትን ነጥቦች እንድታስብባቸውና በጽሑፍ እንድታሰፍራቸው እርዷት፦
የአደጋ ምልክቶች። ብዙውን ጊዜ ራሷን የማጥፋት ሐሳብ የሚመጣባት ምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ስትሆን ወይም ምን ስታስብ ነው?
ጠቃሚ እርምጃዎች። ጭንቀቷ ቀለል እንዲላት ወይም አእምሮዋ በሌላ ነገር ላይ እንዲያተኩር የሚረዷት የትኞቹ እንቅስቃሴዎች ናቸው?
የሚረዷት ሰዎች። ልጃችሁ እርዳታ ሲያስፈልጋት ሊያግዟት የሚችሉ ሰዎች አሉ? ለምሳሌ፣ እናንተ ራሳችሁ ወይም እምነት የሚጣልበት ሌላ አዋቂ ሰው ልታግዟት እንደምትችሉ ንገሯት፤ አሊያም ደግሞ የሥነ ልቦና ባለሙያ ወይም ራሳቸውን የማጥፋት ሐሳብ ያላቸውን ለመርዳት የሠለጠኑ ሰዎች ልታማክር እንደምትችል ጠቁሟት።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “የትጉ ሰው ዕቅድ ለስኬት ያበቃዋል።”—ምሳሌ 21:5
ምንጊዜም ንቁ ሁኑ። ልጃችሁ ጥሩ ሁኔታ ላይ ያለች በምትመስልበት ጊዜም ሁኔታዋን በንቃት ተከታተሉ።
“ልጄ ራሱን ለማጥፋት ማሰቡን እንደተወ ሲነግረኝ ችግሩ እንደተስተካከለ አስቤ ነበር። ይህ ግን ትልቅ ስህተት ነው። አንድ ሰው በድንገት ሌላ ችግር ሊያጋጥመውና ራሱን ስለማጥፋት እንደገና ማሰብ ሊጀምር ይችላል።”—ዳንኤል
ልጃችሁ አንድ ወሳኝ እውነት እንድትገነዘብ እርዷት፦ አሁን ያላት ስሜት ጊዜያዊ ነው። ስለ ልጆች የሚናገር አንድ መጽሐፍ “ስሜት እንደ አየር ጠባይ ነው” ይላል። መጽሐፉ አክሎም እንዲህ ይላል፦ “ዝናብ በእውን ያለ ነገር ነው፤ ዝናብ ላይ ቆመን እየበሰበስን ‘ዝናብ የለም’ ብንል ሞኝነት ይሆንብናል። በሌላ በኩል ደግሞ ዝናቡ አባርቶ ፀሐይ እንደማትወጣ ብናስብም፣ የዚያኑ ያህል ሞኝነት ይሆናል።”—The Whole-Brain Child
እንደምትደግፏት አረጋግጡላት። ልጃችሁን እንደምትወዷትና ምንጊዜም ከጎኗ ሆናችሁ እንደምትረዷት ንገሯት። “ይህን ችግር እንድታልፊው በምችለው ሁሉ እረዳሻለሁ” ልትሏት ትችላላችሁ።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “እውነተኛ ወዳጅ ምንጊዜም አፍቃሪ ነው፤ ደግሞም ለመከራ ቀን የተወለደ ወንድም ነው።”—ምሳሌ 17:17