በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱ ሴቶች ምን እንማራለን?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱ ሴቶች ምን እንማራለን?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በርካታ ሴቶች የተጠቀሱ ሲሆን ከእነሱ ጠቃሚ ትምህርት እናገኛለን። (ሮም 15:4፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) በዚህ ርዕስ ላይ ከእነዚህ ሴቶች የተወሰኑትን በአጭሩ እንመለከታለን። አብዛኞቹ ልንመስለው የሚገባ ጥሩ ምሳሌ ትተውልናል። አንዳንዶቹ ደግሞ የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ይሆኑናል።—1 ቆሮንቶስ 10:11፤ ዕብራውያን 6:12

  ሊያ

 ሊያ ማን ናት? የያዕቆብ የመጀመሪያ ሚስት ናት። ያዕቆብ ታናሽ እህቷን ራሔልንም አግብቷል።—ዘፍጥረት 29:20-29

 ምን አከናውናለች? ሊያ ለያዕቆብ ስድስት ወንዶች ልጆች ወልዳለታለች። (ሩት 4:11) ያዕቆብ ማግባት የፈለገው ሊያን ሳይሆን ራሔልን ነበር። ሆኖም የእነዚህ ሴቶች አባት የሆነው ላባ፣ ያዕቆብ በራሔል ፋንታ ሊያን እንዲያገባ አደረገ። ያዕቆብ፣ እንደተታለለና ሊያን እንዳገባ ሲያውቅ ቅሬታውን ለላባ ነገረው። ላባም ታላቂቱ እያለች ታናሺቱን መዳር በአካባቢያቸው የተለመደ እንዳልሆነ ገለጸለት። ከአንድ ሳምንት በኋላ ያዕቆብ ራሔልንም አገባ።—ዘፍጥረት 29:26-28

 ያዕቆብ ራሔልን ከሊያ አብልጦ ይወዳት ነበር። (ዘፍጥረት 29:30) ይህም ሊያን ስላስቀናት የባሏን ፍቅር ለማግኘት ከእህቷ ጋር መፎካከር ጀመረች። አምላክ የሊያን ስሜት ተረድቶላታል፤ በመሆኑም ስድስት ወንዶች ልጆችና አንዲት ሴት ልጅ እንድትወልድ በማድረግ ባርኳታል።—ዘፍጥረት 29:31

 ከሊያ ምን እንማራለን? ሊያ ወደ አምላክ በመጸለይ በእሱ እንደምትታመን አሳይታለች፤ እንዲሁም በቤተሰቧ ውስጥ ያጋጠሟት ችግሮች አምላክ እየደገፋት እንዳለ የሚያሳየውን ማስረጃ ልብ እንዳትል አላገዷትም። (ዘፍጥረት 29:32-35፤ 30:20) አምላክ ከአንድ በላይ ማግባትን ለተወሰነ ጊዜ ፈቅዶ ነበር፤ ያም ቢሆን የሊያ ሕይወት ቁልጭ አድርጎ እንደሚያሳየው ይህ ዓይነቱ ጋብቻ ብዙ ችግሮች ያስከትላል። የአምላክ ዓላማ ትዳር በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል የሚመሠረት ጥምረት እንዲሆን ነው።—ማቴዎስ 19:4-6

  ሐና

 ሐና ማን ናት? የሕልቃና ሚስት ስትሆን በጥንቷ እስራኤል ትልቅ ቦታ የነበረው የነቢዩ ሳሙኤል እናት ናት።—1 ሳሙኤል 1:1, 2, 4-7

 ምን አከናውናለች? ሐና መሃን በነበረችበት ወቅት መጽናኛ ለማግኘት ወደ አምላክ ዞር ብላለች። የሐና ባል፣ ፍናና የተባለች ሌላ ሚስትም አለችው። ፍናና ልጆች አሏት፤ ሐና ግን ካገባች በኋላ ለረጅም ጊዜ ልጅ አልወለደችም። ፍናና ያለምንም አዘኔታ ትሳለቅባት ነበር፤ በዚህ ጊዜ ሐና አምላክ እንዲያጽናናት ጸልያለች። አምላክ ወንድ ልጅ ከሰጣት ልጁን በማደሪያው ድንኳን (እስራኤላውያን ለአምልኮ የሚጠቀሙበት ከቦታ ቦታ መጓጓዝ የሚችል ድንኳን) እንዲያገለግል እንደምትሰጠው በመግለጽ ስእለት ተሳለች።—1 ሳሙኤል 1:11

 አምላክ የሐናን ጸሎት ሰምቶ ወንድ ልጅ ሰጣት፤ ልጁም ሳሙኤል ተባለ። ሐና ቃሏን በመጠበቅ ገና ትንሽ ልጅ ሳለ ሳሙኤልን በማደሪያው ድንኳን እንዲያገለግል ወሰደችው። (1 ሳሙኤል 1:27, 28) እጅጌ የሌለው ትንሽ ቀሚስ እየሠራች በየዓመቱ ለሳሙኤል ትወስድለት ነበር። ከጊዜ በኋላ አምላክ ሦስት ወንዶችና ሁለት ሴቶች ልጆች በመስጠት ሐናን ባርኳታል።—1 ሳሙኤል 2:18-21

 ከሐና ምን እንማራለን? ሐና ከልቧ መጸለይዋ ያጋጠማትን ችግር ለመቋቋም ረድቷታል። በ1 ሳሙኤል 2:1-10 ላይ የሚገኘው ሐና ያቀረበችው የምስጋና ጸሎት በአምላክ ላይ ጠንካራ እምነት እንደነበራት ያሳያል።

  ሔዋን

 ሔዋን ማን ናት? የመጀመሪያዋ ሴት ናት፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሰችው የመጀመሪያዋ ሴትም እሷ ናት።

