መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አልኮል መጠጥ ምን ይላል? መጠጣት ኃጢአት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
የአልኮል መጠጥ በመጠኑ መጠጣት ኃጢአት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ የወይን ጠጅ የአምላክ ስጦታ እንደሆነና ሕይወትን አስደሳች ሊያደርግ እንደሚችል ይናገራል። (መዝሙር 104:14, 15፤ መክብብ 3:13፤ 9:7) በተጨማሪም የወይን ጠጅ ለመድኃኒትነት ሊያገለግል እንደሚችል ይጠቁማል።—1 ጢሞቴዎስ 5:23
ኢየሱስ በምድር በነበረበት ጊዜ የወይን ጠጅ ጠጥቷል። (ማቴዎስ 26:29፤ ሉቃስ 7:34) ኢየሱስ ከፈጸማቸው ታዋቂ ተአምራት አንዱ በሠርግ ድግስ ላይ ውኃን ወደ ወይን ጠጅ መቀየሩ ሲሆን በዚህ መንገድ ልግስና አሳይቷል።—ዮሐንስ 2:1-10
ከመጠን በላይ መጠጣት የሚያስከትለው አደጋ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ የወይን ጠጅ አንዳንድ ጥቅሞች እንዳሉት የሚናገር ቢሆንም ከመጠን በላይ መጠጣትንና ስካርን ያወግዛል። በመሆኑም አንድ ክርስቲያን የአልኮል መጠጥ የሚጠጣ ከሆነ ከልኩ ማለፍ የለበትም። (1 ጢሞቴዎስ 3:8፤ ቲቶ 2:2, 3) ከልክ በላይ ከመጠጣት እንድንቆጠብ የሚያነሳሱን የተለያዩ ምክንያቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሰዋል፦
የማመዛዘንና ጥሩ ውሳኔ የማድረግ ችሎታን ያዛባል። (ምሳሌ 23:29-35) የሰከረ ሰው የሚከተለውን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ አይችልም፦ “ሰውነታችሁን ሕያው፣ ቅዱስና በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት አድርጋችሁ [አቅርቡ] . . .፤ ይህም የማሰብ ችሎታችሁን ተጠቅማችሁ የምታቀርቡት ቅዱስ አገልግሎት ነው።”—ሮም 12:1
ከመጠን በላይ መጠጣት አንድ ሰው አጉል ድፍረት እንዲያሳይ ያደርጋል፤ እንዲሁም “ትክክል የሆነውን ነገር ለመፈጸም ያለውን ልባዊ ፍላጎት” ያጠፋል።—ሆሴዕ 4:11፤ ኤፌሶን 5:18
ድህነትና ከባድ የጤና እክል ሊያስከትል ይችላል።—ምሳሌ 23:21, 31, 32
ከመጠን በላይ መጠጣትና ስካር አምላክን ያሳዝናል።—ምሳሌ 23:20፤ ገላትያ 5:19-21
ከመጠን አለፈ የሚባለው መቼ ነው?
አንድ ሰው ከመጠን በላይ ጠጥቷል የሚባለው በመጠጣቱ ምክንያት ራሱንም ሆነ ሌሎችን ለጉዳት የሚዳርግ ነገር ሲፈጽም ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው ከሆነ አንድ ሰው ሰክሯል የሚባለው ራሱን ሲስት ሳይሆን እንደ ግራ መጋባት፣ መንገዳገድ፣ ጠበኛ መሆን ወይም አጥርቶ መናገር አለመቻል ያሉት ነገሮች ሲታዩበት ነው። (ኢዮብ 12:25፤ መዝሙር 107:27፤ ምሳሌ 23:29, 30, 33) አንዳንዶች ባይሰክሩም እንኳ ‘ከልክ በላይ በመጠጣት ልባቸው ሸክም ሊበዛበት’ እንዲሁም ከመጠን በላይ መጠጣት ለሚያስከትለው ጉዳት ሊዳረጉ ይችላሉ።—ሉቃስ 21:34, 35
ጨርሶ ከመጠጥ መራቅ
ክርስቲያኖች የአልኮል መጠጥ ጨርሶ መጠጣት የማይኖርባቸው ጊዜ እንዳለም መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፦
ሌሎችን የሚያሰናክል ከሆነ።—ሮም 14:21
የአልኮል መጠጥ መጠጣት በሚኖሩበት አገር የተከለከለ ከሆነ።—ሮም 13:1
አንድ ሰው በመጠኑ መጠጣት ካልቻለ። የአልኮል ሱሰኞች የሆኑ ወይም ከመጠን በላይ የመጠጣት ችግር ያለባቸው ሰዎች ቆራጥ እርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል።—ማቴዎስ 5:29, 30