 ምን አከናውናለች? ሔዋን፣ አምላክ የሰጠውን ግልጽ ትእዛዝ ጥሳለች። እንደ ባሏ እንደ አዳም ሁሉ ሔዋንም ፍጹም ሰው ናት፤ የመምረጥ ነፃነት እንዲሁም እንደ ፍቅርና ጥበብ ያሉትን የአምላክ ባሕርያት የማንጸባረቅ ችሎታ ተሰጥቷት ነበር። (ዘፍጥረት 1:27) ሔዋን፣ እንዳይበሉ የተከለከሉት ዛፍ እንዳለና ከዚያ ከበሉ እንደሚሞቱ አምላክ ለአዳም እንደነገረው ታውቅ ነበር። ሆኖም ሰይጣን፣ እንደማትሞት በመግለጽ ሔዋንን አታለላት። እንዲያውም የአምላክን ትእዛዝ ብትጥስ የተሻለ ሕይወት እንደሚኖራት እንድታምን አደረጋት። ስለዚህ ሔዋን ከፍሬው የበላች ሲሆን ባሏንም እንዲበላ ገፋፋችው።—ዘፍጥረት 3:1-6፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:14

 ከሔዋን ምን እንማራለን? ሔዋን የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ናት፤ ተገቢ ባልሆኑ ምኞቶች ላይ ማውጠንጠን ምን መዘዝ እንደሚያስከትል ከእሷ ታሪክ በግልጽ ማየት ይቻላል። የእሷ ያልሆነውን ነገር ለማግኘት ያደረባት ምኞት ከማየሉ የተነሳ አምላክ የሰጠውን ግልጽ መመሪያ ጥሳለች።—ዘፍጥረት 3:6፤ 1 ዮሐንስ 2:16

  ሚርያም

 ሚርያም ማን ናት? የሙሴ እና የአሮን እህት ናት። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነቢዪት ተብላ የተጠራች የመጀመሪያዋ ሴት ናት።

 ምን አከናውናለች? ነቢዪት እንደመሆኗ መጠን የአምላክን መልእክት ለሌሎች የመናገር ድርሻ ነበራት። በእስራኤል ውስጥ ከፍ ተደርጋ ትታይ የነበረ ሲሆን አምላክ የግብፅን ሠራዊት በቀይ ባሕር ካጠፋ በኋላ ከወንዶቹ ጋር እየተቀባበለች የድል መዝሙር ዘምራለች።—ዘፀአት 15:1, 20, 21

 ይህ ከሆነ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሚርያምና አሮን ሙሴን ይነቅፉት ጀመር። ይህን ለማድረግ ያነሳሳቸው ኩራትና ቅናት እንደሆነ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። አምላክ ንግግራቸውን “ይሰማ ነበር”፤ በመሆኑም ለሚርያምና ለአሮን ጠንከር ያለ ተግሣጽ ሰጣቸው። (ዘኁልቁ 12:1-9) ከዚያም አምላክ ሚርያምን በሥጋ ደዌ መታት፤ ይህን ያደረገው በሙሴ ላይ የሰነዘሩት ነቀፋ ጠንሳሽ እሷ ስለሆነች ሳይሆን አይቀርም። አምላክ ይቅርታ እንዲያደርግላት ሙሴ ልመና ባቀረበ ጊዜ ከሕመሟ ተፈወሰች። ለሰባት ቀን ከሰፈር ውጭ ተገልላ እንድትቆይ ከተደረገ በኋላ ከእስራኤል ማኅበረሰብ ጋር እንድትቀላቀል ተፈቀደላት።—ዘኁልቁ 12:10-15

 ሚርያም የተሰጣትን እርማት እንደተቀበለች መጽሐፍ ቅዱስ ይጠቁማል። ይህ ከሆነ ከበርካታ መቶ ዘመናት በኋላ አምላክ “ሙሴን፣ አሮንንና ሚርያምን በፊትህ ላክሁ” በማለት ሚርያም የነበራትን ልዩ መብት ለእስራኤል ሕዝብ ተናግሯል።—ሚክያስ 6:4

 ከሚርያም ምን እንማራለን? ከሚርያም ታሪክ እንደምንመለከተው አምላክ፣ አገልጋዮቹ እርስ በርስ የሚባባሉትንም ሆነ አንዳቸው ስለ ሌላው የሚናገሩትን ነገር ይሰማል። በተጨማሪም አምላክን ማስደሰት ከፈለግን ተገቢ ያልሆነ ኩራትንና ቅናትን ማስወገድ እንዳለብን እንማራለን፤ ምክንያቱም እነዚህ ባሕርያት የሌሎችን ስም ለማጥፋት እንድንነሳሳ ሊያደርጉን ይችላሉ።

  ማርታ

 ማርታ ማን ናት? የማርያምና የአልዓዛር እህት ስትሆን ሦስቱም የሚኖሩት በኢየሩሳሌም አቅራቢያ በምትገኝ ቢታንያ በተባለች መንደር ውስጥ ነው።

 ምን አከናውናለች? ማርታ የኢየሱስ የቅርብ ወዳጅ ናት፤ ኢየሱስ “ማርታንና እህቷን እንዲሁም አልዓዛርን ይወዳቸው ነበር።” (ዮሐንስ 11:5) ማርታ እንግዳ ተቀባይ ሴት ናት። በአንድ ወቅት ኢየሱስ ሊጠይቃቸው ሄዶ ሳለ ማርታ በቤት ውስጥ ሥራዎች ተጠምዳ ነበር፤ ማርያም ግን ቁጭ ብላ ታዳምጠው ነበር። ማርታ እህቷ ስላላገዘቻት ለኢየሱስ ቅሬታዋን ገለጸች። ኢየሱስ ግን ለማርታ በደግነት ምክር ሰጣት።—ሉቃስ 10:38-42

 አልዓዛር ሲታመም ማርታና እህቷ፣ ኢየሱስ ወንድማቸውን እንደሚፈውሰው በመተማመን መልእክት ላኩበት። (ዮሐንስ 11:3, 21) ይሁን እንጂ አልዓዛር ሞተ። በዚህ ወቅት ማርታ ከኢየሱስ ጋር ያደረገችው ውይይት በግልጽ እንደሚያሳየው ማርታ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተገለጸው የትንሣኤ ተስፋ እንዲሁም ኢየሱስ ወንድሟን ለማስነሳት ባለው ችሎታ ትተማመን ነበር።—ዮሐንስ 11:20-27

 ከማርታ ምን እንማራለን? ማርታ እንግዶቿን ጥሩ አድርጋ ለማስተናገድ የምትችለውን ሁሉ ታደርግ ነበር። የተሰጣትን ምክር በትሕትና ተቀብላለች። ሐሳቧንና እምነቷን በግልጽ የምትናገር ሴት ናት።

  •   ስለ ማርታ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “አምናለሁ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

  ማርያም (መግደላዊቷ)

 መግደላዊቷ ማርያም ማን ናት? የኢየሱስ ታማኝ ደቀ መዝሙር ናት።

 ምን አከናውናለች? መግደላዊቷ ማርያም ከኢየሱስና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ይጓዙ ከነበሩ ሴቶች አንዷ ናት። እነሱ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማሟላት ንብረቷን በልግስና ሰጥታለች። (ሉቃስ 8:1-3) ኢየሱስ አገልግሎቱን እስካጠናቀቀበት ጊዜ ድረስ አብራው የነበረች ሲሆን በተገደለበት ወቅትም ከአጠገቡ አልራቀችም። ኢየሱስ ከሞት እንደተነሳ እሱን የማየት አጋጣሚ ካገኙት የመጀመሪያ ሰዎች አንዷ ናት።—ዮሐንስ 20:11-18

 ከማርያም ምን እንማራለን? መግደላዊቷ ማርያም ኢየሱስ ያከናወነውን አገልግሎት ለመደገፍ ስትል ንብረቷን በልግስና ሰጥታለች፤ ደግሞም እስከ መጨረሻው በታማኝነት ከጎኑ ቆማለች።

  ማርያም (የማርታ እና የአልዓዛር እህት)

 ማርያም ማን ናት? ከኢየሱስ የቅርብ ወዳጆች አንዷ ናት፤ ወንድሟ አልዓዛርና እህቷ ማርታም ወዳጆቹ ናቸው።

 ምን አከናውናለች? ማርያም የአምላክ ልጅ ለሆነው ለኢየሱስ አክብሮት እንዳላት በተደጋጋሚ አሳይታለች። ኢየሱስ፣ ወንድሟ አልዓዛር እንዳይሞት ማድረግ ይችል እንደነበር ያላትን እምነት ገልጻለች፤ ኢየሱስ እሱን ከሞት ባስነሳበት ጊዜም አብራው ነበረች። በአንድ ወቅት ማርያም በቤት ውስጥ ሥራዎች እህቷን ማርታን ከማገዝ ይልቅ ኢየሱስን ለማዳመጥ በመምረጧ ማርታ ቅሬታዋን አሰምታለች። ኢየሱስ ግን ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ በመስጠቷ ማርያምን አድንቋታል።—ሉቃስ 10:38-42

 በሌላ ወቅት ደግሞ ማርያም “በጣም ውድ የሆነና ጥሩ መዓዛ ያለው ዘይት” በኢየሱስ ራስና እግር ላይ በማፍሰስ ለየት ያለ ልግስና አሳይታለች። (ማቴዎስ 26:6, 7) በቦታው የነበሩ አንዳንዶች የማርያም ድርጊት ብክነት እንደሆነ በመግለጽ ወቀሷት። ኢየሱስ ግን “በመላው ዓለም [የአምላክ መንግሥት] ምሥራች በሚሰበክበት ቦታ ሁሉ ይህች ሴት ያደረገችውም መታሰቢያ ሆኖ ይነገርላታል” በማለት ደግፏታል።—ማቴዎስ 24:14፤ 26:8-13

 ከማርያም ምን እንማራለን? ማርያም ጥልቅ እምነት ያላት ሴት ናት። ከዕለት ተዕለት ጉዳዮች ይልቅ መንፈሳዊ ነገሮችን አስቀድማለች። ለኢየሱስ ያላትን አክብሮት ለማሳየት ስትል ብዙ ወጪ የሚያስወጣትን ነገር አድርጋለች።

  ማርያም (የኢየሱስ እናት)

 ማርያም ማን ናት? አይሁዳዊት ሴት ስትሆን የአምላክን ልጅ በተአምራዊ ሁኔታ ፀንሳለች፤ ይህች ወጣት ኢየሱስን በወለደችበት ወቅት ድንግል ነበረች።

 ምን አከናውናለች? ማርያም የአምላክን ፈቃድ በትሕትና ፈጽማለች። አንድ መልአክ ለማርያም ተገልጦ እንደምትፀንስና ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የቆየውን መሲሕ እንደምትወልድ በነገራት ወቅት ማርያም ለዮሴፍ ታጭታ ነበር። (ሉቃስ 1:26-33) ማርያም የተሰጣትን ኃላፊነት ለመወጣት ፈቃደኛ ሆናለች። ኢየሱስ ከተወለደ በኋላ ዮሴፍና ማርያም አራት ወንዶችና ቢያንስ ሁለት ሴቶች ልጆች ወልደዋል። ስለዚህ ማርያም ድንግል ሆና አልቀጠለችም። (ማቴዎስ 13:55, 56) ማርያም ልዩ መብት ያገኘች ቢሆንም ኢየሱስ በምድር ላይ አገልግሎቱን ባከናወነበት ጊዜም ሆነ የጥንቱ የክርስቲያን ጉባኤ በተቋቋመበት ወቅት የተለየ ውዳሴ እንዲሰጣት አልፈለገችም፤ እንዲህ እንደተደረገላት የሚጠቁም ማስረጃም የለም።

 ከማርያም ምን እንማራለን? ማርያም የተሰጣትን ከባድ ኃላፊነት በፈቃደኝነት የተቀበለች ታማኝ ሴት ናት። ስለ ቅዱሳን መጻሕፍት ጥልቀት ያለው እውቀት ነበራት። በሉቃስ 1:46-55 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ በተናገረችበት ወቅት ማርያም 20 ጊዜ ያህል ከቅዱሳን መጻሕፍት እንደጠቀሰች ይገመታል።

  ሣራ

 ሣራ ማን ናት? የአብርሃም ሚስትና የይስሐቅ እናት ናት።

 ምን አከናውናለች? ሣራ፣ አምላክ ለባሏ በገባው ቃል ላይ እምነት ስለነበራት የበለጸገች ከተማ በነበረችው በዑር የነበራትን የተመቻቸ ሕይወት ትታ ለመሄድ ፈቃደኛ ሆናለች። አብርሃም ዑርን ለቆ ወደ ከነአን ምድር እንዲሄድ አምላክ ነገረው። አብርሃምን እንደሚባርከውና ታላቅ ሕዝብ እንደሚያደርገውም ቃል ገባለት። (ዘፍጥረት 12:1-5) በወቅቱ ሣራ በ60ዎቹ ዕድሜ ውስጥ ሳትሆን አትቀርም። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሣራና ባለቤቷ ከቦታ ወደ ቦታ እየተዟዟሩ በድንኳን ውስጥ መኖር ጀመሩ።

 እንዲህ ያለው ሕይወት ሣራን ለአደጋ ቢያጋልጣትም አብርሃም አምላክን ለመታዘዝ የሚያደርገውን ጥረት ደግፋለች። (ዘፍጥረት 12:10, 15) ሣራ ለብዙ ዓመታት ልጅ አልነበራትም፤ በዚህም የተነሳ በጣም ታዝን ነበር። ሆኖም አምላክ የአብርሃምን ዘር እንደሚባርክ ቃል ገብቶ ነበር። (ዘፍጥረት 12:7፤ 13:15፤ 15:18፤ 16:1, 2, 15) ከጊዜ በኋላ አምላክ፣ ሣራ ልጅ እንደምትወልድለት ለአብርሃም አረጋገጠለት። ሣራ፣ ልጅ የመውለጃ ዕድሜዋ ካለፈ ከረጅም ጊዜ በኋላ ልጅ ወለደች። በዚህ ወቅት እሷ 90 ዓመቷ ሲሆን ባሏ ደግሞ 100 ዓመቱ ነበር። (ዘፍጥረት 17:17፤ 21:2-5) ልጃቸውን ይስሐቅ ብለው ጠሩት።

 ከሣራ ምን እንማራለን? አምላክ፣ የሚፈጸም የማይመስለንን ጨምሮ ቃሉን ምንጊዜም እንደሚጠብቅ መተማመን እንደምንችል ከሣራ ታሪክ እንማራለን። (ዕብራውያን 11:11) ሣራ ጥሩ ሚስት በመሆን የተወችው ምሳሌ፣ በትዳር ውስጥ አክብሮት ማሳየት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያጎላል።—1 ጴጥሮስ 3:5, 6

  ረዓብ

 ረዓብ ማን ናት? የከነአናውያን ከተማ በሆነችው በኢያሪኮ የምትኖር ዝሙት አዳሪ ነበረች፤ በኋላ ላይ የይሖዋ አምላኪ ሆናለች።

 ምን አከናውናለች? ረዓብ፣ ምድሪቱን እየሰለሉ የነበሩ ሁለት እስራኤላውያንን ደብቃለች። ይህን ያደረገችው የእስራኤል አምላክ የሆነው ይሖዋ፣ ሕዝቡን ከግብፅ እንዴት እንዳወጣቸው እንዲሁም በኋላ ላይ ከአሞራውያን ጥቃት እንዴት እንደታደጋቸው ስለሰማች ነው።

 ረዓብ ሰላዮቹን የረዳቻቸው ሲሆን እስራኤላውያን ኢያሪኮን ለማጥፋት በሚመጡበት ጊዜ እሷንና ቤተሰቧን ከሞት እንዲታደጓቸው ለመነቻቸው። ሰላዮቹም ይህን ለማድረግ ተስማሙ፤ ሆኖም ረዓብ ስለ እነሱ ተልእኮ ለማንም እንዳትናገር፣ እስራኤላውያን ጥቃት በሚሰነዝሩበት ወቅት እሷም ሆነች መላ ቤተሰቧ ከቤቷ እንዳይወጡ እንዲሁም ቤቷን ለመለየት እንዲያመች በመስኮቷ ላይ ቀይ ገመድ እንድታንጠለጥል ነገሯት። ረዓብ የነገሯትን ሁሉ አድርጋለች፤ በመሆኑም እስራኤላውያን ኢያሪኮን ሲቆጣጠሩ እሷም ሆነች ቤተሰቧ መትረፍ ችለዋል።

 ረዓብ ከጊዜ በኋላ አንድ እስራኤላዊ ያገባች ሲሆን የንጉሥ ዳዊትና የኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ አያት መሆን ችላለች።—ኢያሱ 2:1-24፤ 6:25፤ ማቴዎስ 1:5, 6, 16

 ከረዓብ ምን እንማራለን? ረዓብ ግሩም የእምነት ምሳሌ እንደሆነች መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ዕብራውያን 11:30, 31፤ ያዕቆብ 2:25) የረዓብ ታሪክ፣ ይሖዋ ይቅር ባይና የማያዳላ አምላክ እንደሆነ ይኸውም በእሱ የሚታመኑ ሰዎችን ዘራቸውም ሆነ የቀድሞ ሕይወታቸው ምንም ዓይነት ቢሆን እንደሚባርካቸው ያሳያል።

  ሩት

 ሩት ማን ናት? ሞዓባዊት ሴት ናት፤ ይሖዋን በእስራኤል ምድር ለማምለክ ስትል አማልክቷንና አገሯን ትታ ሄዳለች።

 ምን አከናውናለች? ሩት ለአማቷ ለናኦሚ ለየት ያለ ፍቅር አሳይታለች። በእስራኤል ምድር በተከሰተው ረሃብ የተነሳ ናኦሚ፣ ባሏና ሁለቱ ወንዶች ልጆቻቸው ወደ ሞዓብ ሄዱ። ከጊዜ በኋላ ልጆቹ፣ ሩት እና ዖርፋ የተባሉ ሞዓባውያን ሴቶች አገቡ። ውሎ አድሮ ግን የናኦሚ ባልና ሁለቱ ወንዶች ልጆቿ ሞቱ፤ በመሆኑም ሦስቱ ሴቶች መበለቶች ሆኑ።

 በእስራኤል ምድር የድርቁ ጊዜ ሲያበቃ ናኦሚ ወደዚያ ለመመለስ ወሰነች። ሩትና ዖርፋም አብረዋት ለመሄድ ተነሱ። ናኦሚ ግን ወደ ዘመዶቻቸው እንዲመለሱ ጠየቀቻቸው። ዖርፋ እንደተባለችው አደረገች። (ሩት 1:1-6, 15) ሩት ግን አማቷን የሙጥኝ አለች። ሩት ናኦሚን የምትወዳት ከመሆኑም ሌላ የእሷን አምላክ ይሖዋን ማምለክ ፈልጋ ነበር።—ሩት 1:16, 17፤ 2:11

 ሩት ታማኝ ምራትና ትጉ ሠራተኛ በመሆኗ የናኦሚ የትውልድ አካባቢ በሆነው በቤተልሔም መልካም ስም አተረፈች። ቦዔዝ የተባለ ሀብታም ባለርስት ሩት ባደረገችው ነገር በጣም ስለተደነቀ ለእሷም ሆነ ለናኦሚ ብዙ ምግብ ሰጣቸው። (ሩት 2:5-7, 20) ከጊዜ በኋላ ሩት ቦዔዝን ያገባች ሲሆን የንጉሥ ዳዊት እና የኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ አያት መሆን ችላለች።—ማቴዎስ 1:5, 6, 16

 ከሩት ምን እንማራለን? ሩት ናኦሚንና ይሖዋን ስለምትወድ ቤቷንና ቤተሰቦቿን ትታ ለመሄድ ፈቃደኛ ሆናለች። ሩት ታታሪና አፍቃሪ ሴት ናት፤ በአስቸጋሪ ጊዜም እንኳ ታማኝ እንደሆነች አሳይታለች።

  ራሔል

 ራሔል ማን ናት? የላባ ልጅና የያዕቆብ ሚስት ናት፤ ያዕቆብ ራሔልን አብልጦ ይወዳት ነበር።

 ምን አከናውናለች? ራሔል ያዕቆብን አግብታ ሁለት ወንዶች ልጆች ወልዳለች፤ እነዚህ ልጆች የጥንቱን እስራኤል 12 ነገዶች ካስገኙት የያዕቆብ ልጆች መካከል ይገኙበታል። ራሔል በኋላ ላይ ባሏ ከሆነው ከያዕቆብ ጋር የተገናኘችው የአባቷን በጎች እየጠበቀች ሳለ ነው። (ዘፍጥረት 29:9, 10) ከታላቅ እህቷ ከሊያ በተለየ ራሔል “ዓይን የምትማርክ” ሴት ነበረች።—ዘፍጥረት 29:17

 ያዕቆብ ራሔልን ስለወደዳት እሷን ለማግባት ሲል ለሰባት ዓመት ለመሥራት ተስማማ። (ዘፍጥረት 29:18) ይሁን እንጂ ላባ ያዕቆብን በማታለል መጀመሪያ ሊያን እንዲያገባ አደረገ፤ ራሔልን እንዲያገባ ለያዕቆብ የፈቀደለት ከዚያ በኋላ ነው።—ዘፍጥረት 29:25-27

 ያዕቆብ ከሊያና ከእሷ ከወለዳቸው ልጆች ይበልጥ ራሔልንና ሁለት ወንዶች ልጆቿን ይወዳቸው ነበር። (ዘፍጥረት 37:3፤ 44:20, 27-29) ይህም በሁለቱ ሴቶች መካከል ፉክክር እንዲኖር አድርጓል።—ዘፍጥረት 29:30፤ 30:1, 15

 ከራሔል ምን እንማራለን? ራሔል፣ አምላክ ጸሎቷን እንደሚሰማላት በመተማመን በቤተሰቧ ውስጥ የገጠማትን አስቸጋሪ ሁኔታ በጽናት ተቋቁማለች። (ዘፍጥረት 30:22-24) የራሔል ታሪክ፣ ከአንድ በላይ ማግባት በቤተሰብ ውስጥ የሚፈጥረውን ችግር ያሳያል። ራሔል ያጋጠማት ነገር አምላክ ለጋብቻ ያወጣው መሥፈርት ጥበብ የተንጸባረቀበት እንደሆነ ያሳያል፤ የአምላክ ዓላማ አንድ ወንድ አንዲት ሴትን ብቻ እንዲያገባ ነው።—ማቴዎስ 19:4-6

  ርብቃ

 ርብቃ ማን ናት? የይስሐቅ ሚስት ስትሆን ያዕቆብ እና ኤሳው የተባሉ መንታ ልጆች ወልዳለች።

 ምን አከናውናለች? ርብቃ የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ከባድ በሚሆንበት ጊዜም እንኳ ይህን አድርጋለች። ከጉድጓድ ውኃ እየቀዳች ሳለ አንድ ሰው ውኃ እንድታጠጣው ጠየቃት። ርብቃ ፈጠን ብላ የሚጠጣ ውኃ ከሰጠችው በኋላ የሰውየውን ግመሎችም እንደምታጠጣለት ነገረችው። (ዘፍጥረት 24:15-20) ይህ ሰው የአብርሃም አገልጋይ ሲሆን ለአብርሃም ልጅ ለይስሐቅ ሚስት ለማግኘት ረጅም ርቀት ተጉዟል። (ዘፍጥረት 24:2-4) በተጨማሪም ሰውየው የአምላክን በረከት ለማግኘት ጸልዮ ነበር። ርብቃ ታታሪና እንግዳ ተቀባይ ሴት መሆኗን ሲያስተውል አምላክ ጸሎቱን እንደመለሰለት ይኸውም ርብቃ አምላክ ለይስሐቅ የመረጣት ሴት እንደሆነች ተገነዘበ።—ዘፍጥረት 24:10-14, 21, 27

 ርብቃ ሰውየው የመጣበትን ምክንያት ስታውቅ ከእሱ ጋር ለመሄድና ይስሐቅን ለማግባት ተስማማች። (ዘፍጥረት 24:57-59) ከጊዜ በኋላ ርብቃ መንታ ወለደች። ታላቅየው ልጅ ኤሳው፣ ታናሹን ያዕቆብን እንደሚያገለግል አምላክ ለርብቃ ነግሯት ነበር። (ዘፍጥረት 25:23) ይስሐቅ ለበኩር ልጅ የሚገባውን በረከት ለኤሳው ለመስጠት ባሰበበት ወቅት ርብቃ በረከቱ ለያዕቆብ እንዲሰጥ ስትል እርምጃ ወስዳለች፤ ምክንያቱም የአምላክ ፈቃድ ይህ እንደሆነ አውቃ ነበር።—ዘፍጥረት 27:1-17

 ከርብቃ ምን እንማራለን? ርብቃ ትሑት፣ ታታሪና እንግዳ ተቀባይ ሴት ናት፤ እነዚህ ባሕርያት ጥሩ ሚስትና እናት እንድትሆን እንዲሁም እውነተኛውን አምላክ እንድታመልክ አስችለዋታል።

  •   ስለ ርብቃ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “አዎ፣ እሄዳለሁ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

  ሱላማዊቷ ልጃገረድ

 ሱላማዊቷ ልጃገረድ ማን ናት? ውብ የሆነች የገጠር ልጅ ናት፤ መኃልየ መኃልይ በተባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ የተጠቀሰች ዋነኛ ባለታሪክ ናት። መጽሐፍ ቅዱስ ስሟን አይነግረንም።

 ምን አከናውናለች? ሱላማዊቷ ልጃገረድ ለምትወደው እረኛ ምንጊዜም ታማኝ እንደሆነች አሳይታለች። (መኃልየ መኃልይ 2:16) ባለጸጋ የነበረው ንጉሥ ሰለሞን አስደናቂ በሆነው ውበቷ ስለተማረከ ሊያማልላት ሞክሮ ነበር። (መኃልየ መኃልይ 7:6) አንዳንዶች ሰለሞንን እንድትመርጥ ሊገፋፏት ቢሞክሩም ሱላማዊቷ ልጃገረድ በዚህ አልተስማማችም። እሷ የወደደችው እረኛውን ሲሆን ለእሱም ታማኝ ሆናለች።—መኃልየ መኃልይ 3:5፤ 7:10፤ 8:6

 ከሱላማዊቷ ልጃገረድ ምን እንማራለን? ውብ ከመሆኗም ሌላ የብዙዎችን ትኩረት መሳብ ብትችልም ራሷን ከፍ አድርጋ አልተመለከተችም። የእኩዮቿ ተጽዕኖም ሆነ ሀብታምና ታዋቂ እንደምትሆን የቀረበላት ማባበያ የምትወደውን እረኛ እንድትተው አላደረጋትም። በተጨማሪም ራሷን በመግዛት ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናዋን ጠብቃለች።

  አስቴር

 አስቴር ማን ናት? የፋርስ ንጉሥ አሐሽዌሮስ ንግሥት እንድትሆን የመረጣት አይሁዳዊት ሴት ናት።

 ምን አከናውናለች? ንግሥት አስቴር ሥልጣኗን በመጠቀም፣ በወገኖቿ ላይ ሊሰነዘር የነበረውን የዘር ማጥፋት ዘመቻ ማስቀረት ችላለች። አስቴር በፋርስ ግዛት የሚኖሩ አይሁዳውያን በሙሉ እንዲገደሉ የሚያዝዝና ይህ የሚደረግበትን ቀን የሚገልጽ አዋጅ እንደወጣ አወቀች። ይህን ሴራ የጠነሰሰው ሃማ የተባለ ክፉ ሰው ነው፤ ሃማ ጠቅላይ ሚኒስትር ነበር። (አስቴር 3:13-15፤ 4:1, 5) አስቴር ሕይወቷን አደጋ ላይ መጣል ቢኖርባትም እንኳ ከአጎቷ ልጅ ከመርዶክዮስ ጋር በመተባበር የሃማን ሴራ ለባለቤቷ ለንጉሥ አሐሽዌሮስ አሳወቀች። (አስቴር 4:10-16፤ 7:1-10) አሐሽዌሮስም አስቴር እና መርዶክዮስ፣ አይሁዳውያን ራሳቸውን ከጥቃት እንዲከላከሉ የሚያዝዝ ሌላ አዋጅ እንዲያወጡ ፈቀደላቸው። በመሆኑም አይሁዳውያኑ፣ ጠላቶቻቸውን በሙሉ ድል አደረጉ።—አስቴር 8:5-11፤ 9:16, 17

 ከአስቴር ምን እንማራለን? ንግሥት አስቴር በድፍረትና በትሕትና ረገድ ግሩም ምሳሌ ትሆነናለች። (መዝሙር 31:24፤ ፊልጵስዩስ 2:3) ውበትና ሥልጣን ቢኖራትም እንኳ የሌሎችን ምክርና እርዳታ ጠይቃለች። ባለቤቷን ያነጋገረችው በዘዴና በአክብሮት ቢሆንም ድፍረትም አሳይታለች። አይሁዳዊ መሆን ለአደጋ ያጋልጥ በነበረበት ጊዜም እንኳ አይሁዳዊት መሆኗን በድፍረት ተናግራለች።

  አቢጋኤል

 አቢጋኤል ማን ናት? ናባል የተባለው ሀብታም ሰው ሚስት ነበረች፤ ናባል ኃይለኛ ሰው ነበር። አቢጋኤል ግን አስተዋይና ትሑት ሴት ናት፤ ውብ ከመሆኗም ሌላ መንፈሳዊ ሰው ናት።—1 ሳሙኤል 25:3

 ምን አከናውናለች? አቢጋኤል በቤተሰቧ ላይ አደጋ እያንዣበበ እንደሆነ ስትመለከት በጥበብና በማስተዋል እርምጃ በመውሰድ ቤተሰቧን ከጥፋት ታድጋለች። እሷና ናባል የሚኖሩት የእስራኤል የወደፊት ንጉሥ እንዲሆን የተቀባው ዳዊት በስደት በሚኖርበት አካባቢ ነበር። ዳዊትና ሰዎቹ በዚያ እያሉ የናባልን በጎች ከዘራፊዎች ጠብቀውለት ነበር። ዳዊት ምግብ እንዲሰጠው መልዕክተኞችን ወደ ናባል ሲልክ ግን ናባል የከለከላቸው ከመሆኑም ሌላ ሰዎቹን አዋርዶ መለሳቸው። ዳዊት በዚህ በጣም ተቆጣ! በመሆኑም ሰዎቹን አሰባስቦ ናባልንና በቤቱ ያሉትን ወንዶች በሙሉ ለመግደል መንገድ ጀመረ።—1 ሳሙኤል 25:10-12, 22

 አቢጋኤል ባሏ ያደረገውን ስትሰማ ወዲያውኑ እርምጃ ወሰደች። ለዳዊትና ለሰዎቹ የሚሆን ምግብ በአገልጋዮቿ በኩል ከላከች በኋላ ዳዊት ምሕረት እንዲያደርግላቸው ለመለመን ተከትላቸው ሄደች። (1 ሳሙኤል 25:14-19, 24-31) ዳዊት አቢጋኤል የላከችውን ስጦታና ትሕትናዋን ሲመለከት እንዲሁም ጥበብ የተንጸባረቀበት ምክሯን ሲሰማ ሐሳቡን ቀየረ፤ አምላክ በአቢጋኤል ተጠቅሞ አሳዛኝ ነገር ከመፈጸም እንደጠበቀው ተገነዘበ። (1 ሳሙኤል 25:32, 33) ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ናባል የሞተ ሲሆን አቢጋኤልም የዳዊት ሚስት ሆነች።—1 ሳሙኤል 25:37-41

 ከአቢጋኤል ምን እንማራለን? አቢጋኤል ውብና ሀብታም ብትሆንም ራሷን ከፍ አድርጋ አልተመለከተችም። ሰላም ለመፍጠር ስትል የእሷ ጥፋት ላልሆነ ነገር ይቅርታ ለመጠየቅ ፈቃደኛ ሆናለች። በዘዴና በብልሃት እንዲሁም በድፍረት እርምጃ በመውሰድ ውጥረት የነገሠበትን ሁኔታ ማብረድ ችላለች።

  ኢያዔል

 ኢያዔል ማን ናት? ሄቤር የተባለ እስራኤላዊ ያልሆነ ሰው ሚስት ናት። ኢያዔል በድፍረት የአምላክን ሕዝብ ደግፋለች።

 ምን አከናውናለች? ኢያዔል የከነአናውያን ሠራዊት አለቃ የሆነው ሲሳራ ወደ ድንኳኗ በመጣበት ወቅት ቆራጥ እርምጃ ወስዳለች ሲሳራ ከእስራኤላውያን ጋር ባደረገው ጦርነት ስለተሸነፈ የሚሸሸግበትና የሚያርፍበት ቦታ እየፈለገ ነበር። ኢያኤል ወደ ድንኳኗ ገብቶ እንዲያርፍ ጋበዘችው። ከዚያም በተኛበት ገደለችው።—መሳፍንት 4:17-21

 ኢያዔል የወሰደችው እርምጃ “ይሖዋ ሲሳራን በሴት እጅ አሳልፎ [እንደሚሰጠው]” ዲቦራ የተናገረችው ትንቢት እንዲፈጸም አድርጓል። (መሳፍንት 4:9) ኢያዔል ለድሉ ያበረከተችው አስተዋጽኦ “ከሴቶች ሁሉ እጅግ የተባረከች ነች” እንድትባል አድርጓታል።—መሳፍንት 5:24

 ከኢያዔል ምን እንማራለን? ኢያዔል በራሷ ተነሳስታ የድፍረት እርምጃ ወስዳለች። ይህ ታሪክ፣ አምላክ ትንቢቱ እንዲፈጸም ለማድረግ ሲል ሁኔታዎችን እንዴት እንደሚያመቻች ያሳየናል።

  ኤልዛቤል

 ኤልዛቤል ማን ናት? የእስራኤል ንጉሥ የሆነው የአክዓብ ሚስት ናት። እስራኤላዊት አይደለችም፤ ይሖዋንም አታመልክም። ኤልዛቤል የምታመልከው የከነአናውያን አምላክ የሆነውን ባአልን ነው።

 ምን አከናውናለች? ንግሥት ኤልዛቤል ማናለብኝ ባይ፣ ጨካኝና ክፉ ሴት ናት። የባአል አምልኮና ከዚህ አምልኮ ጋር የተያያዘው የፆታ ብልግና እንዲስፋፋ አድርጋለች። ይህም እንዳይበቃት ደግሞ ለእውነተኛው አምላክ ለይሖዋ የሚቀርበው አምልኮ እንዲጠፋ ለማድረግ ጥራለች።—1 ነገሥት 18:4, 13፤ 19:1-3

 ኤልዛቤል የፈለገችውን ነገር ለማግኘት ስትል ከመዋሸትና ነፍስ ከማጥፋት ወደኋላ የማትል ሴት ናት። (1 ነገሥት 21:8-16) አሟሟቷ ዘግናኝ እንደሚሆንና በሥርዓቱ እንደማትቀበር አምላክ ያስነገረው ትንቢት ተፈጽሟል።—1 ነገሥት 21:23፤ 2 ነገሥት 9:10, 32-37

 ከኤልዛቤል ምን እንማራለን? ኤልዛቤል የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ናት። ወራዳ ሥነ ምግባር የነበራትና ምንም ነገር ከማድረግ የማትመለስ በመሆኗ የዚህች ሴት ስም እፍረት የለሽና ጋጠ ወጥ የሆኑ ሴቶችን ለማመልከት ይሠራበታል።

  የሎጥ ሚስት

 የሎጥ ሚስት ማን ናት? መጽሐፍ ቅዱስ ስሟን አይነግረንም። ይሁንና ሁለት ሴቶች ልጆች እንዳሏትና ከቤተሰቧ ጋር ሆና በሰዶም ከተማ ትኖር እንደነበር ይናገራል።—ዘፍጥረት 19:1, 15

 ምን አከናውናለች? የአምላክን ትእዛዝ ጥሳለች። በሰዶምና በአቅራቢያዋ ባሉ ከተሞች ልቅ የፆታ ብልግና ይፈጸም ስለነበር አምላክ ከተሞቹን ለማጥፋት ወሰነ። አምላክ ለጻድቁ ሎጥና ለቤተሰቡ ባለው ፍቅር የተነሳ ሁለት መላእክትን በመላክ ከሰዶም እንዲያስወጧቸው አደረገ።—ዘፍጥረት 18:20፤ 19:1, 12, 13

 ሎጥና ቤተሰቡ ከአካባቢው እንዲሸሹና ወደ ኋላ እንዳይመለከቱ መላእክቱ ነገሯቸው፤ ወደ ኋላ ከተመለከቱ እንደሚሞቱ አስጠነቀቋቸው። (ዘፍጥረት 19:17) የሎጥ ሚስት ግን “ወደ ኋላ ዞራ መመልከት ጀመረች፤ እሷም የጨው ዓምድ ሆነች።”—ዘፍጥረት 19:26

 ከሎጥ ሚስት ምን እንማራለን? የእሷ ታሪክ፣ ለቁሳዊ ነገሮች ያለን ፍቅር የአምላክን ትእዛዝ እስከ መጣስ የሚያደርስ ከሆነ ምን አደጋ እንደሚያጋጥመን ያሳያል። ኢየሱስ የሎጥን ሚስት የማስጠንቀቂያ ምሳሌ አድርጎ ጠቅሷታል። “የሎጥን ሚስት አስታውሱ” ብሏል።—ሉቃስ 17:32

  ደሊላ

 ደሊላ ማን ናት? የእስራኤል መስፍን የሆነው ሳምሶን የወደዳት ሴት ናት።—መሳፍንት 16:4, 5

 ምን አከናውናለች? አምላክ እስራኤላውያንን ከፍልስጤማውያን ለመታደግ ይጠቀምበት የነበረውን ሳምሶንን ለፍልስጤማውያን አሳልፋ ሰጥታለች፤ ይህን ያደረገችው የፍልስጤም ገዢዎች ገንዘብ ስለሰጧት ነው። ሳምሶን ከአምላክ ያገኘው ከፍተኛ ጥንካሬ ስለነበረው ፍልስጤማውያን ሊያሸንፉት አልቻሉም። (መሳፍንት 13:5) ስለዚህ የፍልስጤም ገዢዎች ደሊላን እንድትረዳቸው ጠየቋት።

 ፍልስጤማውያን ለደሊላ ጉቦ በመስጠት ሳምሶን እንዲህ ያለ ከፍተኛ ጥንካሬ ሊኖረው የቻለው ለምን እንደሆነ እንድታውጣጣው ጠየቋት። ደሊላም ገንዘቡን ማግኘት ስለፈለገች ሚስጥሩን ለማወቅ በተደጋጋሚ ሞከረች፤ በመጨረሻም ያሰበችው ተሳካላት። (መሳፍንት 16:15-17) ከዚያም ሚስጥሩን ለፍልስጤማውያን የነገረቻቸው ሲሆን እነሱም ሳምሶንን ይዘው እስር ቤት አስገቡት።—መሳፍንት 16:18-21

 ከደሊላ ምን እንማራለን? ደሊላ የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ናት። ራስ ወዳድና ስግብግብ መሆኗ የይሖዋን አገልጋይ እንድታታልልና እንድትከዳ አድርጓታል።

  ዲቦራ

 ዲቦራ ማን ናት? ነቢዪት ስትሆን የእስራኤል አምላክ የሆነው ይሖዋ ከሕዝቡ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በተመለከተ ዓላማው ምን እንደሆነ ለመግለጥ ተጠቅሞባታል። በተጨማሪም አምላክ በእስራኤላውያን መካከል ፈራጅ ሆና እንድታገለግል አድርጓል።—መሳፍንት 4:4, 5

 ምን አከናውናለች? ነቢይቷ ዲቦራ የአምላክን አገልጋዮች በድፍረት ደግፋለች። አምላክ በሰጠው መመሪያ መሠረት ባርቅን ካስጠራችው በኋላ የእስራኤልን ሠራዊት በመምራት፣ ይጨቁኗቸው በነበሩት ከነአናውያን ላይ እንዲዘምት ነገረችው። (መሳ. 4:6, 7) ባርቅ አብራው እንድትሄድ ሲጠይቃትም ዲቦራ ሳትፈራ እሱ እንዳላት አድርጋለች።—መሳፍንት 4:8, 9

 አምላክ፣ እስራኤላውያን በጠላቶቻቸው ላይ ወሳኝ ድል እንዲቀዳጁ ረዳቸው፤ ይህን ድል በተመለከተ ዲቦራና ባርቅ ከዘመሩት መዝሙር የተወሰነውን ያቀናበረችው ዲቦራ ናት። ዲቦራ በዚህ መዝሙር ላይ፣ ኢያዔል የተባለች ደፋር ሴት ከነአናውያንን ድል በማድረግ ረገድ ስለተጫወተችው ሚናም ገልጻለች።—መሳፍንት ምዕራፍ 5

 ከዲቦራ ምን እንማራለን? ዲቦራ የራሷን ጥቅም መሥዋዕት የምታደርግ ደፋር ሴት ናት። ሌሎች በአምላክ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር እንዲያደርጉ አበረታታለች። ይህን ሲያደርጉም ላከናወኑት ነገር አመስግናቸዋለች።

 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ሴቶች—የጊዜ ሰሌዳ

  1.  ሔዋን

  2. የጥፋት ውኃ (2370 ዓ.ዓ.)

  3.  ሣራ

  4.  የሎጥ ሚስት

  5.  ርብቃ

  6.  ሊያ

  7.  ራሔል

  8. ዘፀአት (1513 ዓ.ዓ.)

  9.  ሚርያም

  10.  ረዓብ

  11.  ሩት

  12.  ዲቦራ

  13.  ኢያዔል

  14.  ደሊላ

  15.  ሐና

  16. የእስራኤል የመጀመሪያ ንጉሥ (1117 ዓ.ዓ.)

  17.  አቢጋኤል

  18.  ሱላማዊቷ ልጃገረድ

  19.  ኤልዛቤል

  20.  አስቴር

  21.  ማርያም (የኢየሱስ እናት)

  22. ኢየሱስ ተጠመቀ (29 ዓ.ም.)

  23.  ማርታ

  24.  ማርያም (የማርታ እና የአልዓዛር እህት)

  25.  ማርያም (መግደላዊቷ)

  26. ኢየሱስ ሞተ (33 ዓ.ም.)